Latest

የ2018 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዎች ዴኒስ ሙክዌጄ እና ናዲያ ሙራድ ሆኑ - ቢቢሲ

የ2018 የኖቤል የሰላም ሽልማት

ዴኒስ ሙክዌጄ እና ናዲያ ሙራድ የ2018 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል። አሸናፊዎቹ በግጭትና ጦርነት ቀጠናዎች ወሲባዊ ጥቃት እንደ መሳሪያ እንዳይውል ባደረጉት ጥረት መረጣቸው ታውቋል።

ኮንጓዊው ዶክተር ዴኒስ ሙክዌጄ የማህፀን ሀኪም ሲሆኑ የወሲብ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሴቶች ህክምና በመስጠት አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ግዛት በተፈፀመ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ከ50 ሺህ በላይ ሴቶችን አክመዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ኢራቃዊቷ ናዲያ ሙራድ ከአራት ዓመታት በፊት በእስላማዊ ታጣቂ ቡድን ታግታ የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ የሆነች ወጣት ስትሆን ይህንንም ለመታገል ያላሰለሰ ትግል ስታደርግ እንደነበር ተገልጿል።

ምርጫውን የተከናወነው 5 አባላት ባሉት ኮሚቴ 331 ዕጩዎች ለሽልማቱ ቀርበው ነበር ። ከእነዚህም መካከል 216 ግለሰቦች ሲሆኑ 115ቱ ደግሞ ቡድኖች መሆናቸውን ኮሚቴው ጠቁሟል። በኖቤል ሽልማት አሰራር መሰረት ዕጩዎች ለህዝብ ይፋ የሚደረጉት ከ50 ዓመታት በኋላ ነው።

የሁለቱ ኮሪያ መሪዎች የአሸናፊነቱ ቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው ግለሰቦች መካከል ይገኙበታል። የሰሜን ኮሪያው መሪ በሰብዓዊ መብት አያያዘቸው በተደጋጋሚ ቢወቀሱም ከደቡብ ኮሪያው አቻቸው ጋር በመሆን በሁለቱ ሃገራት መካከል የቆየውን ውጥረት ለማርገብ የወሰዷቸው እርምጃዎች የሽልማቱ ተመራጭ ያደርጋቸዋል የሚሉት በርካቶች ነበሩ።

ሌላው ሽልማቱን ሊያሸንፉ ይችላሉ ተብለው ቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው መሪዎች መካከል እንዱ ዶናልድ ትራምፕ ናቸው። ትራምፕ በኮሪያ ባህረሰላጤ ሰላም ለማስፈን እንዲሁም ሰሜን ኮሪያ ኒኩለር ቦንም ከማበልጸግ እንድተቆጠብ ላደረጉ ያላሰለሰ ጥረት ሽልማቱን ሊያሸንፉ ይችላሉ ተብሏል።

አጭር የምስል መግለጫ - በእስር ላይ የሚገኘው ጸሃፊው ራኢፍ ባዳዊ፣ ሊቀ ጳጳስ ፈራንሲስ እና የካታሎንያ የነጻነት መሪ ካርለስ ፑይግዴሞንት ሽልማቱን ያሸንፋሉ ተብሎ ግምት ከተሰጣቸው መካከል ይገኙበታል።
የዘንድሮውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሸንፋሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው ሌሎች ግለሰቦች መካከል እስር ላይ የሚገኘው ጸሃፊው ራኢፍ ባዳዊ፣ ሊቀ ጳጳስ ፈራንሲስ እና የካታሎንያ የነጻነት መሪ ካርለስ ፑይግዴሞንት ይገኙበታል።

የሳውዲ ዜግነት ያለው ጸሃፊው ራኢፍ ባዳዊ ፣ ''የመገናኛ አውታሮችን በመጠቀም እስልምናን ዘልፏል'' በሚል ክስ ላለፉት 6 ዓመታት በሳውዲ እስር ቤት ውስጥ ይገኛል።

በስፔን መንግሥት ሕጋዊ እውቅና ባልነበረው ሕዝበ ውሳኔ ካታላኖች በካርለስ ፑይግዴሞንት እየተመሩ ከስፔን ተገንጥለው ሃገር ለመመስረት ሙከራ አድርገው ነበር። ሕዝበ ውሳኔውን ተከትሎም ካርለስ ከስፔን ሸሽተው በቤልጅም እየኖሩ ይገኛሉ።

ከግለሰቦቹ በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ሽልማቱን ሊያሸንፍ ይችላል ከተባሉ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድስ ከዕጩዎቹ መካከል እንዱ ሊሆኑ አይችሉም?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘት ብቻም ሳይሆን የኖቤል ሽልማት እንዲያገኙም ጭምር ዘመቻ ተከፍቶ ነበር።

ይሁን እንጂ የኖቤልን የሰላም ሽልማትን የጊዜ ሰሌዳ ስንመለከት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የ2018 የኖቤል ሽልማት እጩ የመሆናቸው ነገርን አጠያያቂ ያደርገዋል።

የኖቤል ኮሚቴ የጊዜ ሰሌዳ እንደሚከተለው ነው።


መስከረም፡- በፈረንጆች መስከረም (ሴፕቴምበር) የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ እጩዎችን ለመቀበል ይሰናዳል። እጩ የመቀበሉ ሥራ ለቀጣይ ስድስት ወራት ይጸናል። እጮዎቹን መጠቆም የሚችሉት ከላይ የተዘረዘሩት ብቁ ጠቋሚ የተባሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ብቻ ናቸው።

የካቲት፡- በየካቲት የእጩዎች መቀበያ ጊዜ ያበቃል። ከየካቲት 1 በፊት ያልተጠቆመ በዚያ ዓመት እጩ መሆን አይችልም።

መጋቢት፡-ኮሚቴው የእጮዎችን ዝርዝር ያቀርባል። ከእጮዎቹ ውስጥ ከ20 እስከ 30 የሚሆኑትን ብቻ ለተጨማሪ ማጣሪያ ይቀርባሉ።

ጥቅምት፦ በጥቅምት መጀመርያ ኮሚቴው አሸናፊውን በድምጽ ብልጫ ይመርጣል። ይግባኝ የማይባልበት ምርጫ ነው ታዲያ።

በታኀሳስ፦ 10 (በፈረንጆቹ) በኦስሎ ኖርዌይ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ይካሄዳል።

የኖቤል ሽልማት ከአንድ ዓመት ዘለግ ያለ ጊዜን የሚወስድ ሂደት ነው። ኾኖም ጥቆማ የመቀበያ ጊዜ ከፈረንጆች መስከረም ጀምሮ ለ6 ወራት የሚዘልቅ ነው። ይህ እንግዲህ መጪውን የመስከረም ወር ሳይሆን የ2017ቱን ወር አንድ ብሎ የሚጀምር ነው።

የእጩ መስኮቱ ከተዘጋ ከሁለት ወራት በኋላ ወደ ሥልጣን የመጡት ዐብይ አሕመድ ቢያንስ የ2018 የኖቤል ሽልማት እጩ የመሆናቸው ዐድል ጠባብ ያደርገዋል። ምናልባት የኖቤል ኮሚቴው በመጨረሻዎቹ ጊዜያት እጩ የመጨመር ሥልጣን ስላለው ያ ተግባራዊ ከሆነ ጠባብ እጩ የመሆን እድል ሊኖራቸው ይችላል።

No comments