Latest

"ዶክተር ዐብይን መደገፋችን ዋጋ አስከፍሎናል" ከወልቃይት የተፈናቀለው ክንፈ ጥላሁን - ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው

ክንፈ ጥላሁን

~ አማራዎች ዶ/ር አብይን መደገፋችን ለጥቃት አጋልጦናል። ሰንደቅ አላማ፣ የዶ/ር ዐብይ ምስል ያለበት ቲ ሸርት፣ የአፄ ቴዎድሮስ ቲ ሸርት እንዲሁም ጃኖ የለበሰ ሰው "የአሸባሪ ልብስ የለበሰ" እየተባለ ይደበደባል፣ ይታሰራል፣ ይሰደዳል።

ክንፈ ጥላሁን እባላለሁ። የመጣሁት ከወልቃይት ወረዳ ነው። አዲስ አበባ የመጣነው አማራ ሆነን በወልቃይት መኖር ስላልቻልን ተፈናቅለን፣ ከፌደራል መንግስት መፍትሔ ለማግኘት ነው። 


እኛ የወልቃይት ሰዎች አማራ ሆነን፣ በአማርኛ መማር አልቻልንም፣ አማራ ሆነን በአማራ መሬት ነግደን አትርፈን መኖር አልቻልንም። ቋንቋችን በነፃነት ማውራትም መማርም አልቻልንም። አማርኛ ከዘፈንኩ ወይ ካወራሁ እታሰራለሁ ወይንም እገረፋለሁ።  

መኪናዬ ላይ የዶ/ር ዐብይን ፎቶ ከለጠፍኩ በትራፊክ ፖሊስ ያለአግባብ እቀጣለሁ። ሱቅ ላይ ስለ ዶ/ር ዐብይ የተለጠፈ ነገር ካለ በግብር እያሳበቡ ቅጣት ይጥላሉ።

የአማራነት ነገር ከታየብህ ለእንግልትና ለድብደባ፣ ለእስር መዳረግህ አይቀርም። በወልቃይት ያለው ችግር ጎልቶ የታየው ዶ/ር ዐብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ነው። አማራዎች ዶ/ር አብይን መደገፋችን ለጥቃት አጋልጦናል።

ሰንደቅ አላማ፣ የዶ/ር ዐብይ ምስል ያለበት ቲ ሸርት፣ የአፄ ቴዎድሮስ ቲ ሸርት እንዲሁም ጃኖ የለበሰ ሰው "የአሸባሪ ልብስ የለበሰ" እየተባለ ይደበደባል፣ ይታሰራል፣ ይሰደዳል። በዚህ መንገድ ተደብድበው የት እንደደረሱ ያላወቅናቸው ጓደኞቻችን አሉ።

እኔ እስከ 10ኛ ክፍል ተምሬያለሁ። የተማርኩት ሳልወድ በግድ በትግርኛ ነው። አማርኛ ቋንቋ እንደ አንድ ትምህርት ይሰጥ ነበር። ከሁለት አመት በፊት ያችን ትምህርትም አጥፍተዋታል። ለበአል በአማርኛ መጨፈር መዝፈን አይቻልም። በአዲሱ አመት፣ በመስቀል እኔ ራሴ ተደብድቤያለሁ።  

"የደርግ ቡችላዎች፣ የደርግ ትርፎች" እየተባልን ነው የምንደበደበው። ወደ አዲስ አበባ የመጣነው መንግስት መፍትሔ እንዲሰጠን ነው። አሁን ተሰደድንም ወከባውና ክትትሉ አልቀረልንም። ቤተሰቦቻችን እየተንገላቱ ነው። "እናንተ ናችሁ የላካችኋቸው" ተብለው እየተሰቃዩ ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር ዐብይን መደገፋችን ዋጋ አስከፍሎናል። የፌደራል መንግስት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠን እንፈልጋለን።"

(ከወልቃይት የተፈናቀለው ክንፈ ጥላሁን ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ)

No comments