መስተጋብር፡- አማራጭ አይደለም ሕልውና ነው - ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
ይህ የተፈጥሮ አቅም ማጣትም ቀስ በቀስ የዝርያውን የመባዛት ዕድል እየቀነሰው ይመጣና ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ቀደምቶቻችን የቅርብ ዘመዳሞች እንዳይጋቡ የከለከሉት ይህ ችግር በሰው ዘር ላይ እንዳይከሠት በማሰብ ነው፡፡ ለዚህ ሁነኛ መፍትሔው ከሚራራቁ ወገኖች ጋር የሚመሠረት ግንኙነት ነው፡፡
በማኅበራዊ ግንኙነትም ሰው በዕውቀት፣ በአመለካከት፣ በሐሳብ፣ በመረጃ ምንጭና በአካሄድ ተመሳሳይ ከሆነ ማኅበረሰብ ጋር የሚኖር ከሆነ ውጤታማነቱ እየቀነሰ ይመጣል፡፡ የሐሳብ ኢምብሪዲንግ ይገጥመዋል፡፡ በዕውቀትና በሐሳብ ጠንካራ አይሆንም፡፡ በአመለካከትና በአካሄድ አይሰላም፡፡
አንድ ቋንቋ ብቻ እየሰማ፣ በአንድ መንገድ ብቻ እያሰበ፣ ከአንድ ምንጭ ብቻ እየሰበሰበ፣ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ እያየ ስለሚኖር የእርሱ ሐሳብ ከሌሎቹ ጋር ተወዳድሮ የማሸነፍ ዕድሉ ይጠብባል፡፡ ቀስ በቀስም እየጠፋ ይሄዳል፡፡
በግላዊ ወዳጅነትም ከተመሳሳይ ሰዎች ጋር ከተወዳጀ ሰው ይልቅ የተለያየ ዕውቀት፣ ልምድና አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር የተወዳጀ ሰው የበቃ፣ የነቃ፣ የሰላ የመላ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ነገሮችን ከየአቅጣጫው የሚያይ፣ ሁለገብ ዕውቀት ያለው፣ የአመለካከት ብዙነትን መቀበል የሚችል ሰብእና ይኖረዋል፡፡
በግላዊ ወዳጅነትም ከተመሳሳይ ሰዎች ጋር ከተወዳጀ ሰው ይልቅ የተለያየ ዕውቀት፣ ልምድና አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር የተወዳጀ ሰው የበቃ፣ የነቃ፣ የሰላ የመላ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ነገሮችን ከየአቅጣጫው የሚያይ፣ ሁለገብ ዕውቀት ያለው፣ የአመለካከት ብዙነትን መቀበል የሚችል ሰብእና ይኖረዋል፡፡
ዘረኝነትና ጎሰኝነት በሕዝብ ላይ ከሚፈጥሩት ችግሮች አንዱ ይሄ ነው፡፡ ለሌሎች ሰጥቶና እርሱም ተቀብሎ የማይኖር ማኅበረሰብ እየተዳከመ ከምድረ ገጽ መጥፋቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከሌሎች ጋር የሐሳብ፣ የባሕል፣ የዕውቀት፣ የሥጋና የደም ዝምድና እየፈጠረ የሚሄድ ማኅበረሰብ ግን እጅግ ጠንካራ ይሆናል፡፡ በዓለም ላይ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ለመሆን የቻሉት በቋንቋው ባለቤቶች ብቻ የሚነገሩና ያደጉ ቋንቋዎች አይደሉም፡፡
