Latest

የአዲስ አፈ ጉባኤ ምርጫ በነገው ዕለት ይካሄዳል



የአዲስ አፈ ጉባኤ ምርጫ በነገው ዕለት ይካሄዳል

(ቢቢኤን ራዲዮ) - በወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ቦታ አዲስ አፈ ጉባኤ ለመተካት በነገው ዕለት ምርጫ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡  


የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ያዋቀሩትን አዲስ ካቢኔ ተከትሎ ከቦታቸው እንዲነሱ መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ 

ከአፈ ጉባኤነታቸው ተነስተው የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው በተሾሙት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ቦታ ሌላ ሹም ለመተካት ሲባል ነገ ሐሙስ ጥቅምት 8 ቀን 2011 በፓርላማ ምርጫ ይካሄዳል ተብሏል፡፡

በነገው ዕለት በሚኖረው የፓርላማ ስነ ስርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሚገኙ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾሙ ቀደም ሲል ባቀረቡት የመንግስት አቅጣጫዎች ላይ በመንተራስ የመንግስታቸውን አቋም እንደሚያሳውቁ ተነግሯል፡፡  

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤት የጋራ የመክፈቻ ስብሰባ ወቅት የተገኙት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፤ በዕለቱ የመንግስትን የ2011 የትኩረት አቅጣጫ በተመለከተ ሰፊ ንግግር አድርገው እንደነበር ይታወቃል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው፤ መንግስት በዚህ ዓመት የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎችን ለማድረግ፣ የፖለቲካውን ምህዳር ለማስፋት፣ በቀጣዩ ዓመት በሚደረገው ብሔራዊ ምርጫ ዙሪያ የተለያዩ ስራዎችን ከወዲሁ ለመከወን እንዳሰበ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በሰፊው ለመንቀሳቀስ ማቀዱን ይፋ አድርገው ነበር፡፡  

ፓርላማው በነገው ዕለት በሚኖረው ስብሰባ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፤ በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ በመንተራስ፤ የመንግስታቸው የ2011 አቅጣጫ ምን እንደሆነ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሏል፡፡

ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከፓርላማው አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ዝርዝር ምላሽ የሚሰጡ ሲሆን፤ በመጨረሻም ምክር ቤቱ የአባላቱን ጥያቄ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቡትን የመንግስት አቋም ካዳመጠ በኋላ የድጋፍ ሞሽኑን ያጸድቃል ተብሎ ተጠብቋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚሰጡት ማብራሪያ ጎን ለጎን፤ ምክር ቤቱን በቀጣይነት የሚመራውን ሰው ለመምረጥ ምርጫ የሚካሄድ ሲሆን፤ በዕለቱም አዲሱ አፈ ጉባኤ ማን እንደሆነ እንደሚታወቅ ታውቋል፡፡ 

ቀጣዩን አፈ ጉባኤ ለመምረጥ በሚካሄደው ምርጫ የተለያዩ ዕጩዎች መመልመላቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

No comments