Latest

የአማራው ሰልፍ መንግስትን አስደንግጧል! አማራው ከዚህም በላይ መንግስትን ማስደንገጥ አለበት! ጌታቸው ሽፈራው

የአማራው ሰልፍ መንግስትን አስደንግጧል!

ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጣ ትልቅ ድጋፍ ከሰጠው መካከል የአማራው ሕዝብ አንዱና ዋነኛው ነው። ይሁንና ሰሞኑን የአማራው ሕዝብ በዶክተር አብይ አህመድ መንግስት ቅሬታ ገብቶታትል።  


ቅሬታውን በሰልፍ ለመግለፅ በተዘጋጀበት ወቅት ዶክተር አብይ አህመድ "የራያን ጉዳይ እየተየወያየንበት ነው" ብሎ አስነገረ። ሚዲያዎች ዘገቡት። በዛሬው ዕለት ደግሞ ወደጣና ብሎም ወደ ላሊበላ አቅንቷል። 

የሰልፉ አላማዎች መካከል ቀዳሚዎቹ የማንነትና የቅርሶች ጉዳይ ናቸው። የማንነቱን (በከፊልም ቢሆን) ትናንት ተወያይተንበታል አለ። ቅርሶቹን ዛሬ ጎብኝቷል።

ዶክተር አብይ አህመድ ጣናንና ላሊበላን ሲጎበኝ እግረ መንገዱን የሄደ ለማስመሰል "የርብ ግድብን ለመጎብኘት" ተብሎ ተገለፀ። ሚዲያዎቹም ከሰልፉ ይልቅ የእሱን ጉብኝት ዘገቡት።
የአማራው ሰልፍ መንግስትን አስደንግጧል!

ይህ በአማራ ክልል ከተሞች የሚደረጉ ሰልፎችን ላይ ይሰማሉ የተባሉ ተቃውሞዎች ያስደነገጠው መንግስት የወሰደው ምክንያትና ስልት ነው። ሰልፎቹ በሚደረጉበት ቀናት፣ በሰልፉ ዋነኛ አጀንዳ ወደሆኑት ጣና እና ላሊበላ መሄድ ሽንፈት ሊበል ሆነ። 

ስለሆነም እግረ መንገዱን የሄደ ለማስመሰል ሞከረ። የእሱን ጉብኝት በደንብ ተዘግቦ የሰልፎቹ በተቻለ መጠን እንዲታለፍ ተደረገ። በብዙዎቹ ሚዲያዎች!

በትናንትናው ዕለት ሰልፎቹ ላይ የሚያዙት መፈክሮች እየታተሙ ፌስቡክ ላይ ሲለቀቁ ያየው መንግስት መልዕክቶቹ ጠንካራና ሕዝብ መንግስት ላይ ተስፋ ማጣቱን የሚያሳዩ መሆናቸውን በመመልከቱ ደንግጧል። ይህ የሆነው የዶክተር አብይን ወደ ስልጣን መምጣት የደገፈው አማራ ክልል ላይ መሆኑ እጅግ አስደንጋጭ ነው።

በእርግጥ ዶክተር አብይ አህመድ እንደነ መለስ ዜናዊ ግብዝ አይደለም። ለስልጣኑ ሲል የተወሰነ ተሸንፎ፣ የተወሰነ ላለመሸነፍ እየጣረ ወደ ሕዝብ ለመቅረብ ይሞክራል። ዛሬ ያደረገውም ይህንኑ ነው። የሰልፉ ዋነኛ አጀንዳ የሆኑትን ከሰልፉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማከናወን ጀመረ። በቃል ደረጃም ቢሆን። 

ነገር ግን የጣናንና የላሊበላን እግረ መንገዱን አስመሰላቸው። በጣም ላለመሸነፍ ነው። የሰልፎቹ ዜና ደብዘዝ ብሎ የእሱ እንዲነገር አደረገ። በሌላ በኩል ደግሞ "እግረ መንገዱን መጎብኘቱም ሰምቶናል" እንዲባል ፈለገ። ሕዝብ የልብ ልብ እንዳይሰማው፣ አስመጣነው እንዳይል፣ በሌላ በኩል ደግሞ እግረ መንገዱንም ሲመጣ አልፎ አልሄደም እንዲባል ፈለገ። ደንግጦ አልደነገጠም ለመባል የሚደረግ ጥረት ነው!

