Latest

ቅንጥብጣቢ የአስመራ እና የምፅዋ ወግ አስመራ- ከተወራላት በላይ የምታምረው ከተማ - ከሕይወት እምሻው (ክፍል ሶስት)

ቅንጥብጣቢ የአስመራ እና የምፅዋ ወግ  አስመራ- ከተወራላት በላይ የምታምረው ከተማ  (ክፍል ሶስት)

አዲስ አበባ እና አስመራ በብዙ ነገር የተለያዩ ከተሞች ይሁኑ እንጂ በተለይ የድሮዋን አዲስን ለሚያውቅ ሰው የአስመራን መልክ መገመት የሚከብድ አይመስለኝም፡፡

እስቲ ድፍን ፒያሳን አስቡ፡፡ ብሄራዊ ቲያትር አካባቢን፣ አምባሳደር፣ ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢን ጨምሩ፡፡ ሜክሲኮ የድሮውን ካምቦሎጆ ሰፈር አክሉ፡፡ አይን የሚጣጥበረብር መስታወት ያላቸውን ረጃጅም ፎቆች አንሱና ከአራት ፎቅ በማይበልጡ የድንጋይ ዝም-ያሉ ህንፃዎች ተኩ፡፡

ከዚያ መንገዶቹን ሰፋ ሰፋ አድርጉና በጣም ረጃጅምና ያልተጎሳቆሉ የዘምባባ ዛፎችን ትከሉባቸው፡፡ እነዚህ መንገዶችን ሙልጭ አድርጋችሁ ጥረጉ፡፡ መጥፎውን ሽታ አስወግዱ፡፡ የእግረኛ መንገዱን በጣም አስፉ፡፡ እዚህም እዚያም ያሉትን የግንባታ ስራዎች አጥፉ፡፡ በየቦታው የተከመረውን አሸዋና ብሎኬት አንሱ፡፡ የካፍቴሪያ ወንበሮችን ከሰፋፊ እግረኛ መንገድ ጥግ ጥግ አስቀምጡ፡፡ በጥድፊያ ወዲህ ወዲህ የሚለውን ህዝብ ቁጥር በጣም አሳንሱና ቀስ ብሎ እንዲራመድ አድረጉ፡፡

አሁን ያሰባችሁትን ቦታ በአይነ ህሊናችሁ ሳሉ....... አስመራ በአብዛኛው ይሄን ትመስላለች፡፡

እያሰቡ መሄድን (ቢያሻ ሜዲቴት እያደረጉ) የምትፈቅድ፣ ንፁህ እና ለኑሮ ምቹ ከተማ ነች፡፡ ጫጫታ የላትም፡፡ የመኪና ጥሩምባ አያንባርቅባትም፡፡ አቧራ አይበዛባትም፡፡ የመኪና ሰልፍ አያጨናንቃትም፡፡ እዚህም እዚያም የሚሰሩ አዳዲስ ግንባታዎች በጭራሽ አይታዩባትም፡፡ አብዛኛው የከተማ ክፍል በዩኔስኮ ቅርስነት ስለተመዘገበ አዲስ ግንባታ ማካሄድ ክልክል ነው፡፡

በዚህ የተነሳም አስመራ በአመዛኙ ጣሊያን ኤርትራ ለሃምሳ አመታት ተደላድሎ በተቀመጠበት ጊዜ ያነፃት ትንሽዋ ሮማን ሆና ቆይታለች፡፡ ያም ሆኖ በቅኝ ግዛት ዘመን የሃገሬው ሰውና ጣልያኖች ይኖሩባቸው የነበሩ ሰፈሮች ልዩነት ዛሬም ድረስ ጎልቶ ይታያል፡፡

ልክ እንደ አዲስአበባዎቹ ካዛንችስና ፒያሳ የህንፃዎቹ ውበት፣ የመንገዶቹ ስፋት፣ የቤቶቹ ጥበትና የፎቅ ብዛት ዛሬም ልዩነቱን ያሳብቃል፡፡ አባሻውልን (የአስመራ ጨርቆስን) አይቶ መሃል አስመራን ላየ ይሄ ልዩነት ዛሬም አፍ አውጥቶ ይናገራል፡፡

