Latest

ነገረ ሸገር (በመስከረም አበራ)

ነገረ ሸገር (በመስከረም አበራ)

በኦነግ የሚመሩት የአዲስ አበባ ባለቤትነት ይገባኛል ባይ የፖለቲካ ሃይሎች ባለቤትነትታቸውን ለማስረገጥ የሚያቀርቡት ማስረጃ የሚመዘዘው ከታሪክ እና ከህገ-መንግስቱ አንቀፅ ነው፡፡


እነዚህ ወገኖች ታሪክን የሚጠቅሱት ጥያቄያችንን እውነተኛ ያደርግልናል ብለው ከሚያስቡበት የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡ህገ-መንግስቱንም ቢሆን የሚያነቡት ልባቸውን በሞላው የባለቤትነት መንፈስ ስለሆነ ክርክራቸው ህገ-መንግስቱን ራሱን የሚጣላ ነው፡፡

ታሪክን ከወገቡ ጎምዶ፣ህገ-መንግስታዊ አንቀጾችን “ለራስ ለመቁረስ” በሚመስል መንገድ እየተረዱ መሄዱ ብዙ አዋጭ አይደለም፡፡ታሪክ ከወገቡ ሳይሆን ከስሩ ሲታይ ሸገር ንብረትነቷ የማን መሆን እንዳለበት ከአመት በፊት በሰፊው አስነብቤ ስለነበር ዛሬ ወደዛ ሰፊ ሃተታ አልገባም፡፡በዚህ ፅሁፍ መዳሰስ የፈለግኩት የሸገር ጉዳይ ማወዛገቡ እንዲቀጥል ያደረጉ ምክንያቶችን እና ሌሎች በጥያቄው ዙሪያ ያሉ መገለጥ ያለባቸውን ሃሳቦች ነው፡፡

አዲስ አበባ የኔ ነች የሚለው ኦነግ ይህ ጥያቄው ምክንያታዊ እና ተገቢ ቢሆን ኖሮ ለጥያቄው የማያዳግም መልስ የሚያገኘው በ1983 ከህወሃት ጋር በፍቅር በከነፈበት ዘመን ነበር፡፡ በዛ ዘመን ህወሃት ኦነግን ለማባባል ያልፈነቀለው ድንጋይ እንዳልነበር አቶ መለስ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለምልልስ መግለፃቸውን “World Peace Foundation” የሚባል የጥናት ድርጅት Augest 20,2018 ላይ ባወጣው መጣጥፍ ላይ ተገልጧል፡፡  


መስከረም አበራ
አቶ መለስ በአንደበታቸው ያሉትን ለመግለፅ ያህል እንጅ እንደ ሃገራችን አቆጣጠር በ1980ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ኦነግ የሃገራችንን እጣ ፋንታ ከሚዘውሩ ዋነኛ የፖለቲካ ሃይሎች አንዱ እንደ ነበረ፣ህወሃትም መቀመጫውን እስኪያስተካክል ይለማመጠው እንደነበረ ግልፅ ነው፡፡

ኦነግ እንዲህ ባለው አድራጊ ፈጣሪነት ላይ በተሳተፈበት፣ህወሃትም እጅግ ሲያባብለው በነበረበት ዘመን አጥብቆ የሚፈልጋትን አዲስ አበባን በተመለከተ ማድረግ የቻለው ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የሚኖራትን ጥቅም በተመለከተ በህገ-መንግስት ላይ ማስፈርን ብቻ ነው፡፡ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ጋር ባለው ጉርብትና ምክንያት በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ልዩ ጥቅም ይኖረዋል ማለት ባለቤት ነው ማለት አይደለም፡፡ ይህ ነገር ሲፃፍ ኦነግ እዛው ቤተ-መንግስቱ አካባቢ ባለሟል ነበር፡፡

