Latest

ወይ አዲስ አበባ….!

ወይ አዲስ አበባ….!

ታሪክ የሰው ልጆችን ያለፈ የሕይወት ስንክሳር መርምሮ፣ መጭው ትውልድ ካለፈው ድካምም ብርታትም እንዲማርና የተሻለ ዓለም እንዲፈጥር ማስቻልን ያለመ የጥናት መስክ ነው:: የአገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ አተናተን ዘይቤ ክፉኛ በታሪክ ላይ የተጣበቀ ነው:: ፖለቲካችን ታሪክን የሙጥኝ ማለቱ በራሱ ጥፋት የለውም::
 

አስቸጋሪ የሚሆነው ታሪካችንን ለወቅታዊ ፖለቲካችን ትንታኔ በምንጠቀምበት ጊዜ ሥነ ልቦናችንን አብረን ማጋመዳችን ነው:: የአገራችን ፖለቲካ ውቃቤ እንዲርቀው ካደረጉ ነገሮች ዋነኛው ታሪክን እና ፖለቲካን በየግል ሥነ ልቦናችን ለንቅጠን፣ የሥነ ልቦናችን ደመነፍስ ያቀበለንን የስሜት ግንፍላት በምክንያታዊነት ላይ አንግሰን መንጎዳችን ይመስለኛል:: 

ወደስሜታዊነት የሚመራን ፖለቲካዊ ሥነ ልቦናችን ምንጩ ሲመረመር ወይ ዝቅተኝነት የሚያንገላታው የተበድያለሁ እዬዬ ነው ወይ እብሪት የነገሠበት የገዥ ነኝ የበላይነት ስሜት ነው:: የዚህ ፖለቲካዊ ሥነ ልቦና ምንጩ ደግሞ ደመነፍሳዊ ማነብነብን እንደ ሁነኛ የርዕዮተዓለም ትጥቅ ይቆጥር የነበረው የስልሳዎቹ ትውልድ ፖለቲካዊ ሥነ ምኅዳር ነው::
ያ ትውልድ አገሩ ፀንታ ቆማ ዘመን የተሻገረችበትን አገረሰባዊ አዕማድ፣ ፖለቲካዊ መስተጋብር፣ ማኅበራዊ ቁርኝት፣ ኢኮኖሚያዊ ትንቅንቅ ለመመርመር ጊዜ ሳይወስድ በነስታሊን ወጭት የኢትዮጵያን ወጥ ሊወጠውጥ የተነሳ፣ እንደ ቤቱ ሳይሆን እንደ ጎረቤቱ ሊኖር የፋተረ ነበር::
በመሆኑም ኢትዮጵያ ከሶቬት ኅብረት ቀድማና ተለይታ በራሷ የታሪክ ዱካ ከመጓዟ የተነሳ የተሰበዘችበትን ፖለቲካዊ ሰበዝ ልዩ ተፈጥሮ ለመመርመር የማርክስ/ሌኒንን ድርሳን ማነብነቡ ፋታ አልሰጠውም ነበር:: የማነብነብ ቱርፋቱ ዕውቀት የሚያመጣው እርጋታ እና ብስለት አይደለምና ያነብናቢነት ዕውቀት ያቀበለው ዘረኝነት ክፉ እንክርዳድ በአገራችን የፖለቲካ ማሳ ላይ ተዘራ:: 

አገሪቱ  የድሆች እስር ቤት መሆኗ ቀርቶ “የብሔረሰቦች እስር ቤት ነች” ተባለ:: አንድ ብሔር አሳሪ ሌላው ብሔር ታሳሪ ተደርጎ የአጋች ታጋች፣ የበዳይ ተበዳይ ፖለቲካ እንደ ኤርታሌ ድንገት ገንፍሎ ይንተከተክ ያዘ! የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉ የመበደል መበደል ድራማ ብቻ እስኪመስል ድረስ ተበደልኩ ባይ ሙሾ አውራጁ በዛ:: 

