Latest

“ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት አንድም የረባ ጄኔራል አላፈራችም” ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (ክፍል ፪)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (ክፍል ፪)

ግዮን፡- ከሆላንድ ጉዞህ በፊት በአሜሪካ የተለያዩ ስቴቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንተን ለመቀበል ፕሮግራሞች አዘጋጅተው የነበሩ ቢሆንም፣ ቪዛ በመከልከልህ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል:: በቀጣይ ይህ ጉዞ ዕውን ይሆናል?
ተመስገን፡- የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ኤምባሲ አለው፤ ያ ኤምባሲ ደግሞ አሜሪካ ሀገር የሚገቡትንና የማይገቡትን ሰዎች የመወሰን ስልጣን ነው:: 


በዚህ መሰረትም መጀመሪያ ጊዜ በተላከልኝ ግብዣ ‘ሀብት፣ ንብረት፣ ሚስት የለህም’ በሚል ደርሼ መመለሴን ስልተጠራጠሩ ከልክለውኛል፤ ከዚያ በኋላ ዳላስ በሚዘጋጀው ዓመታዊው የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌስቲቫል ላይ፣ ፕሮግራሙን የሚያዘጋጁት ኮሚቴዎች በዚህ ዓመት የክብር እንግዳ ሆኜ እንድገኝ ጥሪ አድርገውልኝ ነበር፤ እኔ እንዲያውም ኤምባሲውን በድጋሚ ቪዛ የመጠየቅ ፍላጎት እንደሌለኝ ለአስተባባሪዎች ነግሬያቸው ነበር::  

እነሱ ግን፣ ‘የእኛ ፌዴሬሽን ከተመሠረተ ዘንድሮ 35ኛ ዓመቱ ነው፤ እስከ ዛሬ ድርስም 34 ዓመታት ሙሉ ከኢትዮጵያ እንግዳ በየዓመቱ ጋብዘናል፤ በደርግም ጊዜ ቢሆን፣ እስካሁን እኛ የጋበዝነው አንድም ሰው ተከልክሎ አያውቅም:: 

ፌደሬሽናችን በአሜሪካ መንግሥትም ሆነ ኢትዮጵያ በሚገኘው ኤምባሲያቸው ስለሚታወቅ ልትከለከል አትችልም’ ብለው ጋብዘውኝ የነበረ ቢሆንም፤ ኤምባሲው የራሱ በሆነ ምክንያት የመግቢያ ቪዛውን ስለከለከለኝ ሳልሄድ ቀርቻለሁ:: ይኸው ነው። ውሳኔያቸውን ደግሞ አከብራለሁ።

ግዮን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምን ዓይነት ቅርፅ መያዝ እንዳለበትና ተቋሙ አሁን ስላሉት እውነታዎች የምትሰጣቸውን ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች "ወታደራዊ ተንታኝ" እያሉ ሲጠቅሱክ እንሰማለን። መረጃቸውን ከየት ነው የምታገኘው?
ተመስገን፡- ከዚህ በፊት በሠራሁባቸውና በሥርዓቱ በተሠውት አራት ትልልቅ ሚዲያዎች ላይ በነበርኩበት ጊዜ፣ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥም ሆነ በተለያዩ የሲቪል መዋቅር ላይ ያሉ ለውጥ ፈላጊ ኃላፊዎች የተለያዩ መረጃዎችን በምስጢር ያቀብሉኝ ነበር::  

ከእነሱ ጋር ባለኝ የጠነከረ ግንኙነትም የመከላከያውን እንቅስቃሴ በቅርብ እከታተላለሁ፤ በቂ መረጃም አገኝ ነበር:: እስር ቤት ከገባው በኋላ ደግሞ ወታደራዊ ሳይንስ ላይ የሚያተኩሩ ጥቂት መፅሀፎችን የማንበብ ዕድል ማግኘት ችዬ ነበር። ከእስር ከተፈታሁ በኋላ መከላከያው ላይ የጥናት ዲሲፕሊንን በጠበቀ መልኩ ባይሆንም እንኳ፣ ቀለል ባለ መንገድ የሠራዊቱን ቁመናና አሰራር ለመገምገም ሞክሬያለሁ። 