እንግሊዝኛ ያደገውና የሰፋው አሜሪካኖች፣ አፍሪካውያን፣ ሕንዶች፣ አውስትራልያውያን፣ ካናዳውያንና ሌሎችም ባደረጉት አስተዋጽዖ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የሀገራችን የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንኳ ያደገው ከየማኅበረሰቡ ከመጡ ሊቃውንት በወሰደው የዕውቀት ዘረመል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ከሌላው ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሊቃውንትም ለአማርኛ ዕድገት አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ አንድ ቋንቋ የሚነገረው በራሱ ሰዎች ብቻ ከሆነ እየደከመና እየጠፋ ለመሄድ ወስኗል ማለት ነው፡፡
ቋንቋ እንዲያድግ ከተፈለገ ከእርስ በርስ መገናኛነት ወጥቶ የሌሎች ማኅበረሰቦች ጭምር መገናኛ መሆን አለበት፡፡ እንግሊዝኛ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ የደረሰው የልዩ ልዩ ማኅበረሰቦችና ሊቃውንት አስተዋጽዖ ውጤት ስለሆነ ነው፡፡ ዛሬ የምንጠቀምባቸው የእንግሊዝኛ ቃላት 29% ከላቲን፣ 29% ከፈረንሳይ፣ 26% ከጀርመን፣ 6% ከግሪክ፣ 10% ከሌሎች ተወስደው ነው፡፡ ከአፍሪካ እንኳን ከ20 በላይ ቋንቋዎች ለእንግሊዝኛ ቃላትን አበርክተዋል፡፡
በቋንቋ ብቻ ሳይሆን በባሕልም እንዲሁ ነው፡፡ የምዕራባውያን ባሕል ዓለም ዐቀፍ ባሕል እስከመምሰል የደረሰው በሁለት መንገድ ነው፡፡ በመስጠትና በመቀበል፡፡ በተለያየ መንገድ የእነርሱ ባሕል የሁላችን ባሕል እንዲሆን ሠርተዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎቹም የሚፈልጉትን ያህል ወስደዋል፡፡
ዛሬ ወደ 32 በሚጠጉ ሀገሮች በታላቅ በዓልነት የሚከበረው ‹ሐለዊን› መነሻው የሴልቲኮች ባሕል ነው፡፡ የወረቀት ሥራን፣ የባሩድን ዱቄት፣ የኅትመት ሥራ፣ የአቅጣጫ መጠቆሚያ ማሽን፣ የርዕደ መሬት መለኪያን፣ ሻሂን፣ ሐርን፣ ፖርሲሊን፣ ርችትን ምዕራባውያን ከቻይና ወስደዋል፡፡
በዚህ ዘመን የድኻ ማኅበረሰቦች ከፍተኛ ፈተና የሚሆነው ሉላዊነት ነው፡፡ በመገናኛና በመረጃ ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት የምዕራቡን ዓለም አስተሳሰብ፣ ባሕልና ሥርዓት የዓለም ሥርዓት ለማድረግ በርትቶ ይሠራል፡፡ ተነጥለው የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ይህን ማዕበል ለመቋቋም አይችሉም፡፡ ማኅበረሰባዊ ኢንብሪዲንግ ይገጥማቸዋል፡፡
ያላቸው የተሻለ አማራጭ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ጠንካራ ማኅበራዊ ዘረመል መፍጠር ነው፡፡ ይህ ዘመን ተዛምደንና ተጋምደን ጠንክረን በዓለም ፊት የምንቆምበት እንጂ ታጥረን፣ ተከልለና ተነጥለን የምንተርፍበት አይደለም፡፡ ተመሳሳይ ሰዎችና ተመሳሳይ ማኅበረሰቦች የሚያደርጉት ተራክቦ የሚያመጣው ውጤት ኢምብሪዲንግ ነው፡፡ ያ ደግሞ እኛነታችን በዓለም ፊት ጸንቶና በቅቶ እንዳይቆም ማንነታችንም በታሪክ ውስጥ እንዳይቀጥል ያደርገዋል፡፡ ፍጻሜውም ከምድረ ገጽ መጥፋት ነው፡፡
