Latest

በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የተፈጸመው የጅምላ እስር እና ግዞት አግባብነት የሌለው ነው

በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የተፈጸመው የጅምላ እስር እና ግዞት አግባብነት የሌለው ነው

(ECADF ኢዲቶሪያል) - በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የተፈጸመው የጅምላ እስር እና ግዞት በማንኛውም መመዘኛ አግባብነት የሌለውና የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው።

የአዲስ አበባ ወጣቶች በቡራዩ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ከተሞች ብሄርን መሰረት ያደረገ አሰቃቂ ጭፍጨፋን ተቃውመው አደባባይ መውጣታቸውን ተከትሎ ወታደሮች በከፈቱባቸው ተኩስ ተገድለዋል። 


ይህም አልበቃ ብሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች “ቦዘኔ” የሚል ስም ተለጥፎባቸው ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በጅምላ ታፍሰው በወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖች ታጉረው ይገኛሉ።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የብሄር ጥላቻን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በአደባባይ ፎቶ እየተነሱና ቪዲዮ እየቀረጹ ሲፈጽሙ የነበሩ ቡድኖች ላይ ከፍተኛ ትእግስት እያሳየ ያለው የጠ/ሚ አብይ አህመድ አስተዳደር እንዲህ አይነቶቹን ጥቃቶች ለማውገዝ አደባባይ በወጡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የፈጸመው የጅምላ አፈሳ እና ግዞት ያለፈውን የህወሃት ዘረኛ አገዛዝ የሚያስታውሰን ሆኗል።

ጥፋት የፈጸሙ እና ወንጀል የሰሩ ወጣቶች እንደማንኛውም ዜጋ ፍርድ ቤት ቀርበው፣ ጠበቃ አቁመው ተከራክረው፣ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ናቸው ብሎ ሲፈርድባቸው ብቻ ነው ሊታሰሩ የሚገባው።

በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የተፈጸመው የጅምላ አፈሳ እና ግዞት ነገ በሌሎች ዜጎች ላይ እነደማይፈጸም ምንም አይነት መተማመኛ ይለም።

ድርጊቱ ጠ/ሚ አብይ አህመድ በተለያዩ መድረኮች ካደረጓቸው ንግግሮች ጋርም በእጅጉ የሚጣረስ ነው።

በመሆኑም የጠ/ሚ አብይ አህመድ አስተዳደር በግፍ ታፍሰው በወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖች ውስጥ የሚገኙትን የአዲስ አበባ ወጣቶች በአስቸኳይ መፍታት እና ለድርጊቱም ሃላፊነት ወስዶ ይቅርታ መጠየቅ አለበት ብለን እናምናለን።

No comments