ከአንጋፋ የጦር መኮንኖች ጋርም ውይይት በማድረግና በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ የተጻፉ መጽሐፎችን በማገላበጥ፣ የመከላከያው መዋቅርና የአስተዳደር ፍልስፍናውን በተመለከተ የግል አስተያየቴን በሚዲያዎች ላይ መስጠትን ጨምሮ የተሰናዳ ጥራዝ ለማዘጋጀትም እየሞከርኩ ነው:: እንግዲህ መነሻው ይሄ ይመስለኛል::

ግዮን፡- የኢትዮጵያ መከላከያ፣ “በአንድ ብሔር የበላይነት የተዋቀረ፣ እንደ ሀገርና ሕዝብ አገልጋይ ሳይሆን፤ እንደ ፓርቲ እየሠራ ነው” ይባላል፤ ይሄ ችግር ፀድቶ መከላከያው ምን ዓይነት መዋቅር መያዝ አለበት?
ተመስገን፡- አንድ ነገር ሁላችንም መገንዘብ አለብን፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ በሁለንተናዊው የተሟላና ጠንካራ የሚባል ዘመናዊ ሠራዊት ኖሯት አያውቅም::  

ከሞላ ጎደል ለአርበኝነትና ለሀገር ፍቅር ቅድሚያ የሚሰጥ ሠራዊት ነው የነበራት:: አብዛኛው የታሪኳ ክፍል በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ጦርነቶች የሚሸፈነው ኢትዮጵያ ዘመናዊና ጠንካራ ሠራዊት የላትም ሲባል መቼም ማስገረሙ አይቀርም። እንዲህም ሆኖ ግን ከመቶ ዓመት ወዲህ ባለው ዘመናችን ተመርኩዘን ወደ ንፅፅር ውስጥ እንግባ ካልን፤ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አወቃቀርና ብቃት፤ ከደርግ ዘመንም ሆነ አሁን ኢሕአዴግ "ገነባሁት" ከሚለው መከላከያ የተለየና በጣም ጠንካራ ዲሲፕሊን ያለው፣ አካዳሚክ ዕውቀቱ ምዘና ተደርጎበት የተደራጀ ነበር ለማለት ያስደፍራል።  

በነገራችን ላይ ያንን መሰል የሠራዊት ግንባታ አፄ ተዎድሮስ አልመውት የነበረው ነው፣ አፄ ኃይለስላሴ ወደ መሬት ያወረዱት። ተፈሪ መኮንን ገና የንግስት ዘውዲቱ እንደራሴ እያሉ 12 ወጣቶችን ፈረንሳይ ሀገር ወደ ሚገኙ የጦር ትምህርት ቤቶች ልከው የተለያየ ትምህርት እንዲማሩ ከማድረጋቸውም በዘለለ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤትን ገንብትው እጩ መኮንኖችን መልምልው ወደ ስራ ገብተው ነበር።  

ይህ በሆነ በዓመቱ ደግሞ ፋሺስት ጣሊያን ለዳግም ወረራ በመምጣቱ ሥልጠናው ተቋረጦ፣ ሠልጣኞቹም በአርበኝነት በመሰማራት ዝነኛውን የ"ጥቁር አንበሳ ጦር" በመመስረት ሀገር በመታደጉ ሂደት ላይ ታላቅ አበርክቶ እንደነበራቸው ታሪክ ያስታውሳቸዋል። 

