Latest

ዓለማችንን ከረሃብ ሊታደግ የሚችለው የስንዴ ዘር - ቢቢሲ

ዓለማችንን ከረሃብ ሊታደግ የሚችለው የስንዴ ዘር - ቢቢሲ

የትኛውንም አይነት የአየር ጸባይ መቋቋም የሚችሉ የስንዴ ዘር አይነቶችን ማግኘታቸውን ተመራማሪዎች እየገለጹ ነው። አለማቀፉ የተመራማሪዎች ቡድን ለምርምሩ እንዲረዳው ከ100 ሺ በላይ የስንዴ ዘረ መል አይነቶች መለየታቸውን ገልጸዋል።

የዘረ መል ካርታው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለውን ከባድ ሙቀትም ሆነ ማንኛውም አይነት የአየር ጸባይ መቋቋም የሚችሉ አዳዲስ የስንዴ ዝርያዎችን በአጭር ጊዜ ለማስተዋወቅ ይረዳል ተብሎለታል።

የምርምር ስራው ውጤት በአንድ ሳይንሳዊ ግኝቶች የሚቀርቡበት መጽሄት ላይ ታትሟል።

በጆን ኢንስ የምርምር ማዕከል የሰብል ዘረመል ጥናት ክፍል መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ክሪስቶባል ኡዋይ አዲሱን ግኝት የስንዴ ምርትን በአስገራሚ ሁኔታ የሚቀይር ነው ብለውታል።

አክለውም የሰው ልጅ ተለዋዋጭ የአየር ጸባይን ተቋቁሞ ለመኖር እንደዚህ አይነት የምርምር ውጤቶች ያስፈልጉታል ብለዋል። ''ሁላችንም ለብዙ ጊዜ ስንጠብቀው የነበረና በአለማችን ያለውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ወሳኝ ግኝት ስለሆነ፤ ሁሉም የሰው ዘር ደስ ሊለው ይገባል'' ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።


ግኝቱ ምን ያክል ጠቃሚ ነው
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና ግብርና መስሪያ ቤት (ኤፍ ኤ ኦ) እንደገመተው ከሆነ በ2050 የዓለማችን የህዝብ ቁጥር ወደ 9.6 ቢሊዮን ከፍ የሚል ሲሆን፤ የምግብ ፍላጎቱን ለማርካት ደግሞ የስንዴ ምርት ላይ 60 በመቶ ጭማሪ መደረግ አለበት።

WLADIMIR BULGAR/SCIENCE PHOTO LIBRARY
WLADIMIR BULGAR/SCIENCE PHOTO LIBRARY
ይህንን ምርት ለመጨመርና የተሻሉ ዘሮችን የማግኘት ሃላፊነት ወስዶ እየሰራ የሚገኘው ደግሞ በሜክሲኮ ሲቲ መቀመጫውን ያደረገው አለማቀፉ የበቆሎና ስንዴ ምርት ማሻሻያ ማዕከል ነው። የማዕከሉ ዋና አላማ ደሃ በሚባሉ ሃገራት የሚገኙ ገበሬዎችን ህይወት ለማሻሻል ብዙ ምርት የሚሰጡ ዘሮችን በምርምር ማግኘት ነው።

እስከዛሬ ሲያከናውኗቸው የነበሩት የምርምር ውጤቶች ተለዋዋጭ የአየር ጸባዮችን መቋቀወም የሚችሉ እንዳልነበሩና በተለይ ደግሞ ከፍተኛ ሙቀት አስቸጋሪ ሆኖ እንደቆየ የምርምር ማዕከሉ ዋና ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ራቪ ሲንግ ይናገራሉ።

ይህንን የምርመር ውጤት ለማሳካት ከ73 የተለያዩ የምርምር ተቋማትና 20 ሃገራት የተውጣጡ 200 ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ 21 የስንዴ ዘረ መል አይነቶችን ከነቦታቸው ለይተዋል።

የምርምር ውጤቱ የስንዴ ምርትን በብዙ እጥፍ የሚጨምር ሲሆን፤ ተለዋዋጭና አስቸጋሪ አየር ንብረት ላላቸው የሶስተኛው አለም ሃገራት ወሳኝ መፍትሄ ይዞ እንደሚቀርብ ይታሰባል።

ነገር ግን የምርምር ውጤቱ ከተቺዎች አላመለጠም። ተቺዎቹም እንደ ዋና ነጥብ የሚያነሱት አሁንም ቢሆን በአለማችን የሚመረቱ ሰብሎች የአለምን ህዝብ ለመመገብ በቂ ናቸው። ዋናው ችግር ያለው ክፍፍሉ ላይ ነው በማለት ይከራከራሉ።

ስለዚህ የዚህ የምርምር ውጤት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፤ በተገቢው መልኩ የማይከፋፈል ከሆነ ግን አሁንም ብዙ ቁጥር ያለው የአለማችን ህዝብ መራቡ አይቀርም እያሉ ነው።

No comments