Latest

የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ሂደቱን ተከትሎ እንዲፈጸም ወሰነ

የደቡብ ክልል ምክር ቤት

(ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ሂደቱን ተከትሎ እንዲፈጸም ወሰነ።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የሲዳማ ዞን ክልል ለመሆን ባቀረበው ጥያቄ ላይ በዝግ መክሯል።

በዚህም ጥያቄው ህገ መንግስታዊ ሂደቱን ተከትሎ እንዲፈጸም ውሳኔ አሳልፏል።

የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ከዚህ ቀደም የዞኑን ክልል የመሆን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መደገፉን ተከትሎ ነው ጥያቄው ለክልሉ ምክር ቤት የቀረበው።

ምክር ቤቱም በጥያቄው ላይ በጥልቅ ከመከረ በኋላ፥ የቀረበው ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ሂደቱን ተከትሎ እንዲፈጸም ውሳኔ አሳልፏል።
የደቡብ ክልል ምክር ቤት

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ አቶ መንግስቱ ሻንቃ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ በይፋ እንደቀረበለት አረጋግጠዋል።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መሰረት ክልል የመሆን ጥያቄ የሚያቀርበው ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ህዝብ በብሄር ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘት ያለበት በመሆኑ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ይህንን ክልል የመሆን ጥያቄን ባለፈው ዓመት ተቀብሎ ማፅደቁን አስታውሰዋል።


በዚህም መሰረት ህገመንግስቱ ላይ እንደሰፈረው ጥያቄው ለደቡብ ክልል ምክር ቤት መቅረብ ስላለበት በዛሬው እለት በይፋ መቅረቡን አስታውቀዋል።

ከዚህ በኋላ የሚኖረውን ሂደት በተመለከተ የክልሉ ምክር ቤት ህዝበ ውሳኔ በጠያቂው ዞን የሚካሄድበትን ጊዜ እና ሁኔታን እንደሚወስን ነው ያመለከቱት።

ክልል የመሆን ጥያቄውም በህዝበ ውሳኔው በሚገኘው ውጤት ላይ መሰረት አድርጎ ቀጣይ ሂደቶችን እንደሚያልፍ አስታውቀዋል።

በታደሰ ሺፈራው

No comments