ፊልሞን ያለ እረፍት ሲያዞረኝ በአብዛኛው በእግሬ፣ በትንሹ በመኪና ያልዳሰስኩት የአስመራ ክፍል ያለ ለማለት ይከብደኛል፡፡

ከሲኒማ ኢምፔሮና ሮማ እስከ ብረት ተቀጥቅጦ ሁሉን ነገር እስከሚሆንበት መደብር፣ ከአስመራ ማዘጋጃ ቤት እስከ የ119 አመታት የእድሜ ባለፀጋው አልቤርጎ ኢታሊያና ሆቴል (በድሮ ስሙ ከረን ሆቴል)፣ በሽሮ እና አሳ ምግቡ ከሚታወቀው ቤት ምግቢ አስመራ እስከ ፋሚሊ ፒዛ ቤት፣ ከአባሻወል አስከ ኤርትራ ትልቁ ፖስታ ቤት፣ ከየአኬንሪኮ ኬክ ቤትን የሚመስለው ጆርዲኒዮስ የጥንት ኬክ ቤት (1960 የተቋቋመ) እሰከ  ዶክተር አብይ በለስ የበላበት የምፅዋ መውጫ መንገድ ድረስ አካለልኩት፡፡


ሁሉንም ላወራችሁ ስለማልችል ፣ በዚህ ሁሉ ዙረቴ የታዘብኳቸው ጥቂት ነገሮች እነዚህ ናቸው፡፡

  • (አ)ብይ በሃገሩ አይከበርም

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በአስመራ እንደ ድሮ የህንድ መሪ ፊልም ተዋናይ ነው፡፡  አሚታ ባቻን ነገር፡፡ ፎቶውን በየቦታው ማግኘት ብርቅ አይደለም፡፡ ፎቶ ቤቶች ላይ ከአዲስ ሙሽሮች በላይ አብይ አምባሻ በትሪ ሲያስይዝ የሚያሳይ ፎቶ ይገኛል፣ ፀጉር አስተካካዮች ጋር ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር ሲተቃቀፍ የሚያሳይ ፎቶ ይለጠፋል፡፡

በህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ ከቅዱሳን ስእሎች አጠገብ ፎቶውና ጥቅሶቹ ተቀምጠዋል፡፡ በሰዎቸ ስልክ ላይ ስክሪን ሴቨር ሆኖ ያገለግላል፡፡  ምስሉ ተለበዶ በመንገድ ላይ ይሸጣል፡፡

አብዛኛዎቹ ያወረራኋቸው ሰዎች ለእሱ ያላቸው ፍቅር ጥልቅና ያልበረደ ነው፡፡ ‹‹ታድላችሁ›› ይሉኛል ስለሱ ማውራት ሲጀምሩ፡፡ ‹‹እግዜር ላከላችሁ›› ይሉኛል ስለሱ አውርተው ሲያበቁ፡፡


  • ህዝቡ ቀና እና እጅግ ተባባሪ ነው

እንደገርኳችሁ አስመራን ከላይ እስከታች ሳስሳት ነው የከረምኩት፡፡ ነገር ግን አንድም ቦታ፣ አንድም ጊዜ ‹‹እዚህ መግባት አይቻልም፣ ተመለሱ፣ ዝግ ነው፣ አይፈቀድም›› አልተባልኩም፡፡ ሲኒማ ሮማን ውስጡን ለማየት ስንጠይቅ ምንም እንኳን ሰዎች ፊልም እያዩ ቢሆንም ቀስ ብለን እንድንገባ ተባብረውናል፡፡

ማዘጋጃ ቤት እስከ ቢሮዎቹ ድረስ ዘልቀን ስንገባ ‹‹የት ናችሁ…ከየት ናችሁ›› ብሎ ያዋከበን የለም፡፡ መንገድ ጠፍቶብኝ ግራ ስጋባ አማርኛ ባይቸሉ እንኳን ወይ ለሚችል ሰው ያስረከቡኝ፣ ወይ ጉዳያቸውን ትተው ራሳቸው እጄን ይዘው ያደረሱኝ ብዙ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያዊ መሆኔን ሲያውቁ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው አንድ ነው፡፡ ‹‹አስመራ እንዴት ናት?› ‹‹ቤላ ናት›› አላለሁ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ተመሳሳይ ጥያቄ ይጠይቁኛል፡፡ ‹‹ከአዲሳባ ትበልጣለች?›› ያኔ በውበትና ለኑሮ በመመቸት እንደምትበልጥ አስረግጬ እነግራቸዋለሁ፡፡ ብዙ ከኢትዮጵያ የሚመጣ ሰው አስመራ ፎቅ ስለሌለ ቅር እንደሚሰኝና ኋላ ቀር ከተማ ናት ብሎ እንደሚያስብ ይነግሩኛል፡፡


