Latest

በህይወቴ የማልችለው ነገር ቢኖር ማስመሰል ነው!! በመስከረም አበራ

በመስከረም አበራ

በህይወቴ የማልችለው ነገር ቢኖር ማስመሰል ነው፡፡ልቤ ካልሳቀ ጥርሴ ሊስቅ እቸገራለሁ፡፡ልቦናየ ያላለውን በአፌ አውጥቼ ለመናገር አልችልም፡፡ የማይመቼኝ ነገር ውስጥ ለይሉኝታ ብየ መቀመጥ አልችልም፤ደስ ያላለኝ ሰው ጋር አምስት ደቂቃ መቀመጥ ተራራ መግፋት ይመስለኛል፡፡


አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ከዚህ ይለያሉ፡፡ልባቸው በጥቁር የፃፈውን አፋቸው እንደ አመዳይ አንፅቶ ሲያወራ ያጋጥመኛል፡፡ ይህ ነገር ብስለት ነው ምንድን ነው የሚል ነገር ለራሴ አነሳለሁ፡፡ብስለት ከሆነ እኔ በጣም ይቀረኛል ማለት ነው፡፡ "እንዲህ ካልሆነ ፖለቲከኛ መሆን ያስቸግራል፤አንች በቃ ፖለቲከኛ መሆን አትችይም" ያለኝ ሰውም አለ፡፡የማይመቸኝን ሰው፣የማውቀው የታዘብኩት እንከን ያለበትን ሰው የመንቀፍ መብት የለኝም ወይ ምን አዳረቀኝ ብየ ካሰብኩ እንኳን ላመሰግን አልችልምና ዝምታን እመርጣለሁ፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥመኝ ዝም ማለት ውስጥ ያለው ንግግር ጥሩ ይመስለኛል፡፡

የኢህአዴግ ካድሬዎች ደግሞ በዚህ ነገር የተካኑ ናቸው፡፡ በተለያየ አጋጣሚ ያገኘኋቸው የኢህአዴግ ካድሬዎች ቅድም ለብቻችን እያለን ከነገሩኝ ነገር በቀጥታ ተቃራኒ የሆነውን ነገር በመድረክ ላይ ወይም በአለቃ ፊት ሲያወሩ ሳይ አፌን ይዤ እውቃለሁ፡፡ እውን ይህ ብስለት ነው! ብስለት ከሆነ ለምን እንዲህ ያለው ሰው ቀሎ ይታየኛል ብየ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ በበኩሌ ይህን ነገር ብስለት ብየ ለመቀበል ይቸግረኛል፤ ጭራሽ ሽንገላ ይመስለኛል፤እንዲህ ባለ ሁኔታ የሚገለፅ ብስለትም ይቅርብኝ!

ኢህአዴግችን ስታዘብ አብረው የሚኖሩት በሽንገላ ነው፡፡ ለነፍስ እየተፈለለጉ መድረክ ላይ ይሞከሻሻሉ፡፡ግምገማ ላይ ሲራከሱ ውለው ለይምሰል የውሸት ይሳሳቃሉ፡፡ ጠ/ሚ አብይ አህመድ አንድ ቀን የውትድርና ትምህርት ቤት ሄዶ ሳያዉቅ ሙሉ ጄነራል የሆነውን ሳሞራ የኑስን ሲያሞካሽ የሰማሁት ቀን ታዘብኩት፡፡ስሙን ስሰማ አዲስ አበባ አስፋልት ላይ ጭንቅላቱን በጥይት ተበርቅሶ የተደፋ ህፃን የሚታየኝን ወርቅነህ ገበየሁን ሆደ ቡቡ አልቃሻ ነው ሲለን በሽንገላ ጠረጠርኩት፡፡የዛሬው ደግሞ ይባስ!

ሙስናን ከዘረኝነት ደርቦ ዘመዶቹን ከትግራይ አዲስ አበባ አስመጥቶ ዘረፋ ላይ አሰማርቶ፣ግምገማ ሊደረግ ነው ሲባል አፋር ለመስክ ስራ ልኬያቸዋለሁ እንደሚል ኤርሚያስ ለገሰ የነገረንን አውራ ዘራፊውን አርከበ እቁባይን ከመስና እና ዘረፋ ርቆ ለሃገር ደፋ ቀና የሚል ፃዲቅ ነው ሲል አብይ ነገረን፡፡

አርከበ የሸገር ከንቲባ እያለ የከተማዋን መሬት በቀን በብርሃን ለዘረፋ ያሰጣ፣የዘረፋ ቦታውን ሲለቅ በበፊቱ የሹመት ቦታው ለዘረፋ ያሰማራቸውን ሰዎች ጭምር ወደ አዲሱ የሹመት ቦታው የሚያሻግር ዘረኛ ወ ሌባ እንደሆነ ሰው ኤርሚያስ ሲነግረን ሃሰት ነው ብለን እንዳንጠረጥር በፈለጉበት ጊዜ የፈለጉት ሚዲያ ላይ መጥተው ይከራከሩኝ እያለ ነው፡፡ ኤርሚያስ የወያኔዎችን በዘረኝነት የተለወ ሰዘረፋ ሲነግረን ወዲህ ወዲያ የማያስብሉ መረጃዎች(ሰነዶች) ከመፅሃፉ ጋር አያይዞ ነው፡፡

ዛሬ አርከበ ከተመሰገነ ነገ ደም መጣጩ ጌታቸው አሰፋ አታዩትም እንጅ እንደ መልዓክ ክንፍ አለው መባሉ አይቀርም፡፡ አዜብ መስፍንም እንዲሁ ቅድስት ነች፤ በባሏ ደመወዝ የምትኖር ሙስና ባለፈበት የማታልፍ ልንባል እንችላለን፡፡ ይተው ዶ/ር አብይ የማይለቅ ቆሻሻ በአፍ ለማስለቀቅ ሲደክሙ ቆሻሻው እንዳይጋባብዎት፤ሽንገላ የሚጠላ ሰው ደግሞ እንደ እኔ ይታዘብዎታል!

No comments