Latest

ዳያስፖራውን ለማስተናገድ የአዲስ አበባ ሆቴሎች ዋጋቸውን በ31 በመቶ ቀንሰዋል - ታደሰ ገብረማርያም

ዳያስፖራውን ለማስተናገድ የአዲስ አበባ ሆቴሎች ዋጋቸውን በ31 በመቶ ቀንሰዋል

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከአዲሱ ዓመት መግቢያ በፊት ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ አገራቸው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተለይም ከፊት ለፊት ካለው የዘመን መለወጫ በዓል አስቀድሞና ከዚያም በኋላ የሚከበሩትን ሃይማኖታዊና አገራዊ በዓላትን መሠረት በማድረግ ወደ አገሩ የሚገባውን የዳያስፖራ ማኅበረሰብ እንዲሁም ሌሎች እንግዶችን በአግባቡ ተቀብሎ ማስተናገዱ አገራዊ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍፁም አረጋ እንደገለጹት፣ ለዚህ ትልቅ አገራዊ ትኩረትን ለሚስብ ክስተት ተቋማት፣ ማኅበራትና የአገሪቱ አጠቃላይ ማኅበረሰብ ቀጥተኛ ተሳትፎና የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ ከዚህ ግንዛቤ በመነሳት በርካታ ሆቴሎችና ተቋማት ከሚሰጧቸው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ክፍያዎች ላይ 25 በመቶ ቅናሽ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ማበረታቻን ለእንግዶች ለማቅረብ ፈቃደኝነታቸውን ማሳየታቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ቅናሽ ለማድረግ ፈቃደኝነታቸውን ካሳዩትም መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ መምሪያ፣ የአዲስ አበባ ሆቴሎች፣ የኢትዮጵያ አስጎብኚዎችና የቦሌ ኤርፖርት ታክሲዎች ማኅበራት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት አየር መንገዱ ከትኬት፣ የዜግነት ጉዳይ አስተዳደር ከቪዛ፣ ሆቴሎች ከመኝታ አገልግሎቶች ክፍያ ላይ ነው ቅናሽ ያደረጉት፤›› ብለዋል፡፡

ቅናሹ ተግባራዊ የሚሆነው ከነሐሴ 9 ቀን እስከ መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ቀናት ውስጥ ሲሆን፣ በአገልግሎቶቹ ላይ የተጠቀሰውን የዋጋ ቅናሽ እንዲኖር የተደረገው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማትና ማኅበራት ጋር በስፋት ተወያይቶ ከስምምነት በመደረሱ ነው፡፡

በተጠቀሱት ጊዜያት ውስጥ ከሚከበሩ በዓላት መካከል ከነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራና በትግራይ ክልሎች የሚካሄደው የአሸንድዬ በዓል ይገኝበታል፡፡ ይህ በዓል ወደ ካርኒቫልነት እያደገ ሲሆን፣ ትልቅ መስህብ እንደሚሆንና ዳያስፖራውም በዚህ እንደሚደሰት አቶ ፍፁም ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የአረፋ፣ የዘመን መለወጫ፣ የቡሄና የመስቀል በዓላት እንዳሉና እነዚህም በዓላት ለኢትዮጵያዊያንና ለትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ቱሪስቶችም መስህብ መሆናቸውንና ለአገሪቱ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ለዚህም ዝግጅት ሲባል ሆቴሎች ቀለም በመቀባትና ዙሪያቸውን በማስዋብ፣ እንዲሁም እንግዶቻቸውን የቆይታ ጊዜያቸውን አይረሴ ማድረግ የሚያስችላቸውን ዝግጅት አጠናቀው እንግዶቻቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቅናሽም ይሆን መልካም አገልግሎትን በማቅረብ ቆይታቸውን የበለጠ የሚታወስ ማድረግ የሚችሉ ድጋፎችን በመስጠት እንዲተባበሩ አቶ ፍፁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ ፍፁም እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚጠጉ ትራንዚት መንገደኞችን ያስተናግዳል፡፡ እነዚህም በኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አበባ ደርሰው ከኤርፖርት የማይወጡ ወይም ደግሞ የቆይታ ጊዜያቸውን በአንድና በሁለት ቀናት የሚያራዝሙ ናቸው፡፡ በዚህ የቆይታ ጊዜያቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ቢችሉም፣ የሚስቧቸው ነገሮች ባለመኖራቸው ግን አገሪቱ የሚገባትን ጥቅም ማግኘት እንዳትችል አድርጓታል፡፡