የሆነ ሆኖ አባ ጠቅል ከነፃነት በኋላ ዳግም ወደ ስልጣን ሲመጡ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው የአቅማቸውን ያህል ሰርተውብታል። በተለይም በ1950 ዓ.ም የ"ሀረር ጦር አካዳሚ" ከተከፈተ በኋላ የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው ከፍተኛ የሆኑ ወጣቶች ተመልምለው አንዳንዴም ተገድደው በመኮንንነት እንዲሰለጥኑ ማድርጋቸው በተከታታይ ከመጡት ሁለቱ ስርዓቶች በአእምሮ፣ በአካል ብቅት እና በዲሲፒሊን የተሻለ የጦር ሠራዊት መገንባት አስችሏቸው እንደ ነበረ አይዘነጋም። የአየር ኃይልም ሆነ የባህር ኃይል ግንባታም የንጉሠ ነገሥቱ ተጠቃሽ ስኬታማ ስራ ነው።

ግዮን፡- በደርግ ሥርዓት የነበረው የሀገር መከላከያ ሠራዊትስ?
ተመስገን፡- የኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ ማርያም አስተዳደር፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴን የወታደራዊ ተቋማት ሕልምና ፍልስፍና የማስቀጠል ሙከራም ፍላጎትም እንደ ነበረው አይካድም፤ ነገር ግን ገና ከጠዋቱ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የሞሀመድ ዚያድባሬ መንግስት ታላቋን ሶማልያ ለመፍጠር ያደረገው ወረራ፤ በሰሜኑ የሀገራችን ክልል ደግሞ ጀበሃ፣ ሻዕቢያ፣ ኢህአፓ እና ወያኔን የመሳሰሉ ነፍጥ ያነሡ ኃይሎች የጎን ውጋት ሆነውበት ስለነበር፣ በተረጋጋ ሁኔታ መደበኛውን የስልጠና ካሪኩለም ተከትሎ መሄድ የማይችልበት ደረጃ በመድረሱ፣ በንጉሡ ጊዜ እንደ ነበረው ጠንካራ ምልምላ ተደርጎ ለሥልጠና ከሚገባበት አሠራር ይልቅ፣ ሀገርን ወደ ማዳን ግዴታ ፊቱን በማዞሩ ከሞላ ጎደል የጥራት ደረጃውና ጥንካሬው እየወረደ ሄዷል::  


ሶማሊያ የሽንፈትን ፅዋ ተጎንጭታ ከተባረረች በኋላ ጥራት ላይ ለማተኮር ሙከራ ያደረግ ነበር፤ እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ ድረስ። ነገር ግን የሰሜኑ ጦርነት በተለያዩ ሀገራት ጣልቃ ገብነት የተፅዕኖ ቀጠናውን እያሰፋ በመሄዱ፣ ደርግም ባነበረው አምባገነናዊ አስተዳደር ምሬት የተነሳ ሕዝባዊ ድጋፍ በማጣቱ፣ የአማፂያኑ ጡንቻ እየፈረጠመ፣ የመንግስት ደግሞ እየተሸረሸረ በመሄዱ ከጥራት ይልቅ ብዛትን አማራጭ በማድረጉ ሙከራው ሊከሽፍበት ችሏል።

በተለይ በዓለም ደረጃ እንኳን ባይሆን ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ የተሻሉ የሚባሉ ጄኔራሎች የነበሯት እስከ 1981 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ድረስ ብቻ ነው ብዬ አስባለሁ:: የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን መክሸፍ ተከትሎ እነ ጄኔራል ደምሴ ቡልቱ፣ ጄኔራል ፋንታ በላይ፣ ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ፣ ጄነራል አማሃ ደስታን የመሳሰሉ ብቃት ያላቸው ስመ ገናና፣ በታላላቅ የምዕራብ ሀገራት ወታደራዊ ዩኒቨርስቲዎች ተምረው በማዕረግ የተቀመረቁትን ጨምሮ ከ26 በላይ ጄነራሎች የክሽፈቱ ሰለባ በመሆናቸው ሞራሉ የተዳከመውን ሠራዊት አመራር አልባ አድርጎታል።

