Latest

መጪው አዲስ ዓመት “በፍቅር እንደመር በይቅርታ እንሻገር” በሚል መሪ ቃል ይከበራል- መንግሰት

መጪው አዲስ ዓመት “በፍቅር እንደመር በይቅርታ እንሻገር” በሚል መሪ ቃል ይከበራል- መንግሰት

(ኤፍ.ቢ.ሲ) መጪው አዲስ ዓመት “በፍቅር እንደመር በይቅርታ እንሻገር” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ በዓሉ ከ25 ሺህ በላይ ህዝብ በሚገኝበት በሚሊኒየም አዳራሽ በድምቀት እንደሚከበር ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን፥ መንግስት በሀገሪቱ ተስተውሎ የነበረውን ቀውስ በትክክለኛ መንገድ በመፍታት በህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር የሪፎርም ስራዎችን በመስራት የለውጥ፣ የአንድነትና የይቅርታ ሂደት በመጀመሩ መጪውን አዲስ አመት በደማቅ ሁኔታ ለመቀበል አስፈልጓል ብለዋል በመግለጫቸው።

መጪውን አዲስ ዓመት በደማቅ ሁኔታ ማክበር ያስፈለገበት ምክንያት ሚኒስትር ዴኤታው ሲገልጹ በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር የነበረውን ችግር መፍታት መቻሉ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር ቤት ገብተው በሰላማዊ ሁኔታ ለመስራት መወሰናቸው፣ እንዲሁም የሀይማኖት መሪዎች የነበራቸውን ልዩነት ወደ አንድነት የቀየሩበት ይቅርታና አንድነት በተግባር የታየበት ወቅት በመሆኑ ነው ብለዋል።

በኢኮኖሚው መስክ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረትም ኢንቨስትመንት በመሳብና የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በመቋቋም ችግሩን በፍጥነት ማስወገድ መቻሉንም አቶ ካሳሁን አንስተዋል።

እንዲሁም በዲፕለማሲው በኩልም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በተለይ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ሻካራ ግንኙነት በመፍታት ወደ እርቅና ሰላም የተመጣበት ጊዜ ነውም ሲሉ አስረድተዋል።

ለረዥም ዓመታት ታስረው የነበሩ የፖለቲካ እስረኞችንም በመፍታት ሀገራዊ መግባባት የተፈጠረበት እንደሆም ገልጸዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጣውን የለውጥ ሂደት በመጪው ዓመትም በአዲስ ተስፋ በተጠናከረ ሁኔታ ለማስቀጠል ቃልን የማደስ መርሀ ግብር ለማከናወን በማሰብ በደማቅ ሁኔታ የአዲሱን ዓመት ዋዜማ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በእለቱም የኪነጥበብ ዝግጅቶችን ጨምሮ የአንድነትና የይቅርታን ጠቀሜታ የሚያጎሉ መልእክቶች እንደሚተላለፉም ሚኒስትር ደኤታው አቶ ከሳሁን አስታውቀዋል።

በአሉ በዋናነት በሚሊኒየም አዳራሽ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት የሚከበር ቢሆንም መሪ ቃሉን በሚያሰርፅ መልኩ ከአዲሱ ዓመት በፊትና በኋላ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቃል የማደስ ፕሮግራሞች ይከናወናሉ ሲሉም ተናግረዋል።

የሚዲያ ተቋማትም የመሪ ቃሉን ጽንሰ ሃሳብ በዝርዝር ለህብረተሰቡ በማስረዳት አዲሱ ዓመትን በተስፋና በአዲስ መንፈስ ልንቀበለው ይገባል ሱሉም አቶ ካሳሁን መልእክት ማስተላለፋቸውን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

No comments