ከእነዚህ መንገደኞች ማግኘት የሚቻለውን የውጭ ምንዛሪ አገሪቱ ውስጥ ለማስቀረት መንገደኞቹን የሚስብ የቱሪዝምን እንቅስቃሴ ለመፍጠር ከዓለም ባንክ በተገኘ የአንድ ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ የባለሙያዎችን አቅም ከማሳደግ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ሰባት ቦታዎች ላይ የመሠረተ ልማት አውታሮች ሪዞርት ሆቴሎችን ለመገንባት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች እስከ አምስት ዓመት የገቢ ግብር እፎይታ፣ መሬት ከሊዝ ነፃ የሚቀርብበት ሁኔታ እንዲሁም ከውጭ የሚያስገቧቸውን ማንኛቸውንም ዓይነት የመገልገያ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የሚያደርጉ ማበረታቻዎች እንደሚደረግላቸውም ተናግረዋል፡፡

የመሠረተ ልማት አውታሮችና የሪዞርት ሆቴሎች ከሚገነቡባቸው ቦታዎች መካከል ኤርታአሌ፣ የባሌ ተራራዎች፣ በደቡብ አርባ ምንጭ፣ በሰሜን የገረሃልታ አካባቢዎች እንደሚገኙበት አቶ ፍፁም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማኅበር ተወካይ አቶ ያዕቆብ መላኩ፣ ዝግጅቱን በማስመልከት ተቋማት ያደረጉት የመነሻ የዋጋ ቅነሳ 25 በመቶ እንዲሆን የተወሰነ ቢሆንም፣ በባለሙያ የተደገፉ ለዳያስፖራው ብቻ የተዘጋጁ ፓኬጆች ወይም ዝቅተኛ የሆነ ክፍያ በማስከፈል ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ከሁለት መቶ በላይ አስጎብኚዎችን በአባልነት ያቀፈው ይህ ማኅበር፣ እንዲህ ዓይነት አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጀበት ምክንያት ዳያስፖራዎች ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ አገሪቱን ሊያስተዋውቁ ይችላሉ ከሚል የፀና እምነት በመነሳት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢንያም ብስራት፣ ማኅበሩ አንድና ከዚያ በላይ ኮከብ ያላቸው 118 ሆቴል አባላት እንዳሉት፣ በሥሩ ያሉት ሆቴሎች በሙሉ ለዚህ ፕሮግራም ዋጋቸውን በ31.08 በመቶ ቅናሽ ለማድረግ እንደተዘጋጁ አመልክተዋል፡፡

መስተንግዶ በቅናሽ ዋጋ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን ሆቴሎችን በማስዋብ፣ አስተናጋጆችም እንግዶቹን በፈገግታ፣ በአክብሮትና በትህትና አቀባበል ሊያደርጉላቸው የሚያስችሉ ሁኔታዎች በመመቻቸት ላይ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሬስቶራንቶችና ታክሲዎች አቀባበልና መስተንግዶ እንዲያደርጉም ማኅበሩ እያነሳሳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኩሪፍቱ ሪዞርቶች ባለቤትና የቢሾፍቱ ከተማ የሆቴሎች ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ አቶ ታዲዎስ ጌታቸው በተለያዩ ሰባት ሐይቆች ላይ የተሠሩና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው 23 ሪዞርቶች በተለያዩ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ለመቀበል የሚያደርጓቸውን ዝግጅት እንዳጠናቀቁ ገልጸዋል፡፡

ከነዚህም መካከል በተለይ የኩሪፍቱ ሪዞርት ቅዳሜና እሑድ 25 በመቶ ቅናሽ አድርጎ ሌሎቹን ቀኖች ማለትም ከእሑድ እስከ ሐሙስ 50 በመቶ በመቀነስ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን፣ ለዚህም ተጠቃሚዎች ፓስፖርት ይዘው መምጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

No comments