እንግዲህ ይህ አጋጣሚ ነው ሸዕቢያን ለሶስት አስርታት ከተንጠላጠለበት ናቅፋ ተራራ አወርዶ ወደ ምፅዋና አስመራ እንዲገሰግ፤ ወያኔን ደግሞ ከትግራይ ባሸገር አዲስ አበባን እንዲያማትር ያደፋፈረው። በነገራችን ላይ የጄኔራሎች ህልፍት ሌላም ጦስ አስከትሏል። 

ይሀውም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም በፈንቃዮቹ በተገደሉት መከላከያ ሚንስትር ሜ/ጄ ሀብተ/ጊዮርጊስ ምትክም ሆነ፣ ራሳቸውን ባጠፉት ኤታ ማዦር ሹም ሌ/ጄ መርድ ንጉሴ እና በወቅቱ ጠንካራ የነበረው የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት አዛዥ ሜ/ጄ ደምሴ ቡልቱም ሆነ በተዋረድ ለተዋቀሩት ክፍለ ጦሮች አዳዲስ ጄነራል አዛዦችን መተካት ስለነበረባቸው፣ የተከተሉት አማራጭ የግድ ኮለኔሎችን በጄነራልነት መሾም ነበር፤ ያ ደግሞ ወቅቱን ጠብቆና በሥራ አፈፃፀም የመጣ የማዕረግ ዕድገት ስላልሆነ አዲሶቹ ጄኔራል ተሿሚዎች የቀድሞ አለቃዎቻቸውን ብቃት ተክተው መስራት አልቻሉም::  

ምክንያቱም ኮለኔሉን፣ ጄኔራል ብታደርገው የሚኖረው አቅም የኮለኔል ነው፤ ሻለቃውንም በኮለኔሎቹ ብትተካው ልክ እንደዚያው:: ከመፈንቅል መንግስቱ በፊት ግን ኮሎኔሎቹም ሆነ ሻለቃዎቹና መቶ አለቃዎቹ በቦታቸው የነበራቸው ውጊያን የመምራት ችሎታ፣ የአስተዳደር ዘይቤያቸው እና አጠቃላይ ሠራዊቱን ይመሩበት የነበረውን ብቃት ብትመለከተው በጣም ትደነቃለህ::

በነገራችን ላይ ከላይ የጠቀስኩት ክፍተት የተፈጠረው በጦር ሰራዊቱ ላይ ብቻ አይደለም፤ ወደ ፖሊስ ተቋም ብትመጣ ተመሳሳይ አሰራርን ነው የተከተሉት፤ የአዲስ አበባ ፖሊስም ሆነ የኢትዮጵያ ፖሊስ በደርግ ጊዜ በጣም ጠንካራ ነበረ:: ለምሳሌም በወቅቱ የኢትዮጵያ ፖሊስ አዛዥ የነበሩት አዛውንቱ ጄኔራል ወርቁ ዘውዴን ብንወስድ በመፈንቅለ መንግሥቱ ነው የተገደሉት፤ ልምድና ችሎታ ያላቸው ትልቅ ጄኔራል ነበሩ:: 

እርሳቸው ‘በመፈንቅለ መንግሥቱ ተሳትፈዋል’ ተብለው መጀመሪያ ታሰሩ፣ ከአመት በኋላ ደግሞ ተረሸኑ፤ ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም በቦታቸው የተኩት ሻለቃ ግርማ ንዋይ የሚባሉ ፖሊስን፣ ሜጀር ጄኔራል አድርገው በማሳደግ ነበር ለፖሊስ ሠራዊት አዛዥነት የሾሙት:: 

ሻለቃው፣ በሻለቃነቱ በቂ ዕውቀት ሊኖረው ይችላል፤ ግን በተፋጠነ የማዕረግ ዕድገት፣ ሰዎች ስለተጓደሉብህ ብቻ ጄኔራል ብታደርገው ብቁ ጄኔራል ሊሆንልህ አይችልም:: በዚህና በሌሎች ገፊ-ምክንያቶች የተነሳ በደርግ የመጨረሻ ዘመን አካባቢ የአፄው የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ጅማሮ ታሪክ ሆኖ ሊቀር ችሏል።

ይቀጥላል...

No comments