Latest

አዲስ አበቤን መመጠን የሚችሉ ተቋማትና ግለሰቦች መቼ እናገኛለን? ብርሃኑ ተ/ያሬድ



ብርሃኑ ተ/ያሬድ

መስከረም 10/2011 ጠዋት የእስር ክፍሌ(የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጨለማ ክፍል)በሀይል ተንኳኳ ከዚያም ወደ ክፍሉ ብርሀን በምታስገባው ትንሿ መስኮት በኩል "ብርሀኑ ተክለ ያሬድ እዚህ ነህ?" የሚል ጥሪ መጣ
፡፡ 

በተኛሁባት ፍራሽ ላይ ሆኜ"አዎ እዚህ ነኝ" ብዬ መለስኩ ራሴ ፈልጌ የገባሁ ይመስል "ና ውጣ!!" የሚል የቁጣ ድምፅና የቁልፍ መቅጨልጨል ተከተለ፡፡ ከክፍሉ ስወጣ ኮሪደሩ ላይ በሁለት ፖሊሶች የታጀበና በእጁ የሬድዮ መገናኛ የያዘ ሰው ቆሟል፡፡ 

"ያኛውስ የታለ መኮንን የሚባለው?" አለ ፖሊሶቹ መኮንን ያለበትን ክፍል መክፈት ጀመሩ ሰውየው ወደኔ ዞሮ በንቀት እየተመለከተኝ፡፡ "እሺ ባለ ባንዲራው የራስህ ባንዲራ አለህ አይደል"አለኝ የለበስኩት ጃኬት ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ማለቱ ነው፡፡ "ለመሆኑ ምን አርገህ ነው የተያዝከው?" አለኝ ፡፡ "አላውቅም" አልኩ፡፡ 

በቁጣ እየጮኸ "እኛ ግን እናውቃለን" አለኝ በግርምት እያየሁት ዝም አልኩ፡፡ "ለመሆኑ አገር ለማስበጥበጥ ለአዲስ አበባ ልጆች ገንዘብ የምትበትነው ለምንድነው?" አሁንም በግርምት እያየሁት "ከየት አምጥቼ?" "እሱንም እኛ እናውቃለን" አለኝ፡፡ 

ከዚህ ሰው ጋር ተነጋግሮ መግባባት እንደማይቻል ገባኝ ሰውየው ወደ መኮንን ዞሮ "ምን አድርገህ ነው የተያዝከው?" ብሎ ጠየቀው ፡፡ መኮንን ከህመሙ ጋር እየታገለ "ሰዎች አይደላችሁም? ልብ በሽተኛ ነኝ የምጠጣው ውሀ አጣሁ በዛ ላይ በር ተቆልፎብኛል እንድሞት ነው የምትፈልጉት?" አለ፡፡ ሰውየው በቁጣ "የተጠየቅከውን ብቻ መልስ ምን አድርገህ ነው የተያዝከው?"ብሎ ደነፋ፡፡ 

መኮንን አሁንም በጨዋነት "ልጄ ታማ ሆስፒታል ወስጃት ስመለስ........"ብሎ ሲጀምር "ዝም በል በቃ ምን አድርገህ እንደተያዝክ እኛ እናውቃለን እወቁት አይሳካላችሁም የአዲስ አበባ ወጣቶችን ለማነሳሳት ምን ያህል ስትጥሩ እንደነበር እናውቃለን፡፡ እናንተን ብሎ ባለ ባንዲራ ህገ ወጦች በትንሹ እየታሰሩ መለቀቅ ለምዳችኋል ትበሰብሷታላችሁ......." መጮህና መዛት ጀመረ ፡፡ 

የሰውየው በባዶ ሜዳ መንጨርጨር አስገርሞኝ "ያጠፋችሁትን አውቃለሁ ካሉ ያልተናገርኳቸው አያስፈልግም የሚያስረንና የሚቀጣን ፍርድ ቤት መስሎኝ" አልኩ ""ዝም በል አንተን ብሎ ሀገር ወዳድ ደግሞ የአዲስ አበባ ልጅ ብሎ ታጋይ ሌባ ሁሉ ..............."እያለ አሁን ልናገራቸው የማልችላቸውን ስድቦች መደርደር ጀመረ፡፡ 

ሁለታችንም የሰውየውን ስድቦች ትተን ፖሊሶቹ ክፍተሸ ወደ ተዉአቸው ክፍሎቻችን አዘገምን የሰውየው አጃቢዎች ለመማታት ተገለገሉ እዚህ ያልተናገርኳቸውእና ሰውየው ይሰነዝራቸው የነበሩ ስድቦችን ተመርኩዤ "አንዱ የከፋው ደህንነት ነኝ ባይ ይሆናል" ብዬ ነበር ስለ ማንነቱ ያወቅኩት መርማሪዎቼ "ኮሚሽነር ሲያናግርህ ለምን በስነ ስርአት አልመለስክለትም" ብለው ሲጠይቁኝ ነው ለካ ሰውየው ኮሚሽነር ደግፌ በዲ ነው ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሚመራው እስረኛ ላይ በሚዝት ተጠርጣሪን ያለ ፍርድ ቤት ፍርድ ወንጀለኛ የሚል የፖሊስ አባል ለአዲስ አበባ ይገባታል? ንፁሀንን ያለ ፍርድ በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ አስቀምጦ እንደፍርድ ቤት ዳኛ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ይፈታሉ ብሎ መናገርስ ህጋዊነት ነው? 

ለሰከንድስ ንፁሀን ለምን ይታሰራሉ? እመኑኝ አዲስ አበባን የሚመጥን ፖሊስ አልተገነባም አዲስ አበባን የሚመጥኑ ባለስልጣናትም የሉንም መቼ ይነጋል?

No comments