Latest

መላኩ ፈንታን ጨምሮ ያልተጠበቁ ግለሰቦች ለአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዕጩ ሆነው ቀረቡ - ቢቢሲ አማርኛ

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)

መላኩ ፈንታ እና ጀነራል አሳምነው ፅጌን ጨምሮ ያልተጠበቁ ግለሰቦች ለ
አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።

አዴፓ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ እያካሄደ ይገኛል። 75 ግለሰቦች ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 65ቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው የሚመረጡ ይሆናል።

ለጉባኤው ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል 

  • ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ 
  • የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ 
  • የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባዋ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ 
  • የቀድሞ የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን ኃላፊ አቶ መላኩ ፈንታ፣ 
  • ጀነራል አሳምነው ፅጌ፣ 
  • የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ 
  • የብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ 
  • በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ስዩም መስፍን እና 
  • የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሥራ ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ እናታለም መለሰ ይገኙበታል።
ከድርጅቱ ነባር አመራሮች መካከል አቶ ከበደ ጫኔ፣ አቶ መኮንን ወሰንየለህ፣ ወ/ሮ ፍሬህይወት አያሌው፣ ወ/ሮ ብስራት ጋሻው ጠና፣ አቶ ጌታቸው አምባዬ፣ ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ፣ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ከድርጅቱ እንዲሰናበቱ ተወስኗል።

በሌላ በኩል የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) የቀድሞውን ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ 23 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱን አሰናብቷል።

በሀዋሳ ከተማ እያተካሄደ ባለው ጉባኤ ከተሰናበቱት ነባር አመራሮች መካከል አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ ሲራጅ ፈጌሳ፣ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና መኩሪያ ኃይሌ ይገኙበታል።

ማእከላዊ ኮሚቴ እስከ 10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ በእግድ እንዲቆዩ አድርጓቸው የነበረውን አቶ ሳሙኤል ደምሴ፣ ከሰተብርሃን አድማሱ (ዶ/ር) እና ወ/ሮ አማረች ኤርሚያስን ከድርጅቱ አሰናብቷል።

ከባለፈው ረቡዕ ጀምሮ በመቀሌ ሲካሄድ የቆየው 13ኛ የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት)ድርጅታዊ ጉባኤም ዛሬ ተጠናቋል።

ሕወሓት ዶ/ር ደብረፅዮንና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ሊቀ-መንበርና ምክትል ሊቀ-መንበር አድርጎ መርጧል።

ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም እና አዲስዓለም ቤለማ (ዶ/ር) ጨምሮ 11 አባላትን ለኢህአዴግና ለሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች አባላትን መርጧል።

ነገር ግን ከአስራ አንዱ ሥራ አስፈጻሚዎች ሁሉም ነባር የድርጅቱ ታጋዮች ሲሆኑ አንድም አዲስና ወጣት አባል አለማካተታቸው ታውቋል።

ሕወሓት ቀደም ሲል የነበረውን የድርጅቱን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቁጥርን ከ45 ወደ 55 ያሰደገ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 15 የሚሆኑት ወጣትና አዳዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ናቸው።

የድርጅቱ ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ባደረጉት ንግግር ጉባኤው ዴሞክራሲያዊ ትግል የተደረገበት እና ታሪካዊ ነበር ብለዋል።

No comments