ህገመ-ንግስቱ ከላይ ወደታች በህዝብላይ የተጫነ እንጅ በትክክል የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ የተሳተፈበት ባለመሆኑ ኦነግ ከቅርበቱ የተነሳ “ልዩ ጥቅም” የሚለውን ዛሬ በሚለው “የአዲስ አበባ ባለቤት ኦሮሚያ ነው፤ መኖርግን ለሁሉም የተፈቀደ ነው” በሚለው ማስቀየር ያልሆነለት ለምንድን ነው? ሲባል ይህ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ነች ሌላው ህዝብ የሚችለው ዝምብሎ መኖር ነው የሚለው ጥያቄ ለሌላው ሰው ቀርቶ ለወንበሩ ሲል ሁሉን ሸጦ ለማረፍ በማያመነታው ህወሃት ዘንድ እንኳን ተቀባይነት በማጣቱ ነው፡፡ጥያቄው ለምን ተቀባይነት አጣ ለሚለው መልስ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ጥቄው ተገቢ ካለመሆኑ ባሻገር ተጨባጭም ስላልሆነ ነው፡፡

“አዲስ አበባ ባለቤትነቷ የኦሮሚያ ሆኖ ሌላው ሰውም ግን መኖር ይችላል” የሚለው ሃሳብ ጭብጥ አልቦ፣ለተፈፃሚነትም አስቸጋሪ፣ከህገ-መንግስቱም ጋር የማይጣጣም ነው፡፡የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሶስቱም የመንግስት ክንፎቹ የሚያስተዳድረው ውስን ግዛት ያለው አካል ነው፡፡ ይህ አካል በህገ-መንግስቱ የተሰጠው መብት ኦሮሚያ የሚባለውን ግዛት የማስተዳደር መብት ብቻ ነው እንጅ “በአቅራቢያህ ባለው ግዛት ላይ ሁሉ ጌታ ነህ” አልተባለም፡፡

በዚህ ምክንያት በክልሉ የማይኖሩ ኦሮሞዎች በስፋት የሰፈሩባቸውን ግዛቶች እንኳን ማስተዳደር አይችልምና ነው የኦሮሚያ ዞን የሚባለው የከሚሴ ልዩ ዞን በአማራ ክልል ስር የሚተዳደረው፡፡ በአንፃሩ ኦነግ የኦሮሚያ ንብረት ነች የሚላት ሸገር በግዛቷ የሰፈሩ አንድ ወጥ ቋንቋ የማይናገሩ ህዝቦች ራሳቸውን በሚመስል፣ስብጥርነታቸውን በሚወክል መንገድ ያቋቋሙት የራሳቸው መስተዳደር አላቸው፡፡

እንዴት/በምን የሚገለፅ ባለቤትነት?
እንዲህ ባለ ነባራዊ ፖለቲካዊ ቅርፅ ኦነግ እና ሌሎች የኦሮሞ ብሄረኞች የሚሉት ኦሮሚያ የአዲስ አበባ ባለቤት መሆኗ የሚገለጠው እንዴት ነው?ባለቤትነት ከሚገለፅበት ነገር አንዱ ማስተዳደር ነው፡፡አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት ሆኖ ሌላው ዝም ብሎ ይኑር ከተባለ አዲስ አበባ ፓርላማዋ ፈርሶ፣መስተዳድሯ ታጥፎ በጨፌ ኦሮሚያ ስር ትተዳደራለች ማለት ነው፡፡ይህ ደግሞ በህገ-መንግስቱ ከተቀመጠው ጋር ይጋጫል፡፡

ህገመንግስቱ አዲስ አበባ ራሷን እንደምታስተዳድር ቁልጭ አድርጎ አስቀምጧል፡፡ታዲያ የኦሮሚያን የአዲስ አበባ ባለቤትነት ማጣቀሻው የህግ ማዕቀፍ ከወዴት ነው?ሃገሩ የሕግ ሃገር ቢሆን ኖሮ ለኦሮሚያም ለራሷ ለአዲስ አበባም ለራሷ እንዴት እንደሚተዳደሩ ያስቀመጠን ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ጥሶ አዲስ አበባ የኔ ነች ማለት በህግ የሚያስጠይቅ ነገር ነበር፡፡ ወይስ በአስተዳደራዊ፣ፖለቲካዊ እና ህጋዊ ማዕቀፍ የማይገለፅ በስነ-ልቦና ብቻ የኔ ነው ለማለት የሚያስችል የባለቤትነት ፅንሰ-ሃሳብ አለ?