ለእኔ መዘመን ንፁህ መሆን እና ለሰው ኑሮ የሚመች ከተማ መሆን እንጂ ፎቅ መገንባት ብቻ አለመሆኑን ጨምሬ እነግራቸዋለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ሲስማሙ ሌሎቹ ደግሞ በአዲሳባ እንደሚቀኑ ይነግሩኛል፡፡ ምን ይደረጋል? ሰው የሌለውን ነው ሚመኘው፡፡

  • ሁሉም ሰው አነጣጥሮ መተኮስ ይችላል

ሁሉም ኤርትራዊ የውትድርና ስልጠና ወስዷል፡፡  ይሄንን በተለይም ከማርቲን ፐላውት ‹‹Understanding Eritrea: Africa’s Most Repressive State ›› መጽሃፍ ቀደም ብረዳም በየምግብ ቤቱ፣ በየመንገዱ፣ በየሆቴሉ፣ በየአውቶብሱ ስሳፈር ትዝ እያለኝ እገረም ነበር፡፡ ለምሳሌ በአውቶብስ እየሄድኩ አውቶብሱ ውስጥ 30 ሰው ቢኖር ከ30ዎቹ ጠመንጃ መተኮስ የማልችለው እኔ ብቻ ነኝ እያልኩ አስቤ ፈገግ እል ነበር፡፡ ነገሩ የብሄራዊ አገልግሎት ውጤት ነው፡፡

ማርቲን ፕላውት ስለዚህ ጉዳይ አጀማመር ሲያወራ እንዲህ ይላል፡፡

…እ.ኤ.አ በ1995 የኤርትራ መንግስት ብሄራዊ አገልግሎትን የሚመለከት አዋጅ አወጣ፡፡ በዚህ አዋጅ መሰረት ማናቸውም ከ18 እስከ 50 አመት ያለ ኤርትራዊ ብሄራዊ አገልግሎትን የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ በተለይ ከ18 እስከ 40 ላሉ ሰዎች ይሄ አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው፡፡

ማርቲን እንደሚለው የኤርትራ መንግስት ብሄራዊ አገልግሎትን የወጣቶችን የስራ ባህል እና ፍቅር መገንቢያ፣ የሃገር ግንባታ ብቸኛው አማራጭ ብሎ ያስቀምጠዋል፡፡

እንግዲህ ብሄራዊ አገልግሎትን የሚያስፈፅመው የመከላከያ ሚንስቴር ሲሆን አገልግሎቱን ላለመስጠት መኮብለል ወይ ደግሞ ሰበብ እየፈጠሩ ከምልመላ ራስን ለማግለል መሞከር ከባድ ቅጣት ያስከትላል፡፡ በኤርትራ ፓስፖርት ማውጣት ዛሬም እጅግ ብርቅ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ ይሄ ነው፡፡

መፅሃፉ እንደሚለው አዋጁ በወጣ ጊዜ የብሄራዊ አገልግሎት የጊዜ ገደብ 18 ወር  ሲሆን ስድስቱ ወር በሰራዊትነት ማገልገል ቀሪው 12 ወር ደግሞ መንግስት በሚመድበው ቦታ ተገኝቶ ለነጻ የሚቀርብ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡  ከዚያ ወዲህ ግን አገልግሎቱ በ18 ወር የተወሰነ ሳይሆን ላልታወቀ ጊዜ የሚቆይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከአዋጁ ጊዜ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ ብሄራዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ ብዙ ኤርትራዊያን አሉ፡፡


