Latest

ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ከንቲባ! ግልባጭ ለጠቅላይ ሚንስቴር (ከሙሉቀን ገበየሁ )

ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ከንቲባ!

ጉዳዩ «ስለ መተንፈሻ ቦታ»


እንደምን ሰነበቱ ከንቲባ? አዲስ አበባስ እንደምን አለች? የከተማችን ነዋሪስ ሰላም ነው? በባእድ አገር ከተማ በስደት ስኖር መልካም ነገር ባየሁ ቁጥር ላገሬ ኢትዮጲያ እንዲህም ተወልጄ ላደኩባት ከተማ ቢሆንልን ብዬ የምመኘው ነገር ብዙ ነው፡፡ መቼስ ይሄ የአብዛኛው ኢትዮጲያዊ ስደተኛ ምኞት ነው፡፡ ሰው ለሚወደው መልካምን ነገር ይመኛልና፡፡

ዛሬ ግን ደፍሬ እንድ ነገር ላስቸግሮት ነው፡፡ ይህን ነገር ከእርሶ በፊት ለነበሩት ከንቲባዎች ልጠይቅ ብዬ ደብዳቤ ጽፌ ሳልከው ብዙ ግዜ ትቸዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ዞር ብለው እያዩትም፣ ደግሞም ጥያቄውን ለመመለስ ፍላጎቱም ችሎታውም የላቸውም ብዬ ነው፡፡ የነበሩበት የመንግስት ስርአት አይፈቅደምና ነው፡፡

ባለፉት 5 ወራት ግን በሃገራችን የሚታይው የለውጥ ጅምር አበራታች ሆኖ አገኘሁትና እስኪ ከንቲባውን ላስቸግር ብዬ ደፈርኩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቲር ዶ/ር አብይ አህመድ በስደት ያለነውን ወገኖች አገራችሁን እርዱ ፣መጣችሁም እዩ ብለው መልክትና ግብዣ ሲያደርጉ ብዞዎቻችን ደስ ብሎናል፡፡ ይሄንንም ደብዳቤ በዚህ ተስፋ መንፈስ የተጻፈ ነው፡፡

ደብዳቤውን በመስሪያ ቤት እድራሻዎ ልልክ ብዬ ነበር፤ ግን “የማይረባ ደብዳቤ” ብለው ረዳቶቾ እንዳይጥሉት ስጋት ገባኝ ፡፡ ባደባባይ ግልጽ ደብዳቤ መጻፉን መረጥኩ፡፡ ግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ማድረጌ እርዳታ ካስፈለገ እንዲያውቁት ነው እንጂ ማሳበቄ አይደለም፡፡

አይዞት ስጋት አይግባዎት። መሬት፣ ቢሮ ወይም የመኖርያ ቤት ወይም የንግድ ቦታ ይሰጠኝ ብዬ አይደለም የምጠይቆዎት፡፡ ለእንደሱ እይነት ጥያቄ በድሮው ስርአት መሰረት (የኔ ነገር ……ድሮ መባል ተጀመረ እንዴ) ባደባባይ ሳይሆን፡ ዘመድ አዝማድ ወዳጅ ተፈልጎ ፡ ገንዘብ ተይዞ ነው ደጅ የሚጠናው፡፡ የኔ ጥያቄ ግን ሌላ ነው፡፡

አዲስ አበባ የኢትዮጲያ ዋና ከተማችን፣ የአገራችን የኢኮኖሚ እምብርት፣ የሁሉ ጎሳና ቋንቋ ተናጋሪ መኖሪያና እንጀራ መቁርሻ፣ የንጉሶቻችን መቀመጫ እንዲሁም የአፍሪካ የፖለቲካ መዲና ናት። እንደ ስሟ አበባ ባትሆንም እንድ አፈጣጠሯና እንድ ልጅነትዋ ግን ልጆቹዋ አበባ ሊያደርግውት የምትችል ከተማ ናት። 


