Latest

"ማንነትን የመለሰ ፌዴራሊዝም ስህተቱን የሚያርምበት አቀበት ላይ መላ ሊያጣ አይገባም" - ጥናት

"ማንነትን የመለሰ ፌዴራሊዝም ስህተቱን የሚያርምበት አቀበት ላይ መላ ሊያጣ አይገባም" - ጥናት

  • ‹‹ሕገ መንግሥቱ የወልቃይት እና የራያን ጥያቄ መመለስ ያልቻለው ሕዝቦቹ በየት እንደሚተዳደሩ ቅድሚያ ስላልተጠየቁ ነው፡፡››
  • ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ-መንግሥት ተጻፈ እንጂ አልተተገበረም፡፡›› የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር
  • ‹‹አሁን የወልቃይት ጥያቄ የማንነት እና የመሬት ይገባኛል ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲ እና ችግሩን የሚፈታ ሕገ መንግሥት ጭምር ነው›› ዶክተር ሶኛ ጆን
  • ‹‹ማንነትን የመለሰ ፌዴራሊዝም ስህተቱን የሚያርምበት አቀበት ላይ መላ ሊያጣ አይገባም፡፡›› ጥናት
ባሕር ዳር፡ጥቅምት 16/2011 ዓ.ም(አብመድ) የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህሩ ቻላቸው ታረቀኝ ‹‹ሕገ መንግሥቱ የወልቃይት እና የራያን ጥያቄ መመለስ ያልቻለው ሕዝቦቹ በየት እንደሚተዳደሩ ቅድሚያ ስላልተጠየቁ ነው፡፡ አንቀፅ 46 የግዛት ወሰን ላይ ቋንቋ፣ አሰፋፈር እና የሰዎች ይሁንታ ይላል፡፡

ነገር ግን በ1984 ክልሎች ‹አንድ፣ ሁለት …› ተብለው ሲለዩ የተካለሉበት በ1987 ሕገ-መንግሥቱ ሲፀድቅ ያለ ሕዝብ ይሁንታ በዚያው ቀጥሏል›› ብለዋል፡፡ ይህም አሁን ላሉት ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄዎች በር መክፈቱንም ጠቁመዋል፡፡


መምህር ቻላቸው ‹‹የሕዝቦች ፍላጎት ቀሰበቀስ ሲቀሰቀስ በዛ ልክ የተሰፈረው ሕገ-መንግሥት መመለስ የሚችልበት አቋም ላይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ-መንግሥት ተጻፈ እንጂ አልተተገበረም፤ የፖለቲካ ወገንተኝነት እና ጥገኛ ተቋማት እንደአሸን ነበሩ፡፡  

አሁንም ችግሩን ለመፍታት በሕገ-መንግሥቱ ታሪካዊ ማንነት ሊካተት ይገባል›› በማለት መፍትሔ ያሉትን ሐሳብም ምሁሩ ሰንዝረዋል፡፡ የግዛት ወሰን ችግሮች ሲኖሩም መፍትሔውን ጥያቄ ለሚነሳበት ክልል መንግሥት ከመስጠት ይልቅ የፌዴራል መንግሥት የሚወስንበት አሠራር ቢኖር እንደሚሻልም ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስ እና የዓለምዓቀፍ ጥናት ትምህርት ክፍል ተመራማሪው ዶክተር ሶኛ ጆን ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እና የወልቃይት ጥያቄ ሆድና ጀርባ ናቸው›› የሚል ሐሳብ አንስተዋል፡፡ ‹‹የዜጎች ጥያቄ እና የሕገ መንግሥቱ ዝምታ ከጊዜ ወደጊዜ አሳሳቢ ነው፡፡  

የወልቃይት ነዋሪዎች አንቀፅ 39 ባለው መብት እና አንቀፅ 46 ባስቀመጠው መሠረት ‹ቋንቋችን፣ ማንነታችን እና ባሕላችን አማራ ሁኖ ሳለ በሌላ ክልል እንተዳደራለን› የሚል ቅሬታ አላቸው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ በቀጥታ እኛን ያላማከለ ውሳኔ በማሳለፉ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እና እስር እየተዳረግን ነው›› ማለታቸውን ጥናታቸውን ዋቢ አድርገው ዶክተር ጆን ገልጸዋል፡፡ 

‹‹አሁን የወልቃይት ጥያቄ ‹የማንነት እና የመሬት ይገባኛል› ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲ እና ችግሩን የሚፈታ ሕገ-መንግሥት ጭምር ነው›› ብለዋል ዶክተር ሶኛ ጆን፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ጥናት አቅራቢ መምህር ቢንያም መኮንን ደግሞ ‹‹በብሔር ላይ የተመሠረተው ፌዴራሊዝም የሕዝቡን ምጣኔ ሀብታዊ ፍላጎት የመመለስ ፈተና ላይ ወድቋል፡፡  

ማንነትን የመለሰ ፌዴራሊዝም ስህተቱን የሚያርምበት አቀበት ላይ መላ ሊያጣ አይገባም፡፡ የግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሠረተ፣ ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነትን ሊያሻሽል የሚችል ሥርዓት መፍጠር መፍትሔ ነው፡፡ ከማንነት ባሻገር ደግሞ የጋራ እሴቶችና ጥቅሞች ላይ መረባረብ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡

ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን የጥናትና ምርምር ዓውደ ጥናት በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ዘጠኝ ምርምሮች ቀርበውበት ተጠናቋል፡፡

ዘጋቢ፡-ግርማ ተጫነ

No comments