የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምን እያደረገ ነው? አሳዬ ደርቤ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትናንት በማንነቱ ምክንያት ስራውን እንዲለቅ ያደረገውን "ካፒቴን" ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው ዛሬ ደግሞ በብቃቱ እንዲሸማቀቅ ለማድረግ ሰፊ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ ደግሞ በህግ የሚያስጠይቅ ይመስለኛል፡፡
ምክንያቱም ማንኛውም ድርጅትም ሆነ መስሪያ ቤት የሚመራባቸው እሴቶችና የመልካም አስተዳደር መርሆች አሉት፡፡ ከእነዚህ መርሆች መሃከል ደግሞ ‹‹ሚስጢር ጠባቂነትና ተጠያቂነት›› ይገኙበታል፡፡ የአየር መንገዱ ስራ አስኪያጆች ግን ይሄንን መርህ በመደርመስ... የማንነት ጥቃት አለማድረሳቸውን ለማስረዳት በካፒቴኑ ስም የተዘጋጁ ሰነዶችን ሶሻል-ሚዲያ ላይ በመዘርገፍ ተጨማሪ ጥቃት እየፈጸሙበት ይገኛሉ፡፡
ይሄም ሁኔታ በድርጅቱ ውስጥ ያሉት ሃላፊዎች ከራሳቸው ደህንነት ውጭ በሌላ ሰው ላይ ለሚደርሰው የሞራል ስብራት… ምንም አይነት ደንታ እንደሌላቸው የሚመሰክር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አየር መንገዱ የቀረበበት ዘገባ ‹የሃሰት› መሆኑን ማስረዳት ከፈለገ… ያሉትን መረጃዎች ይዞ መሄድ ያለበት ዘገባውን ወደሰራበት ሚዲያ እንጂ ወደ ሶሻል ሚዲያ አይደለም፡፡ ከዚህ አልፎ ቢከሰስ እንኳን የክሱን ሃሰተኝነት የሚያስረዱ መረጃዎችን ማቅረብ ያለበት ለሚመለከታቸው የህግ አካላት ነው፡፡
የአየር መንገዱ ስራ አስኪያጆች ግን የቀረበባቸው ወቀሳ ከሚዲያ ዘገባነት አልፎ ተጠያቂነትን ከማምጣቱ በፊት በእንጩጩነቱ ለማስቀረት በማሰብ… ከፓይለትነት ወደ አርሶ አደርነት እንዲቀየር የፈረዱበት ካፒቴን ላይ ያዘጋጇቸውን ሰነዶች መበቱንን ተያይዘውታል፡፡
ሆኖም ግን ያወጧቸው ሰነዶች ለህግና ለመርህ ተገዥ አለመሆናቸውን ከመግለጽ ባለፈ የቀረበባቸውን ትችት የሚያፈራርስ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ዮሐንስ ወደ ዩኒቨርስቲ ሲገባም ሆነ ተመርቆ ሲወጣ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ነው፡፡ ከዚህም አልፎ የአንድ ቤተሰብ አባላት በሚቀጠሩበት የአየር መንገድ ድርጅት ውስጥ ገብቶ ፓይለት መሆን የቻለው ብቃቱና ውጤቱ አግዞት እንጂ ቤተ-ዘመድ ስለነበር አይደለም፡፡
እናም አብዛኛው ሰው በማንነቱ በሚገባበት ድርጅት ውስጥ በብቃቱ የገባው ‹ካፒቴን› በእነሱ ቁና ሲሰፈር… የነበረው ብቃት ቀንሶ ከተገኘ የጥቃቱን ግዝፈት እንጂ የክሱን ሃሰተኝነት ሊገልጽ አይችልም፡፡
እነሱ አልገባቸውም እንጂ… ያደረሱበት ጥቃት እኮ ብቃቱን ብቻ ሳይሆን ጤንነቱንም አመሰቃቅሎታል፡፡
ከአውሮፕላን አውርዶ ጎጆ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ አብራሪነትን ጠልቶ አርሶ-አደርነትን አስመርጦታል፡፡
.
ስለዚህም አየር መንገዱ ራሱን ለማንጻት መፍገምገሙን ትቶ በካፒቴኑ ላይ ላደረሰው ጉዳት ተገቢውን የሞራል ካሳ መስጠትና የዚህ አይነት ጥቃት የሚፈጽሙትን ስራ አስኪያጆች ማሰናበት ግድ ይለዋል፡፡
No comments