Latest

የአባይ ግድብ ግንባታ የተንጓተተው በሜቴክ አቅመ ቢስነት መሆኑ ተገለጸ - ቢቢኤን

የአባይ ግድብ ግንባታ

የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን-ሜቴክ፤ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ ቶሎ እንዳይጠናቀቅ ወይም ግንባታው እንዲዘገይ ማድረጉ ተገለጸ፡፡  


በግድቡ ግንባታ ላይ በተለያዩ ስራዎች ሲሳተፍ የቆየው ሜቴክ፤ ከተሰጡት ስራዎች ውስጥ አንዱንም በአግባቡ አለማጠናቀቁ ተነግሯል፡፡ 

ሜቴክ ‹‹የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የኃይድሮ መካኒካል ስራዎች እንዲሁም ከጀርመንና ፈረንሳይ ኩባንያዎች የሚገዙ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን እንዲገጥም ውል ተሰጥቶት እንደነበር፡፡›› የኮርፖሬሽኑ የኮሜርሻልና ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድ አስታውሰዋል፡፡

‹‹ከዚህ ባለፈም፤ ግድቡ ከሚኖሩት 16 ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሶስቱን አምርቶ እንዲገጥም ስራ ተሰጥቶት በሀገር ውስጥ የሚያመርትበትን ድርጅት ከፍቶ ነበር፡፡›› ያሉት ኃላፊው፤ ሆኖም ከተሰጡት ስራዎች አንዱንም አጠናቅቆ አለማስረከቡን ተናግረዋል፡፡  

ሜቴክ ለተጠቀሱት ስራዎች እንዲከፈለው የጠየቀው ገንዘብ 25 ቢሊዬን ብር ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 16 ቢሊዬን ብሩን አስቀድሞ ወስዷል፡፡ 

ድርጅቱ ስራውን በተዋዋለው ቀነ ደገብ መሰረት አለማጠናቀቁን ተከትሎ፤ ስራው ለጀርመን ኩባንያ በጨረታ መሰጠቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ሜቴክም ከዚህ በኋላ በግድቡ ግንባታ ላይ የሚኖረው ተሳትፎ በጥቃቅን ስራዎች የተገደበ ይሆናል ተብሏል፡፡

ሜቴክ፤ የኃይድሮ መካኒካል ስራዎች፣ ከጀርመንና ፈረንሳይ ኩባንያዎች የሚገዙ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን እንዲገጥም እንዲሁም ግድቡ ከሚኖሩት 16 ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሶስቱን አምርቶ ለመግጠም የተዋዋለው 25 ቢሊዬን ብር ነበር፡፡  

ሜቴክ ስራውን ማንጓተቱን ተከትሎ ስራውን ለሌሎች ኩባንያዎች ለመስጠት በወጣው ጨረታ ትልቅ የዋጋ ልዩነት መኖሩ ተነግሯል፡፡ 

የሜቴክን ስራ የተረከበው የጀርመን ኩባንያ የተጫረተበት ገንዘብ፤ ሜቴክ ከተዋዋለው ያነሰ ሲሆን፤ ‹‹የዛሬ ሁለት ሳምንት የጨረታው ሰነድ ሲከፈት ከእያንዳንዱ ተርባይን የ5 ነጥብ 9 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ቅናሽ ተገኝቷል፡፡›› ብለዋል አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ፡፡ ጨረታውን ያሸነው ቮይስ የተባለው የጀርመን ኩባንያ መሆኑም ተናግረዋል፡፡

የጀርመኑ ኩባንያ ከዚህ ቀደም ከኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ውስጥ ስምንቱን እንዳቀረበ፣ አሁን ደግሞ ሶስቱ እንደተጨመሩለት የተገለጸ ሲሆን፤ አሊስቶን የተባለው የፈረንሳይ ኩባንያ ደግሞ አምስቱን ተርባይኖች ለማቅረብ ውል ተፈራርሟል ተብሏል፡፡  

እንደ አባይ ግድብ ላሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልጉ ተርባይኖች በዓለም ላይ በጣት በሚቆጠሩ ኩባንያዎች ብቻ የሚመረቱ ቢሆኑም፤ ሜቴክ ግን ተርባይኖቹን በሀገር ውስጥ አመርታለሁ በሚል የያዘው አቋም ለግድቡ ግንባታ መንጓተት መንስኤ ሆኗል ተብሏል፡፡ 

ስራውን ለመስራት ያቀረበው ገንዘብም ከዓለም ዓቀፍ ኩባንያዎች ጋር ሲወዳደር፤ ዋጋው በእጅጉ ውድ መሆኑን ለመመልከት ተችሏል፡፡

No comments