ወደ ሃገር ቤት የተመለሱ ታጣቂዎችን ለማቋቋም የጀርመን መንግስት ቃል ገባ
በአጠቃላይ ትጥቅ ፈተው ወደ ሃገር ቤት የተመለሱ ታጣቂዎች ቁጥር 35ሺ ያህል መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከተመራው የኢትዮጵያ መንግስት ልኡካን ጋር በፈረንሳይና በጀርመን ቆይተው ሲመለሱ መግለጫ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ከአለም ባንክ የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ብድርና ድጋፍ መገኘቱንም ገልጸዋል።
አርበኞች ግንቦት 7፣የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣የአማራ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄና ሌሎች በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ሃይሎች በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስነው ታጣቂዎቻቸውን ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸው ይታወቃል።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባርና ሌሎች መሰል ሃይሎችም ከመንግስት ጋር በንግግር ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
እስካሁን ወደ ሃገር ቤት የገቡት ታጣቂዎች በቁጥር 35ሺ ያህል መሆናቸውን የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እነዚህን ሃይሎች ለማቋቋም ይረዳ ዘንድ በልማትና በቴክኒክ ለመደገፍ የጀርመን መንግስት ቃል መግባቱን ገልጸዋል።
ለሃገሪቱ ልማት ከአለም ልማት ባንክ በብድርና በእርዳታ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መገኘቱን የገለጹት አቶ አህመድ ሽዴ ተጨማሪ 500 ሚሊየን ዶላር ለመስጠትም የአለም ባንክ ቃል መግባቱን ተናግረዋል።
No comments