Latest

በሰላማዊ መንገድ የጀመረውን ትግል እንደሚያጠናክር የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራሮቹ ገለጹ

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራሮቹ

ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሂደት መጎልበት በሰላማዊ መንገድ የጀመረውን ትግል እንደሚያጠናክር የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራሮች ገለጹ። ለአመራሮቹ ዛሬ በደብረብርሃን ከተማ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ስታዲየም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

የንቅናቄው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ንቅናቄው ለህግ የበላይነት መስፈንና ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅምና መብት መከበር የሚያካሂደውን ትግል አጠናክሮ ይቀጥላል።

ንቅናቄው በአገሪቱ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የኢትዮጵያውያን ታሪክ፣ ወግ፣ ባህልና ማንነት ተከብሮ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶች እንዲዳብሩ ይሰራል ብለዋል፡፡

ዴሞክራሲው  እንዲሰፋና የኅብረተሰቡ እኩል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ንቅናቄው ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከመንግሥት ጋር በቅንጅት ለመሥራት መዘጋጀቱንም ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስታውቀዋል፡፡

የተጀመረው ለውጥ በጥቅመኞች እንዳይቀለበስ ኅብረተሰቡ ለህግ የበላይነት መስፈን እንዲታገልና የየአካባቢውን ሰላም ነቅቶ እንዲጠብቅ ሊቀመንበሩ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብታቸው ተጠብቆ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ከመንግሥት ጋር እንሰራለን ብለዋል፡፡

ወጣቱ ጥቅማቸው የተነካባቸው ግለሰቦች ብሄርንና ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው በሚያስነሱት ሁከትና ብጥብጥ  መጠቀሚያ መሆን እንደማይገባውም አስገንዝበዋል።

በአገሪቱ ነጻነት እንዲሰፍንና ድህነት እንዲወገድ ተግቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ  የህዝብ ግንኙተን ኃላፊ አቶ ነዓምን ዘለቀ በበኩላቸዉ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል፤ አንድነትና አብሮነት በማጎልበት ማንነታችንን ለመሸራረፍ የሚያስቡ ግለሰቦችን መታገል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ በማስቀጠልና መጪውን ምርጫ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን በማድረግ ሂደት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ቃል ገብተዋል፡፡

ምንጭ፡- ኢዜአ

No comments