ነዋሪዎችዋ እስክዛሬ ድርስ በቀጥታ ግለሰብ ከንቲባ ለመምርጥ ያልታደሉባት ነገር ግን የአገራችን ገዥውች ሁሉ የሚስይሙላት ምስኪን ግን ተስፋ ያላት ከተማ ናት። የታሪካዊቷ ኢትዮጲያና የአፍሪካ መዲና ፣ ክ 3-4 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት ከተማ እንድመሆኗ መጠን ነዋሪዎችዋ በቀጥታ ግለሰብ ከንቲባ የመምርጥ እድል ያስፈልጋቸው ነበር፤ አሁንም ወደፊትም ያስፈልጋቸውል።  

ለጨዋታው ያህል ይህን አልኩ እንጂ ልጠይቆት ያስብኩት ጉዳይስ ይሄ አይደለም። ነገር ግን በአዲስ አበባ ዋና ከተማችን ለመጀመርያ ግዜ ተግባራዊ እንዲያደርጉት የምጠይቆትን ጉዳይ እንደ ከንቲባነትዎ ለመማጸን ነው።

ፈረንጅ አገር በተለይም ለንደን ከተማ ውስጥ አንድ መልካም ነገር አስትዋልኩ። ለነገሩ ይሄ ነገር በአውስትራሊያ፣ካናዳ ፣እንዶኒዥያ፤ጣልያን፣ ሆላንድና ሲንጋፖር፣ትሪንዳድ ና ቶባጎ እንዲሁም ታይላንድ ያለ ነገር ነው። በ አሜሪካን አገርም በክሊቭ ላንድ፣ ካሊፎርኒያ እንዲሁም ዋሽንግተን ለተወሰነ ገዜ የነበር ሲሆን ባሁን ግዜ ይኑር አይኑር ግን እርግጠኛ አይደልሁም::

ከሁሉ አስቀድሞ ግን የሆነው በለንደን ከተማ ነው። “መተነፈሻ ቦታ” ብየዋለሁ። የአገሩ ሰው Speaker Corner ብሎ ይጠራዋል። እ አ አ በ1850 ና 60’ች በነበሩ የህዝብ ብሶት፣ ሰልፍና ጥያቄ መሰርት ኋላ ላይ በህግ የተፈቀደ ነገር ነው። እሁድ ቀን መገበያየት አይቻልም የሚል ህግ ወጣና እሁድ ለት ብቻ እረፈት የነበርቸው ምስኪን ሰራተኞች የሚገበያዩቡት ቀን በመከልከሉ ይህን ብሶታቸውን በለንደን ከተማ ሃይድ ፓርክ (Hyde Park) በሚባል መናፈሻ ቦታ የተስባስቡብትና ብሶታቸውን ያሰሙበት ቦታ ነው። 

ከግዜ በኋላ በህግ እውቅና አግኝቶ ሰው ሁሉ ያሻውን፤ የአንጀቱን፤ በሆዱ የቋጠረውን የሚተነፍስበት፤ ጎብዝ ወጣቶች አዲስ ሃሳባቸውን የሚገልጹበት፣ አንዳንዶች ሃይማኖታቸውን የሚስተዋውቁበት፣ የሃገር ውስጥ ወይም የውጭ አገር ፖለቲካ፣ በደል ፣ጦርነት፣ግጥሞች ፣ፍልስፍና በሰለማዊ መንገድ በሃሳብ የሚከራክሩበት፣ የሚወያዩበት፤ ምንም ፍቃድ ከመንግስት ወይም ከባለስልጣን የማይጠየቅበት በኔ አጠራር “የመተንፈሻ ቦታ” Speaker corner መስርተዋል።