ሃያ አመት በላይ ማለት ነው፡፡ ከብሄራዊ አገልግሎት ቢወጡም ተጠባባቂ የሰራዊት አባል መሆን ግድ ነው፡፡ በዚህ የአገልግሎት ዘመን የኪስ ገንዘቡን በተመለከተ ግልፅ መረጃ ማግኘት ከባድ ቢሆንም በወር ከአምሰት መቶ ናቅፋ (ወደ አንድ ሺህ የኢትዮጵያ ብር) ይከፈላል የሚለው ሳያስማማ አይቀርም፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም ከመውረዱ በፊት ይሄ ግዴታ መቼ እንደሚነሳ የተጠየቀው መንግስት ኢትዮጵያ በማናቸውም ሰአት ትወረናለች የሚለው ስጋት እስካለ የመነሳት እድሉ አነስተኛ መሆኑን ተናግሮ ነበር፡፡ አሁን ይነሳ ወይ ይቀንስ ይሆን?

በነገራችን ላይ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ሴት ልጅ በኤሪቲቪ የብሄራዊ አገልግሎት እየሰጠች እንደምትገኝ ሰምቻለሁ፡፡ ከዚህ በተረፈ አንድ የኢንተርኔት ካፌም ተቀጥራ ትሰራለች ብለውኛል፡፡

  • እንጀራው!

ብዙዎቻችን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትጣላ የጤፍ ዋጋ ሰማይ እንደነካ ሰምተን ነበር፡፡ እውነት ነው፡፡ ይጋነን ይሆን አላውቅም እንጂ በአንድ ወቅት አንድ ኩንታል ጤፍ ከ6- 8ሺህ ናቅፋ ደርሶ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ በብር ስትመቱት እስከ 16 ሺህ ይሄዳል ማለት ነው፡፡

ከእርቁ ወዲህ ግን ጤፍ እንደልብ ስለሚገባ ዋጋው አሽቆልቁሎ አንድ ሺህ አምሰት መቶ ናቅፋ ደርሷል፡፡ ወደ ሶሰት ሺህ ብር ገደማ ማለት ነው፡፡ እኔን የገረመኝ ግን በአስመራ ምግብ ቤቶች ያገኘሁት እንጀራ በሙሉ በስፋቱ የአዲሰባን እንጀራ በእጥፍ የሚበልጥ (ሰፌድ ያህላል)፣ በውፍረቱ ለአነባብሮነት የሚቀርብ፣ በጣእሙ ደግሞ እጅግ የሚያሰደስት ሆኖ ማግኘቴ ነው፡፡ እንደሰማሁት ይሄ ምንም ያህል ጤፍ ቢወደድ ቀድሞም የነበረ ነገር ነው፡፡

በእርግጥ ምግብ በአስመራ ምግብ ቤቶች መመገብ እጅግ ውድ ነው፡፡ መካከለኛ ደረጃ ላይ አለ የሚባል አንድ ምግብ ቤት (ለምሳሌ አዲሰባ ላይ በፅጌ ሽሮ ደረጃ የሚመደብ) አንድ ሽሮ (ሽሮውም በጣም ብዙ ነው) በወፍራም እንጀራ በትንሹ እስከ ሁለት መቶ ብር ያስከፍላል፡፡ አሳም ከቀይ ባህር እንደማይመጣ ውድ ነው፡፡ በአጠቃላይ ንፁህ ግን ቅንጡ ያልሆነ ቤት መመገብ የሚፈልግ አንድ ሰው ለምግብ በቀን ከአምሰት መቶ ብር በላይ ሊያወጣ ይችላል፡፡

  • ሰአት እና ቀን

ኤርትራዊያን የቀን አቆጣጠራቸውን በፈረንጅኛ አድርገዋል፡፡ አሁን አመቱ 2018 ሲሆን ወሩም ጥቅምት ነው፡፡ ሰአትም የሚቆጥሩት እንደ ፈረንጅ ነው፡፡ ‹‹ነይ…ጠዋት 8 ሰአት ላይ ቁርስ እንብላ አይነት››፡፡ ሆኖም ቀኑ በአውሮፓ ዘዬ ይቆጠር እንጂ የወራቱ ስሞች ግን መስከረም፣ ጥቅምት….እየተባሉ ይቆጠራሉ፡፡  የኦርቶዶክስ ሃይማኖት በአላት እንደ መስቀል፣ ገና እና ፋሲካ እንዲሁም ቅዱስ ዮሃንስ በሰፊው ይከበራሉ፡፡  ዘመን የሚቀየረው ግን ጥር ላይ ከፈረንጆቹ ጋር ነው፡፡