የህግ ማህበረሰብ የምንሆንበት ጊዜ ገና ስለሆነ የህጋዊነቱን ነገር ለጊዜው እናቆየውና አምስቱ የኦሮሞ ፓርቲዎች ስሜታቸው እንዳቀበላቸው ያሉትን ተቀብለን ብንሄድ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ሆና ሌላውም ሰው ግን መኖር ይችላል የሚለው ነገር ተግባራዊነቱ እንዴት እንደሚሆን ተናጋሪዎቹ ራሳቸው አውቀውት በተጨባጭ አመክንዮ ለሚያስብ ሌላ ዜጋ የሚያስረዱት ነገር አይመስለኝም፡፡

የራሱ መስተዳድር ያለው ህዝብ ሌላ ባለቤት እንዳለበት እያሰበ የሚኖረው እንዴት ነው? በተባለው መሰረት ቦረና የሚኖር አንድ አርሶ አደር ቦሌ ተወልዶ ካደገ የአዲስ አበባ ነዋሪ ይልቅ የአዲስ አበባ ባለቤት ነው ማለት ነው፡፡የቦሌው ነዋሪ የአዲስ አበባ ባለቤት ለሆነው የቦረና ወይ የባሌ ኦሮሞ ስለባለቤትነቱ የሚሰዋለት ነገር ምንድን ነው? ምናልባት የቦረናው አርሶ አደር ቦሌ መኖር ያማረው ቀን ቦሌን ለቆ መድረሻውን መፈለግ ወይስ እርሱ ያልመረጠው ከባሌ የመጣ ኦሮሞ አስተዳዳሪህ ነው ሲባል ዝም ብሎ መቀበል?ይህን ነገር ራስን በራስ ከማስተዳደር ዲሞክራሲያዊ መብት ጋር እንዴት ማጣጣም ይቻላል?

በመንግስት ደረጃ ስናየው የነገሩ ጭብጥ አልቦነት ይብሳል፡፡ኦሮሚያ የአዲስ አበባ ባለቤት ከሆነች አዲስ አበባ መስተዳድር ህልውና ምን ይሰራል?ወይስ የአዲስ አበባ መስተዳድርም አዲስ አበባ ላይ መኖር ይችላል የአዲስ አበባ ባለቤት ግን ጬፌ ኦሮሚያ ነው ሊባል ነው?ይሄ ራሱ ትርጉሙ ምንድን ነው? 

ጨፌ ኦሮሚያ በትርፍ ጊዜው የሸገርን ነገር ሊያይ ሊቀመጥ ነው?አዲስ አበባ ሰው ሳይጠፋ ህግ ተጠረማምሶ ከንቲባ ከአጎራባች ሚጢጢ ከተማ መምጣቱ የዚህ ምልክት ይሆን? ይሄ የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ እንዳያስተዳድር የሚያደርግ ትልቅ የመብት ጥሰት ነው፡፡ በእሳት ላይ ቤንዚን ላለመጨመር ተብሎ ዝም ስለተባለ ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡

መሰረታዊው ችግር

ከስሜት ወጥተን ነባራዊ ሃቆችን ያገናዘበ ነገር ስናነሳ በሃገራችን ህገ-መንግስት ድንጋጌ መሰረት ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በአንድ ክልል ውስጥ ያድራሉ፤ ኦሮሚያ ክልልም ኦሮምኛ የሚናገሩ ህዝቦችን በአንድ ሸክፎ ያስተዳድራል፡፡ሸገር ደግሞ አንድ ቋንቋ አትናገርምና በቋንቋ በተከለለ ክልል ውስጥ መከለል አልቻለችም፡፡በመሆኑም ኦሮሚያ ቢያጎራብታትም፣ ቢከባትም፣ ቢዞራትም ኦሮሚያ በሚለው ክልል ውስጥ ልትካለል አልቻልችም፤አትችልምም፡፡ህገ-መንግስቱ ያስቀመጠውም ይህንኑ ነው፡፡