በዚህ ቦታ ላለፉት 140 አምታት በላይ ማንኛውም ሰው ስድብ አይቀላቀልበት እንጂ ያሻውን የሚናግርበት ፣የሚተነፍስበት፣ ለሌሎች የሚያሰማበት ቦታ ነው። አሁንም በየሳምንቱ እሁድ እሁድ ከ ጥዋቱ 2 እስክ 11 ሰአት ድርስ በዚህ ስፍራ ማንኛውም ሰው ያሻውን የሚዶስክርበት ቦታ ነው። ከንቲባው ግጭትና ወንጀል እንድይፈጠር የተወሰኑ ህግ አስከባሪ ፖሊሶችን ያሰማራል እንጂ ሁሉ ነገር በሰላም ሃሳብ የሚንሽራሽርብት ቦታ ነው።

እንግሊዞች እንዲህ ያለ ነገር መፍቀዳቸው ማሀብረሰባቸውን በሃሳብ እንድይገደብ፣በነጻ እንዲናግር፣ ሌላውም እንዲያደምጥ የተለያየ ሃሳቦች በሰላማዊ መንገድ የሚንጸባርቁበት ባህል ፈጥርዋል። እኛም አገር አሁን የተጀመርው ለውጥን ለማገዝና ዜጎቻችን ሃሳባቸውን ያለገድብ (ስድብ ና የጉልበት እርግጫን ሳይጨምር) የሚግልጹበት መድርክ ቢፈቀድ ለዲሞክራሳያዊ ግንባታና የተለያየ ሃሳብን በስላማዊ መንገድ ለማንሸራሸር ባህል ለመፈጠር እጅጉን ይጠቅማል።

እርግጥ ነው አሁን ሬድዮ፣ ቴሌቭዥን እንዲሁም ጋዜጣ መጽሄት ተፈቅዷል። ይህን የሚጠቀመው ግን እጅግ አንስተኛ የህበረተሰብ ከፍል ሲሆን የነዚህ የህዝብ መገናኛ (ሚዲያ) ባለቤቶችን ፍላጎት የሚያንጸባርቁ (ወይም የማይቃወሙ) ሃሳብ ነው እንጂ የአብዛኛውን ህዝብ፣ የምስኪኑን፣ የደሃውን ህዝብ የሆዱን መተንፍሻ ወይም ሃሳብ ማቅርቢያ መደረክ አይሆኑም።

እኔ እንድ ሃሳብ የማቀርበው አዲስ አበባችን እንዲህ ያለ የዜጎችን “መተነፈሻ ቦታ” ሊኖራት ይገባታል። ከንቲባው ለዚህ መልካም ሃሳብ ስራ ላይ ማዋል ሀላፊነት ይኖርባቸዋል። ለህዝባችንም ላገራችንም ይጠቅማልና። ሰው አምላኩ የሰጠውን የመናገር መብቱን ያለማንም ፈቃድ በሃላፊነት መግለጽ እንዲችል መድርክ/ቦታ ያሸዋል።

ለምሳሌ መሃል አዲስ አበባ ከጥቁር አንብሳ ሆስፒታል ፊትለፊት የሚገኘው “የትግላችን” ሃውልት መናፋሻ ውስጥ ቢፈቀድና በሳምንት አንድ ቀን ፡ እሁድ ለት ከ2 እስክ 11 ሳት ድርስ ማንኛውም ተናጋሪ ሰው የሚቆምበትን ከፍ ብሎ ሰው ሊያየው ሊሰማው የሚስችለው መቀመጫ ወይም መቆሚያ ላይ ሆኖ የልቡን እንዲናገር መፍቀድ መልካም ነገር ነው። 

ሌሎችም ይህን ለመስማት፣ለመከራከር፤አዲስ ሃሳብ ለማቅርብ በሰላማዊ መንገድ የሚቻልበት መድርክ ይሆናል። ታድያ ለሁሉም ተሳታፊ (ተናጋሪም አድማጭም) ዋና መስማሚያ ህግ ደንብ የሚሆነው ስድብ ና ድብድብን ወይም የጉልበት ጸብ የማይፈቀድ መሆኑንን ተናጋሪውም አድማጩም እንዲስማማበት የሚገልጽ ማስታዋቂያ ማድርገና በቦታው ወንጀል እንዳይፈጸም የተወሰኑ የአዲስ አበባ ከተማ ሀግ አስከባሪ ፖሊሶች ጥበቃ እንዲያደርግ ማድርግ ነው። ቦታውን እንድ ምስሌ ጠቀስኩ እንጂ ከንቲባው የተሻለ ቦታ፣ መሃል የሆነ፣ ለሁሉ የሚያመች ለትርንስፖርት የሚደርስበት ቦታ ሊመርጡ ይቻላል።