  • መስቀል እና ደመራ

አስመራ መስቀል ትልቅ በአል ነው፡፡ ደመራ የሚደመረው ግን በመስቀል እለት ጠዋት ላይ ነው፡፡ የዘንድሮው በአል ተሳታፊ ለመሆን ሄጄ ነበር፡፡ መዝመሮቹ በትግርኛ ይሁኑ እንጂ ምቱ አንድ፣ አኳሃኑ እንደ እኛው ነው፡፡ ዘማሪዎች ነጫጭ ለብሰው በከበሮ ታጅበው ደመራው ወደ ተደመረበት የቀድሞው አብዮት አደባባይ የአሁኑ ሃርነት ወይም ነፃነት አደባባይ ይተማሉ፡፡

ትእይነቱ በህዝብ ቁጥር ይነስ እንጂ እንደ አዲስአበባው ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ግን ቀልቤን የሳበው አንድ ነገር ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ባንዲራ የያዙ ተሳታፊዎች፣ ዘማሪዎች እና መደበኛ ሰዎች ከኤርትራ ባንዲራ አጠገብ የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዘዋል፡፡ ይጨፍራሉ፡፡ ያውለበልባሉ፡፡ እኛ እዚህ በባንዲራ አውርድ ስቀል የሰው ሕይወት ስንቀጥፍ ከወራት በፊት በጠላትነት የምናየው ሃገር ህዝብ ከባንዲራው እኩል የእኛን ባንዲራ ሲያውለበልብ ሳይ ተገረምኩ፡፡

  • ዮፍታሄ እና ቡና በዝንጅብል

ስለ ዮፍታሄ ራሱን የቻለ ወግ መፃፍ ይገባኛል፡፡ ዮፍታሄ በእጅ ስራ የተካነ ሰው ነው፡፡ ዘናጭ ቦርሳ ከጆንያ እና ሳጠራ አሽሞንሙኖ ይሰራል፡፡ ከፖስታ ቤት አጠገብ ባለው ትንሽዬ እና የተጨናነቀች የስራ ክፍሉ ውስጥ የሚውለው ዮፍታሄ የ47 አመት ጎልማሳ ሲሆን ቁጭ ጃንሆይን ይመስላል፡፡

እጥረቱ፣ ቅጥነቱ፣ ግርማው ቁጭ ጃንሆይን፡፡ ከሰራልኝ ውብ ቦርሳ በላይ የወደድኩት ግን ጨዋታውን ነው፡፡ ለዛው! አቤት ለዛው! በዚያ ላይ ደግሞ ወደ ህይወቴ ያመጣው አዲስ ጣእም፡፡ ይህ ጣእም ቡና በዝንጅብል ነው፡፡ ወይ ሲጥም! ካላመናችሁ ሞክሩና እዩት፡፡

…እንግዲህ ከእርቁ ወዲህ ፣ አሁን አሁን በአስመራ የአዲስ አበባ እና ሌላም ታርጋ ያላቸው የኢትዮጵያ መኪኖቸን ማየት ብርቅ አይደለም፡፡ ብዙ ሰው ከኢትዮጵያ በመኪና መጥቶ ይጎበኛታል፡፡ የንግድ ሃሳብ ይነድፋል፡፡ አንዳንዱም ንግዱን ቀድሞ አጡፎታል፡፡

ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ቢራዎች፣ አምቦውሃ፣ ብዙ የታሸጉ ውሃዎች አስመራ ማግኘት ብርቅ ያልሆነው፡፡ ከዚህ የተረፈው ደግሞ ቀይባህርን ያያል፡፡ ምፅዋን ይጎበኛል፡፡ የሆነው ሆኖ ምንም እንኳን በርከታ የሃገሬ ልጆች የምፅዋን አስቸጋሪ መንገድ በቅንጡ መኪናዎች ለመሄድ ቢወስኑምእኔ ግን 42 ናቅፋ ከፍዬ በመንግስት አውቶብስ ለመሄድ ወሰንኩ፡፡ ለምን? ለእናንተው ወሬ ይዞ ለመምጣት፡፡

ጉዞ ወደ ምፅዋ በሚቀጥለው ክፍል፡፡

No comments