ንጉሣውያን ቤተሰቦች ሥልጣናቸውን በራሳቸው ዙሪያ ለመጠበቅ ሲሉ ከሌሎች ጋር መጋባትን ይከለክሉ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ የቅርብ ዘመዳሞችን ያጋባሉ፡፡ በ19ኛውና በ20ኛው መክዘ በአውሮፓ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ዘንድ የተከሠተው በሽታ(hemophilia) በዚህ የመጣው በዚህ የዘመዳሞች ጋብቻ (consanguineous marriage) ምክንያት መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡
ለ200 ዓመታት በስፔን ገናና ሆኖ የኖረው የሐብስበርግ ሥርወ መንግሥት(Habsburg Dynasty) በኖቬምበር 1 ቀን 1700 የተጠናቀቀው በኢንብሪዲንግ የተነሣ ነው፡፡ እነዚህ ኃያላን ንጉሣውያን ቤተሰቦች በአንድ በኩል ሥልጣን ከራሳቸው እንዳይወጣ ሲሉ፣ በሌላ በኩልም ክብራቸውን ለመጠበቅ በማሰብ የቅርብ ቤተሰቦችን ሲያጋቡ ኖረዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ዝርያቸው በምድር ላይ የመቀጠሉን ዐቅም እያጣ መጥቶ የመጨረሻው ዘር ቻርልስ 2ኛ በ35 ዓመቱ በልዩ ልዩ ሕመሞች ተጠቅቶና ልጅ አልባ ሆኖ ሲሞት ከመድረክ ተሰናበቱ፡፡
ሥልጣናቸውንና ክብራቸውን የጠበቁ መስሏቸው እንደ ስፔን ንጉሣውያን ቤሰቦች ማኅበረሰቡን የሚነጥሉና በራሱ ምሕዋር ብቻ እንዲሽረከር የሚያደርጉ መሪዎች ማኅበረሰቡንም ራሳቸውንም በሂደት መጉዳታቸው የማይቀር ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ የእንግሊዝ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ከቤተሰብ ውጭ መጋባትን ለልጆቻቸው የፈቀዱት ይህንን ከምድረ ገጽ የመጥፋት መቅሰፍት ለመቋቋም ይመስላል፡፡ የአሁኗ የእንግሊዝ ንግሥት ኤልዛቤልና ባላቸው ፊልፕ ሦስተኛ አያታቸው አንድ ናቸው፡፡ ንግሥት ቪክቶርያና ልዑል አልበርት፡፡
የሥነ ምሕዳር ባለሞያዎች ‹በአንድ መስክ ላይ ልዩ ልዩ ዝርያ ያላቸው ዕጽዋት ካሉ፣ በአካባቢው ልዩ ልዩ ዓይነት ነፍሳት እንዲኖሩ ያበረታታቸዋል፡፡ ይህም የዕጽዋቱን የመራባት ዐቅም(productivity) በመጨመር አካባቢው ጤናማ ሥነ ምሕዳር እንዲኖረው ያደርጋል ይላሉ፡፡› አንድ ዓይነት የዕጽዋት ዝርያ ከተሰበሰቡበት ቦታ ይልቅ ልዩ ልዩ ዝርያ ያላቸው ዕጽዋት ያሉበት አካባቢ ዝርያዎቹ በምድር ላይ እንዲቀጥሉ ከማድረጉም በላይ አካባቢውንም ጤነኛ ያደርገዋል፡፡
በሰዎች የኑሮ ሂደትም እንዲሁ ነው፡፡ መስተጋብር ከተናጥል ኑሮ ይልቅ ማኅበረሰብን ያጠነክረዋል፡፡ በምድር ላይ ዘሩ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ከማስቻሉም በላይ ኅብራዊ የሆነና በኅብራዊነትም የሚያምን ማኅበረሰብ ከአንድ ወጥ ማኅበረሰብ ይልቅ ሰላማዊ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ተዛምዶና ተጋምዶ፤ አብሮና ተባብሮ መኖር አማራጭ አይደለም፤ ሕልውና ነው፡፡
ፍራንክፈርት፣ጀርመን
No comments