አዲስ አበባ ከህገ-መንግስታዊም ሆነ ከነባራዊ ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሃቆች ባፈነገጠ ሁኔታ ራሷን እንዳታስተዳድር ጭራሽ የእንቶኔ ነች የእከሌ ነች ወደሚለው ንጥቂያ የገባችው ለምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ሸገርን ለንትርክ ምን ዳረጋት? ሲባል የነገሩ ስር መሰረት የውክልና አልቦነት ችግር ነው፡፡

1. በገዥው ፓርቲ ውስጥ ውክልና አልቦነት

በኢትዮጵያ ነባራዊ ፖለቲካ ፓርቲ መንግስትን ይመራል፡፡ ይህ ማለት ኢህአዴግ መንግስትን ይመራል ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ የአራት ድርጅቶች ጥምረት ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በየሁለት አመቱ አንዴ፣እንዳስፈላጊነቱ በሚደረግ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባላት ስብሰባ በሚወስኑት ውሳኔ ሃገር ይመራል፡፡

እነዚህን አራት ፓርቲዎች የሚወክሉ አባላት ጎሳቸውን ወክለው ነው ውሳኔውን የሚያሳልፉት፡፡ጎሳ አልቦዋ ሸገር በዚህ ውስጥ ውክልና የላትም፡፡ ይህ ማለት ግን የሸገር ጉዳይ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ አይነሳም ማለት አይደለም፡፡ ሲነሳ የሚነሳው ግን ኦሮሚያን፣አማራን ወይም ደቡብን አለያም ትግራይ ክልልን ወክለው በመጡ፣በዋናነት ሸገር ለእናት ክልላቸው መጠቀሚያነት እንዴት እንደምትመቻች በሚያሰሉ ሰዎች እንጅ የሸገርን ጉዳይ ለራሷጥቅም እና እድገት ሲሉ በሚያነሱ ሰዎች አይደለም፡፡

ታከለ ዑማ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚነት ወንበር ቁጭ ብሎ ስለሸገር ሲያወራ ሸገር እንዴት የኦሮሚያ ንብረት ትሆናለች የሚለውን ነገር ተመርኩዞ ነው፡፡የቦሌ ወጣቶችን ሰበሰብኩ ብሎ ከነማን ጋር ስብሰባ እንደተቀመጠ ግልፅ ነው፡፡ አርከበ እቁባይ ከንቲባ እያለ የአዲስ አበባን መሬት ለማን እንዴት አድርጎ እንዳደለ የሚታወቅ ነው፡፡እንዲህ ባለው ጉባኤ የሚነሳው ነገር ሸገር የኔ ነች የኔ ነች በሚል ጥቅመኝነት እና ዘረኝነት ተባብረው በተጫኑት ዝንባሌ እንጅ አዲስ አበባ ከተማ ራሷን በማስተዳደሯ የምታገኘውን ጥቅም ለማስረገጥ ሊሆን አይችልም፡፡

2. ህገ-መንግስታዊ ክፍተት

የኢትዮጵያን ህዝቦች በጎሳቸው መትሮ ክልል ያደለው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ሸገርን ራሷን ታስተዳድራለች ቢልም ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግስት እንደሆነ በመደንገግ ከሞላ ጎደል ለፌደራሉ መንግስት ክርን አመቻችቶ ትቷታል፡፡ 

በምርጫ 1997 ማግስት አቶ መለስ የገቢ ምንጮቿን ሁሉ በአንድ ጀንበር በፌደራሉ ክልል ስር አዙረው ያሸነፋቸውን ፓርቲ ቅንጅትን ከተማዋን ለመረከብም ለመተውም እንዳይወስን ግራ ያጋቡት ይህንኑ ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ነበር፡፡ሰውየው ከዚህ አለፍ ብለው በቅንጅት ስም የተመረጡ የከተማዋን አስተዳዳሪዎች እንደ ቁም እስረኛ እንዲቆጣጠሩ የሚያስችል መመሪያ ሁሉ ሊያወጡ እንደ ከጀላቸው ኤርሚያስ ለገሰ “ባለቤትአልባ ከተማ” ባለው መፅሃፉ አስቀምጦታል፡፡

