Latest

ለ650 የህግ ታራሚዎች ይቅርታና ምህረት ተደረገ


(ኤፍ.ቢ.ሲ) ለ650 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ እና መህረት መደረጉ ተገለፀ።

ይቅርታ የተደረገላቸው የሀግ ታራሚዎች በፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የተፈረመ የይቅርታ ሰርተፍኬት እንዲደርሳቸው በማድረግ ከእስር እየተፈቱ መሆኑም ተነግሯል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የይቅርታ ቦርድ በሀምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ባሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ ለፕሬዚዳንቱ ማቅረቡን ተከትሎ ነው ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ ታራሚዎቹ እንዲፈቱ እየተደረገ የሚገኘው።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የይቅርታ ቦርድ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዘለቀ ዳላሎ ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ድሬደዋ፣ ከቃሊቲ፣ ዝዋይ እና ቂሊንጦ ማራሚያ ቤት የሚገኙ ናቸው።

ታራሚዎቹ በይቅርታ አዋጁ መስፈርት መሰረት በልዩ ሁኔታ ማለትም በእድሜ መግፋት፣ በከባድ ጤና ችግር እና የተፈረደባቸውን ፍርድ አንድ ሶስተኛ የጨረሱ እንዲሁም የተላለፈባቸውን የገንዘብ ቅጣት የከፈሉም ይገኙበታል።

ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ የፀደቀውን የምህረት አዋጅ ተከትሎ መስፈርቱን የሚያሟሉ ጉዳያቸው በክርክር ሂደት ላይ የሚገኙና በተለያዩ ጉዳዮች ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፖሊስ ምርመራ ላይ የሚገኙ አካላት በሀገር አቀፍ ደረጃ የምህረት ሰርተፍኬት እየደረሳቸው እና ክሳቸው እንዲቋረጥ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከ200 በላይ የሆኑት የምህረት ሰርተፍኬት እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፥ በክልል ደረጃም በተመሳሳይ ለክልሎች ፍትህ ቢሮ በተሰጣቸው ውክልና መሰረት የምህረት ሰርተፍኬት መስጠት ጀምረዋል ብለዋል አቶ ዘለቀ።

በታሪክ አዱኛ

No comments