Latest

በቦምብ ፍንዳታው ተጠርጥረው የታሰሩ የፖሊስ አመራሮች በዋስ ተለቀቁ - ታምሩ ጽጌ

በቦምብ ፍንዳታው ተጠርጥረው የታሰሩ የፖሊስ አመራሮች በዋስ ተለቀቁ

ቦምቡን በመወርወርና በማቀበል ለተጠረጠሩት የክስ መመሥረቻ ጊዜ ተፈቀደ


ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተዘጋጀው ድጋፍና የምሥጋና ሠልፍ በወጡ ሰዎች ላይ ቦምብ ተወርውሮ ካደረሰው የሞትና የአካል ጉዳት ጋር በተያያዘ፣ ላለፉት 52 ቀናት በእስር ላይ የቆዩት 11 የፖሊስ አመራሮች ማክሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በዋስ ተፈቱ፡፡

ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የምርመራ መዝገቡን ከአሥራ ሁለት ቀናት በፊት መረከቡን ያረጋገጠው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የተረከበውን መዝገብ መርምሮ ያጠናቀቀ ቢሆንም፣ ውሳኔ ለመስጠትና በሚከሰሱ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መሥርቶ ለማቅረብ ጊዜ እንዳጠረው ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡  


በመሆኑም ክስ መሥርቶ ለማቅረብ ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲፈቀድለት ሲጠይቅ፣ ክሱን እስከሚመሠርት ድረስ በእስር ላይ የሚገኙት 11 የፖሊስ አመራሮች በበቂ ዋስ ቢለቀቁ፣ የማይቃወም መሆኑን ነሐሴ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት አስታውቆ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪዎች ያላቸውን ወርኃዊ ገቢ ከጠየቀ በኋላ፣ ገቢያቸውን የሚመጥን ዋስትና ለመወሰን በአዳር በቀጠረው መሠረት፣ ማክሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በወር ተጣርቶ የሚደርሳቸው ከ2,500 ብር እስከ 7,000 ብር መሆኑን መግለጻቸውን ታሳቢ ያደረገ ዋስትና አስይዘው፣ ወይም የሰው ዋስ አቅርበው ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡  

በትዕዛዙ መሠረት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞው ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ በ15,000 ብር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አባል የሆኑት ኮማንደር ገብረ ኪዳን አሰግዶም፣ ኮማንደር ገብረ ሥላሴ ተፈራ፣ ኮማንደር ግርማይ በርሄ፣ ኮማንደር አንተነህ ዘነበ፣ ምክትል ኮማንደር አባቡ ዳምጤ፣ ምክትል ኮማንደር አብዲሳ ጋዲሳና ምክትል ኮማንደር ጫኔ ጠቋሬ እያንዳንዳቸው በ9,000 ብር፣ እንዲሁም ምክትል ኢንስፔክተር ሀገሬ ቀኔሳና ዋና ሳጅን ድራር ታረቀኝ እያንዳንዳቸው በ6,000 ብር፣ ዋና ሳጅን ከድር ዓሊ በ7,000 ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በዋናነት የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ መስቀል አደባባይ የተመመው ሕዝብ በአግባቡ ተፈትሾ እንዲያልፍ ባለማድረጋቸውና እኩይ ተግባር ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ቦምብ ይዘው እንዲያልፉ ክፍተት በመፍጠራቸው፣ ሁለት ሰዎች እንዲሞቱና ከ100 በላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆነዋል በማለት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹም ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወናቸውንና ምንም ዓይነት ክፍተት አለመፍጠራቸውን፣ እነሱ ማድረግ የሚችሉት በሥራቸው ያለውን የፀጥታ ኃይል ሥራውን በተገቢው ሁኔታ እንዲሠራ ትዕዛዝ መስጠትና መከታተል መሆኑን በተደጋጋሚ በመናገር፣ ያንንም ተግባራዊ በማድረጋቸው፣ የሚፀፅታቸው ነገር እንደሌለ ለፍርድ ቤቱ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡  

መታሰር ከነበረባቸውም እነሱ ብቻ ሳይሆኑ በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ላይ አብረዋቸው ተሰማርተው የነበሩ በሙሉ መሆን ሲገባቸው፣ እነሱ ብቻ ተነጥለው መታሰራቸውን በመቃወም ‹‹ለምን እኛ ብቻ?›› በማለትም ሲጠይቁ ከርመዋል፡፡ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ጥያቄ እንጂ የተለየ ምርመራ ተደርጎባቸው እንደማያውቁ ለፍርድ ቤቱ በመግለጽ፣ እነሱም በወቅቱ የተፈጸመውን ድርጊት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የሚያወግዙትና የሚቃወሙት መሆኑን በመናገር፣ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው የምርመራው አካል ሆነው ለመሥራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡  

አንዳንዶቹ ኮማንደሮች ፍርድ ቤት በቀረቡ ቁጥር ለፍርድ ቤቱ ስለራሳቸው ለመናገር ሳግና እንባ እየተናነቃቸው ንፁህ መሆናቸውን በተቆራረጠ ድምፅ ሲያስረዱ ቆይተዋል፡፡ እንደነሱ ተደጋጋሚ ጥያቄ የዋስትና መብታቸው ወዲያውኑ ባይፈቀድላቸውም፣ በ52ኛ ቀናቸው የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው ከእስር ተፈትተዋል፡፡

ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ የተወረወረውን ቦምብ በማቀበልና በመወርወር ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ብርሃኑ ጃፋርና አቶ ጥላሁን ጌታቸውን ጨምሮ፣ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን የጠየቁ ቢሆንም ዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ አቅርቦባቸዋል፡፡  

በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ሁለት ሰዎች በመሞታቸውና ከ100 በላይ ሰዎች ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ስለደረሰባቸው፣ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በሚመሠረተው ክስ የሚጠቀሰው የሕግ አንቀጽ ዋስትና ሊከለክል ወይም ላይከለክል ስለመቻሉ ማወቅ ስለማይቻል፣ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ እንዲለቀቁ ያቀረቡትን ጥያቄ ዓቃቤ ሕግ ተቃውሟል፡፡  

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ በማለፍ፣ ዓቃቤ ሕግ ከጠየቀው ክስ መመሥረቻ 14 ቀናት ውስጥ ሰባት ቀናት ፈቅዶ ለነሐሴ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments