Latest

በክልላዊና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የመከረው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ተጠናቀቀ

 የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ

(ኤፍ ቢ ሲ) የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሶስት ቀናት ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ አጠናቀቀ።

ማዕከላዊ ኮሚቴው ለጣቢያችን በላከው መግለጫ በሃገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ የተወያየ ሲሆን፥ በቀጣይ የልማት፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስራዎችን ትርጉም ባለው መንገድ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል።

በክልሉ ልማትን፣ መልካም አስተዳደር እና ዴሞክራሲን በማረጋገጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ አልመው በምሁራን የቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች የደረሱበትን ደረጃና የህዝቡን ሁለንተናዊ ፍላጎት በሚያሟላ መንገድ በተግባር መፈጸም የሚቻልበትን አቅጣጫም አስቀምጧል።

የኢትዮ ኤርትራን የሰላም ሂደት በመደገፍ፣ በህገ መንግስታዊና ፌደራላዊ ስርዓት ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን በማውገዝ፣ በክልሉ በተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች ህዝቡ ያሳየውን ፅናት በማድነቅ፥ አሁንም ህዝቡ ለክልሉ ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ለህገ መንግስታዊና ፌደራላዊ ስርዓት መከበር ዘብ እንዲቆም ጥሪውን አቅርቧል።

አሁን ላይ ባለው የትግል ደረጃ ከሁሉም በላይ የአመራር፣ የአባላትና የህዝብ አንድነት አስፈላጊ መሆኑን ያነሳው ማዕከላዊ ኮሚቴው፥ ከዚህ አንጻርም በተቃራኒው የሚፈጸሙ እንቅስቃሴዎችን በፅናት እንዲታገሉም ነው ጥሪ ያቀረበው።

ከሁሉም በላይ የድርጅቱን ተቋማዊ አንድነት በማጠናከርም ለህዝቡ ሰላም፣ ልማትና አንድነት ዋስትና በመሆን አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም በመግለጫው አረጋግጧል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በቀጣይ በሚያካሂደው 13ኛ መደበኛ ጉባኤን በተመለከተም ጥልቅ ውይይት ማድረጉን ገልጿል።

ህወሓት አሁን ያለው የትግል መድረክ በተሻለ መልኩ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ፥ ጉባኤውን በብስለት በመምራት ተጨማሪ ጉልበት ፈጥሮ እንዲወጣ በሚያስችለው መንገድ እንደሚመራውም ነው ማዕከላዊ ኮሚቴው የገለጸው።

ቀጣዩ ጉባኤ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ እንዲካሄድ እና አንድነትና ፅናትን ጠብቆ አሁን ላይ በክልሉ ብሎም በሃገር ደረጃ ያሉ ፈተናዎችን ለመመከት በሚያስችል መንገድ ድርጅቱ ተጠናክሮ የሚወጣበት እንዲሆንም ወስኗል።

ለዚህም ቀጣዩን ጉባኤ ለማደናቀፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ከህዝቡና አባላቱ ጋር በመሆን በመመከት በተሳካ ሁኔታ እንደሚካሄድ እምነቱን ገልጿል።

በክልሉ በህጋዊ መንገድ በተደራጀና ባልተደራጀ ሁኔታ የሚካሄዱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በክልሉ ያለው ዴሞክራሲ እንዲጎለብትና የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ የላቀ ትርጉም ያላቸው ናቸው ብሏል።

ስለሆነም ማዕከላዊ ኮሚቴው ለህገ መንግስታዊ ስርዓት፣ ለህዝብ ተጠቃሚነትና ክብር ቅድሚያ በመስጠት ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር የጋራ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ለመስራት ያለውን ዝግጁነትም አረጋግጧል።

No comments