ጦላይ የሚገኙ የአዲስ አበባ ወጣቶች በሳምንቱ መጨረሻ እንደሚለቀቁ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ - ቢቢሲ
ወጣቶቹ የተያዙት "በጎዳና ላይ ንብረት ሲያወድሙና ሁከት ሲፈጥሩ ነው" ያሉት ኮሚሽነሩ መጀመሪያ ከተያዙት ተጣርቶ አሁን በማሰልጠኛ ያሉት 1174 እንደሆኑ ገልፀዋል።
እሳቸው እንደሚሉት የፈፀሙት ተግባር በህግ የሚያስጠይቃቸው ቢሆንም መታነፅ እንዳለባቸው በማመን ለዚህም ከቤተሰብና ከማህበረሰብ ቀጥሎ ሃላፊነት ያለበት መንግሥት በመሆኑ ይህን ተግባሩን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
"ማነፅ ብቻ ሳይሆን የወጣቶቹን ማንነት በመገንዘብ ሥራ የሌለው ሥራ እንዲሰራ፣ ተማሪውም ትምህርቱን እንዲቀጥል ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ነው። እነዚህ ልጆች ላይ ሥራ እየሰራን ያለነው" ብለዋል ኮሚሽነሩ።
ይህን ለማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የሚመለከታቸው ትብብር ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ፖሊሶች ወጣቶችን በቡድን ሲደበድቡ የሚያሳይ ቪዲዮ ስለመለቀቁ የተጠየቁት ኮሚሽነሩ፤ ምንም እንኳ እሳቸው ተንቀሳቃሽ ምስሉን ባይመለከቱትም ቦታው ተገልፆ ትክክለኛ መረጃ ከደረሳቸው ማጣራት ተደርጎ ድርጊቱን በፈፀሙት አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀዋል።
በጅምላ ተይዘው ወደ ጦላይ ከተወሰዱ ወጣቶች መካከለ መሳለሚያ ሞቢል አካባቢ ለግንቦት ሰባት መሪዎች አቀባበል ሲደረግ ሰንደቅ አላማ በመስቀልና ባነሮችን በመለጠፍ ተሳትፎ የነበረ ወጣት አንዱ ነው።
ያሳደጉትና የክርስትና ልጃቸው በአመፅ ሳይሆን የግንቦት ሰባት መሪዎች አቀባበል ላይ ባደረገው ተሳትፎ ከዚያም የቡራዮውን ግድያ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣቱ መታሰሩን አቶ ዘመነ ሞላ ለቢቢሲ ይገልፃሉ።
ከዚህ ውጭ ልጃቸው ሰላማዊ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ያሳደጉት ልጃቸው ወጣት ፍስሃ ደምስ የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን እናቱ እንደሌለችና የሚኖረው ከአቅመ ደካማ አያቱ ጋር እንደነበር አቶ ዘመነ ይናገራሉ።
እሳቸው እንደገለፁት የታሰረው ወደ ቤቱ የሚወስድ መንገድ ላይ አመሻሽ ላይ ነው። መጀመሪያ ወደ ተወሰደበት ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ሲጠይቁ ጦላይ መወሰዱን መስማታቸውንና ከዚያ በኋላ ያለ ምንም መረጃ ቤተሰብ ስቃይ ላይ እንዳለ ይገልፃሉ።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ጅምላ እስር የመገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ ሚዲያ ርእሰ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። በማህበራዊ ሚዲያው የአዲስ አበባ ወጣቶች ይፈቱ የሚል ዘመቻም በመካሄድ ላይ ነው።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የአዲስ አበባ ወጣቶችን በጅምላ አስሮ ስልጠና ማስገባት የህግ አግባብነት እንደሌለው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የህግ ባለሙያና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆነችው ሶሊያና ሽመልስ መንግሥት እነዚህን ወታደሮች አስሮ ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በመላኩ የጣሳቸው ህጎች አሉ ትላለች።
"ተግባሩ በትንሹ አራት የሕገ መንግሥቱን አንቀፆች ይጥሳል። የታሰሩ ሰዎች መብት፣ የተከሰሱ ሰዎች መብት ፣ የተጠረጠሩ ሰዎች መብትና ከዚያም ጋር ተያይዞ መደረግ የሚገባቸው ነገሮች በትንሹ አንድ አራት የሕገ መንግሥቱ አንቀፆች ተጥሰዋል። የወንጀል ሥነ ሥርዓት ህጉንም ብንመለከት እዚያ ላይም የተጣሱ ነገሮች አሉ" ትላለች።
እሷ እንደምትለው በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ መንግሥት ሰዎችን ሰብስቦ ካሰረ ያሰረበትን ምክንያት ፍርድ ቤት አቅርቦ ፍቃድ መጠየቅ ይኖርበታል። በወሰደው እርምጃ የቀማው የግለሰቦችን ነፃነት በመሆኑ ይህን ደግሞ ያለ ፍርድ ቤት ፍቃድ ማድረግ አይቻልም።
ስለዚህም ግለሰቦቹን ፍርድ ቤት አለማቅረብ፣ የተከሰሱበትን ምክንያት አለማወቃቸውን እንዲሁም የዋስትና መብታቸውን መነፈጋቸው በሃይማኖትና በዘመድ መጎብኘት አለመቻላቸውን የመሰሉ ነገሮች ሲታዩ በእርምጃው ብዙ የመብት ጥሰቶች እንዳሉ ታስረዳለች።
No comments