የክልሎችን በጄት በሚወስነው የፌደሬሽን ምክርቤት ውስጥ ሸገር ህገ-መንግስታዊ ውክልና የላትም፡፡በዚሁ ምክርቤት ባለመወከሏ ከአጎራባች ክልሎች ጋር የሚኖራትን ውዝግብ በህገ-መንግስታዊ ማእቀፍ ለመፍታት ድምጿን ማሰማት አትችልም፡፡በአንፃሩ ለኔ ትገባለች የሚለው ኦሮሚያ ክልል በፌደሬሽን ምክርቤት ውስጥ ሰፋ ያለ ወንበር አለው፡፡

አንዳንዴ በፌደሬሽን ምክርቤት የተወከሉትስ ምን ተጠቀሙ የሚል ሃሳብ እሰማለሁ፡፡ይሄ የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ ለውጥ ኖረም አልኖረም ካልተወከለ አካል ይልቅ የተወከለ አካል ድምፁን ማሰማት ይችላል፡፡የወልቃይትን ጉዳይ የሚከታተሉ ቡድኖች አማራ ክልል ከትግራይ ክልል ጋር ያለውን ጉዳይ አስመልክቶ አቤቱታቸውን ያሰሙት ውክልናው ስላለ ነው፡፡አቤቱታን ሰምቶ በተገቢው መንገድ የመመለስ አለመመለስ ነገር የመልካም አስተዳደር እጦት ጉዳይ ሆኖ ሳለ ከነአካቴው አለመወከል ላመጣው ችግር መፅናኛ ሊሆን አይችልም፡፡

ሌላው ህገ-መንግስታዊ ክፍተት ሃገሪቱ የብሄር ብሄርሰቦች ናት የሚለው ነው፡፡ ሃገሪቱን ለብሄር ብሄረሰቦች የሰጠው ህገ-መንግስት የአዲስ አበባን ህዝብ “ነዋሪ” ይለዋል፡፡ለብሄር ብሄረሰቦች በባለቤትነትን የተሰጠችው ሃገር ከዚህ የተለየ ማንነት ያላቸው ግን ደግሞ ኢትዮጵያ ሃገራቸው የሆነች ሰዎች(ከሁለት ብሄር የተወለዱ፣ራሳቸውን በብሄር የማይገልፁ…) የሃገራቸው ባለቤት የሚሆኑበትን መንገድ ጥርት ባለ መንገድ መግለጽ ነበረበት፡፡ይህ ክፍተት ነው ለአዲስ አበባ ትልቅ ፈተና የደቀነው፡፡

ወደ መፍትሄው ስንመጣ እነዚህን እና ሌሎችን ክፍተቶችን ባገናዘበ መልኩ ህገ-መንግስታዊ መሻሻል መደረግ አለበት፡፡ህገ-መንግስቱ እንዲነካ አንፈልግም የሚሉ አካላት ይህን እርምጃ እንዳይደረግ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡አሁን ሃገራችን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እንዲህ ያለ ንትርክ ውስጥ መግባት አስቸጋሪ ስለሚሆን ለአጭር ጊዜ መፍትሄ የሚሆነው አሁን በስራ ላይ ያለውን ህገ-መንግስት አክብሮ መንቀሳቀሱ ነው፡፡

አሁን ያለው ህገመንግስት ደግሞ አዲስ አበባ በጥብቅ የፌደራል ቁጥጥር ውስጥ እንዳለች ቢደነግግም ከተማዋን ለማንኛውም ክልላዊ መንግስት በንብረትነት አልሰጠም፡፡ስለዚህ ከከተማዋ መጠሪያ ጀምሮ ህገመንግስቱ ካስቀመጠው ውጭ የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት ይባስ ብሎም ይህንኑ መግለጫ አድርጎ ማንበብ ኢ-ህገመንግስታዊ ህነው፡፡

ህገ-መንግስቱ መቀየር የለበትም የሚል አካል እሱው ራሱ ህገ-መንግስታዊ ድጋፍ ሌለው ሁኔታ ስሜትን ብቻ ተመርኩዞ ያዩትን ሁሉ የኔነው ማለት ትርፉ ትዝብት ላይ መውደቅ ብቻ ነው፡፡

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

No comments