ኢትዮጵ ለቀጠናው ሰላም እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ቀዳሚ አድርጓታል- ጠቅላይ ሚ/ጽ/ቤት
አዲስ አበባ ህዳር 12፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ሀላፊ ቢል ለኔ ስዩም ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ለማስከበር እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ቀዳሚ እንዳደረጋት ገለጹ።
ሃላፊዋ ዛሬ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
ሀገሪቱ ተቋማትን በመገንባት እና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ምጣኔ ሃብታዊ ውህደት እውን ለማድረግ በወሰደቻቸው የማሻሻያ እርምጃዎች በአህጉር ብሎም አዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽህኖ ፈጣሪነት ደረጃ ላይ መድረሷን ተናግረዋል።
ባለፉት ጥቂት ወራት የተደረጉ ጥልቅ ማሻሻያዎችና በሂደት ላይ ያለው ጅምር እንቅስቃሴ ታይቶ የማይታወቅ ድጋፍ ከሁልም የዓለም አቀፍ ክፍል ከማስገኘቱም ባሻገር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ቦታ ከፍ እንዳደደረገው ነው የገለጹት።
ሀላፊዋ አያይዘውም በዚህ ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ሁሉንም የተፎካካሪ ፓርቲዎች ያሳተፈ እንደነበርም አንስተዋል።
በውይይቱ ላይ ከውጭ ሀገራት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ትጥቅ ፈተው የገቡ ፓርቲዎች መታደማቸውንም ተናግረዋል።
ውይይቱ በሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር የሚያስችል ነው ያሉት ሃላፊዋ አሁን ላይ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥ የሚያጠናክር መሆኑን አመላክተዋል።
ተመሳሳይ ውይይት ከዚህ በኋላም በምርጫ ቦርድ በኩል በቀጣይነት የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ወደ ተሻላ መቀናጀት ለማምራት ያስችላል ብለዋል።
ባለፉት ወራት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተቋማት አደረጃጀትን ከማጠናከር ባለፈ በመንግስት በኩል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አንስተዋል።
የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ በኩል መንግስት የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።
መንግስት ስርዓትን በማጠናከር እስከታችኛው አደረጃጀት ማውረድ እንዳለበት ያነሱት ሃላፊዋ፥ ሁሉም ማህበረሰብ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
መንግስት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በመተማመንና በመደጋገፍ የተሟላ መረጃ ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
ለዚህም ጽህፈትቤቱ በቀጣይነት በጋራ አብረው የሚሰሩ 50 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር የመገናኛ ብዙሃንን መለየቱንም ነው የተናገሩት።
ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር ሚዲያዎች በኮረስፖንዳንትነት ከተለዩት የመገናኛ ብዙሃን መካከል ህትመት፣ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተካትውበታል።
የህትመት ሚዲያዎች ቢያንስ 5 ሺህ ቅጅ የሚያሰራጩ እና ለአንድ አመት ያህል በተከታታይ ስራ ላይ የቆዩ ወይም የህትመት ስርጭታቸው 8 ሺህ ኮፒ የሆኑት መካተታቸውን ጠቁመዋል።
ይሁን እንጅ ወደ ፊት ሌሎች ሚዲያዎችም እየተገመገሙ አሁን ላይ ከተለዩት የሚዲያ ተቋማት ጋር ተካተው የሚሰሩበት አግባብ እንደሚኖርም ጠቁመዋል።
No comments