እንድዚህ ያለ መድርክ ለአገራችንና ለሚገነባው ዲሚክራሲያዊ ባህል እጅግ ጠቃሚ ነው። በተዋቂው የለንደን Speaker corner በአለም ገናና የነበሩ ሰውች በዚያ መድርክ አዳዲስ ሃሳባቸውን ገልጸውበታል፤የተከራከሩበትም ቦታ ነበር ነውም። 

እነ ካርል ማርክስ፤ ሌኒን ፣ጆርጅ ኦርዊል፣ማርክስ ጋርቬ፣ የጋናው ክውሚ ንክሩማን የመሳሰሉትን ሁሉ ይጭመራል። አዲስ አበባችን ይህን ነገር ብትፈቅድ የመጀመርያዋ የአፍሪካ ከተማ በመሆን ወደፊት ለአገራችንና ለአፍሪካ እንዲሁም ለአለም አዲስ ሃሳብ የሚያቀርቡ ዜጎች ሃሳብ ማሰሚያ መዲና ትሆናለች።

ማንኛውም ዚጋ የመንግስትን መመሪያ ወይም ህግ ወይም ድርጊት የሚከራከርበት፣ የሚሞግትበት እንዲሁም አዲስ ሃሳብ የሚያቀርበበት ቦታ ይሆናል። ማንም ዜጋ መናገር እስከቻለ ድርስ በደሉን የሚገልጥበት፣ ሌብነትን፣ አድሎን የሚያጋልጥባት፣ ያሻውን የሚተነፍስበት ቦታ መሆን ይችላል። ይህ የመናገር ነጻነትን ከሀገ- መንግስቱ ወርቀት ላይ ብቻ የቀረውን የዜጎች መብታቸውን በተግባር መጠቀሚያ ማድርጊያ መድርክ ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ላአገራችን የሚበጅ ሃሳብ አምጡ ብለው ጠይቅወናለና እኔም በፈረንጅ አገር ያየሁትን ለሃገራችን ዲሞክራሲይዋ ባህል እድግት የሚርዳን ሃሳብ በዚህ ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ከንቲባ አቀርባለሁ። ወደፊት ለንደን ከተማን ወይም ሌሎች ከላይ የጠቀስኳቸው አገሮችን በስራ ወይም በግል ጉብኝት ሲሄዱ Speaker Corner ሂደው ይመልከቱ። እንዚህ ቦታዎች በብዛት በቱሪስቶች የሚጎበኙ ቦታዎች ናቸው።

ይህን በአደባባይ ያቀረብኩሎትን ሃሳብ እንዳልስማ ሰው ቢተኙበት ግን አንድ ቀን እኔም ሆነ በሃሳቡ የሚስማሙ ወገኖች የምንጠይቆትና የምንወቅስቦት ጉዳይ ይሆናል። ሃሳቡን በተግባር ለማዋል አንዳንድ አስፍላጊ ጥናትና እርዳታዎች የሚያስፈልጉ ከሆነ ግን ለመርዳት ፈቃድኞች ነን።

አዲስ አበባን እንዲሁም ነዋሪውን ህዝብ አክብረው፣ ታዛዥ ሆነው፣ መልካም ስራ ለመስራት እንዲችሉ መልካም ምኞቴን እየገለጽኩ፤ አንድ ቀን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንድሌሎች ታላላቅ የአለማችን ከተማ ነዋሪዎች የራሷን ግለሰብ ከንቲባ የመምርጥ ቀን በህግና በተግባር እንዲመጣ እመኛልሁ።

ደህና ይስንብቱ።

No comments