የዶክተር አብይ አህመድ መንግስት ዛሬ ለሚደረጉት ተቃውሞዎች የሰልፉ ዝግጅት ላይ መልዕክቶቹን አይቶ መደንገጡ ጥሩ ነው። ደንግጦ መልስ ለመስጠት መሞከሩ መልካም ነው። ምን አልባትም ከመደረጋቸው በፊት ውጤት ያመጡት የዛሬዎቹ ሰልፎች ናቸው።  
የአማራው ሰልፍ መንግስትን አስደንግጧል!
ምን አልባት ሰልፎቹ ሳይጠናቀቁ ሰልፉ ያተኮረባቸው ጉዳዮች ትኩረት ሲያገኙ ይህ የመጀመርያው ሳይሆን አይቀርም። ቢያንስ በቅርብ ከምናስታውሳቸው መካከል የሰልፉ አጀንዳዎች እንደ አማራው ሰልፍ የመንግስት ባለስልጣናትን በሰልፉ እለት አንከልክለው ሲያስመጡ አላየንም።

በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን ከሰልፍ በኋላ በፌደራል መንግስቱ ትዕዛዝ ግድያና ድብደባ፣ እንዲሁም "ፀረ ሰላም" የሚል መግለጫ እንጅ ሰልፎቹ ከመጠናቀቃቸው በፊት መልስ የሚመስሉ ማሳያዎች ታይተው አያውቁም። በኢህአዴግ ዘመን ከሰልፍ ቀን ቀደም ብሎ የሰልፍ አዘጋጆች ላይ እስር፣ መግለጫ እንጅ "ጥያቄውን አዳምጠናል" የሚመስል ምልክት የታየ አይመስልም።  

በአማራ ከተሞች የተደረጉ ሰልፎች ቀድመው ውጤታማ ሆነዋል። መንግስትን ከልብ አስደንግጠዋል። የድሮው ኢህአዴግ ከመደንገጥ ይልቅ መታበይን ያስቀድም ነበር። እነ አብይ የአማራው ሮሮ አዳፍነውትም ለስልጣናቸው እንደማይጠቅም ስጋት ገብቷቸዋል። መልካም ነው። መደንገጣቸው በበጎነት መታየት አለበት። በዘመናዊነት መታየት አለበት።

ነገር ግን ሴራም አለው። ፖለቲካ ነው። አብይ ነው። ቃልና ታይታ ይበዛዋል። ሰልፎቹ የሚዲያ ሽፋን ሳያገኙ የእሱ ጉብኝት በደንብ እንዲዘገብ ያደረገበት አንዱ ሴራ ነው።

መጎብኘትና እየተወያየንበት ነው ማለት የሰልፎቹ ትልቅ ውጤት ሆኖ ተግባርን ይጠይቃል። የአማራው ጥያቄም ይህ ብቻ አይደለም። አማራው በወጣቶች፣ በሴቶች፣ በሙያ ማህበራት ተደራጅቶ እንቅስቃሴ ቢያደርግ ደግሞ ከዚህ በላይ ማስደገጥ ይችላል። በቃልና በታይታ ሊታለፉ ይችላሉ ተብለው ከሚሰጉት ባሻገር ጥቅሞቹን ማስከበር፣ መብቱን ማስከበር፣ መደመጥ ይችላል። አማራው የሚጠይቀው የተቀማውን እንጅ የሌላን አይደለም።  

ነገር ግን ይህ በተደራጀ መንገድ የተለመደ ባለመሆኑ መንግስትንም ተቃዋሚውንም ማስደንገጥ ጀምሯል። መብትን፣ ርስትን፣ ማንነትን መጠየቅ መብት ነው። ይህ ጥያቄ የሚያስደነግጥና የሚያስፈራ ከሆነ የአማራው ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን እስካሁን የአማራውን ጥያቄ መመለስ ያልጀመረ፣ ማዳመጥ ያልቻለ አገዛዝ አማራው ሲያመር ደምግጦ፣ ገና ከሰልፍ በፊት፣ ሰልፎቹ ሳይጠናቀቁም "እሰማሃለሁ" ማለት ይገባዋል።  
የአማራው ሰልፍ መንግስትን አስደንግጧል!
ምክንያቱም እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ የነበረባቸው ድሮ ድሮ ነበር። ሰልፍ ሳይደረግ፣ ስብሰባ ሳይጠራ። እስካሁን ሰልፍ ሲያደርግ የሚገደለው አማራ ከሰልፉ በፊት የመንግስት ድንጋጤን ማየቱ ግን የድል ምልክት ነው። የመተባበሩ ምልክት ነው። ማሸነፍ፣ መደራደር፣ መከበር የሚችልበት ምዕራፍ ላይ እየደረሰ ስለመሆኑ ምልክት ነው!

አማራው ከዚህ የተሻለ ተደራጅቶ መንግስትን ማስደንገጥ አለበት! ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት እስኪመሰረት በጥፋቱ ሕዝብ "ይቆነጥጠኛል" ብሎ የሚደነግጥን መንግስት በሚሰማበት መንገድ ማናገር ይሻላል! የትኛውም ጥያቄው ያልተመለሰው አማራው ደግሞ ከዚህ ውጭ አማራጭ የለውም።

አብይ ስለደነገጠ ሳይሆን የአማራው መደራጀትና ጥያቄ ለገዥዎች አስደንጋጭ እየሆነ መጥቷል። አማራው ከዚህ መስመሩ ወደኋላ ከተመለሰ አማራጩ መረገጥ ነው። 

የሚገባውን በሚገባው መንገድ መጠየቁን ከቀጠለ ደግሞ ሰልፍ ከመውጣቱም በፊት ገዥዎቹን "እየሰማሁህ ነው፣ እሰማሃለሁ" እንዲሉ ያስገድዳቸዋል። 

አማራጩ ይሄ ነው!

No comments