አንድ ብሔረሰብ በነሲብ በዳይ ሌላው ብሔረሰብ በጅምላ ተበዳይ ሆኖ የጎሳ ጥላቻ ሰልፍ፣ የመነጣጠል ጎራ፣ የጥርጣሬ መንፈስ በአገራችን የፖለቲካ አየር ረበበ:: ሁሉም የተሰለፈበት የዝቅተኝነት ወይ የበላይነት ፖለቲካዊ ሥነ ልቦና እንደመራው ብድግ ብሎ ፖለቲካን መተንተን ጀመረ::
 

ፖለቲካዊ ስድነት በአገሪቱ ነገሠ! የገዛ አገርን ቅኝ ገዥ ማለት ከአዋቂነት ተጻፈ:: የአገርን ትውፊት ማቃለል ዘመናዊነት ሆነ:: የእነገብረሕይወት ባይከዳኝ ምጡቅ ልቦና ለአገራችን ችግር አገርኛ መንስኤ እና ያ ትውልድ አገሩ ፀንታ ቆማ ዘመን የተሻገረችበትን አገረሰባዊ አዕማድ፣ ፖለቲካዊ መስተጋብር፣ ማኅበራዊ ቁርኝት፣ ኢኮኖሚያዊ ትንቅንቅ ለመመርመር ጊዜ ሳይወስድ በነስታሊን ወጭት የኢትዮጵያን ወጥ ሊወጠውጥ የተነሳ፣ እንደ ቤቱ ሳይሆን እንደ ጎረቤቱ ሊኖር የፋተረ ነበር መፍትሔ የጠቆመበትን ድርሳን ትራስ አድርጎ ተኝቶ የነሌኒንን የጠብ ዶሴ ማገላበጥ፣ ውጭ ውጭውን ማለት የምጡቅነት መለዮ ሆነ:: 

ይህ የማነብነብ ደመነፍስ በጠመንጃ ታግዞ ሥልጣን ላይ ለመውጣት በሚፋትርበት ወቅት ያዋጋ ያጋድል የነበረው ደመ-ጠጭ ዛር በስተመጨረሻ ለሕወሓት ቆሞለት ሥልጣን ላይ ሰየመው:: ሕወሓት ከላይ ከተነሱት ሁለት ፖለቲካዊ ሥነ ልቦናዎች በተበድያለሁ መስመር የተሰለፈ ነበረና የሕወሓት ሥልጣን ላይ መውጣት ለተበድያለሁ ፖለቲከኞች ጥሩ የማላዘኛ መድረክ ፈጠረ:: 

የተበድየ ፖለቲካው ሰልፍ ፊታውራሪዎቹ ኦነግና ሕወሓት ፍቅራቸው ገመሬ እንዳየው ዝንጀሮ ድራሹ እስኪጠፋ ድረስ ሻዕብያን ሙሾ አውራጅ አድርገው በተበድየው ሙዚቃ ደረት ሲደቁ ባጁ! በአንጻሩ የበዳይነት ጦስ የወደቀበት የአማራ ሕዝብ የሚወረወርበትን የወቀሳ ፍላጻ ለመመከት የሚያስችል መድረክ እንኳን ተነፈገው:: በሌለበት የፖለቲካ ችሎት ወንጀለኝነቱ ተረጋግጦ የመገለል ክፉ ፍርድ ተፈረደበት::
 

በአገሩ ሁነኛ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ እንዳይሳተፍ በግልፅም በስውርም እግድ ተጣለበት:: ሽግግር ቻርተር በማርቀቅ ቢሉ ቻርተሩን ሕገ መንግሥት በማድረጉ ሂደት ይህ ነው የሚባልውክልና ተነፈገው:: ያለፈው የአገሪቱ ክፉ ክስተት ሁሉ ተጠያቂ ተደረገ:: ታሪክም አማራውን ጭራቅ አድርጎ ለማሳየት ያስችላል ተብሎ ከተገመተበት ዘመን ይቆጠር ጀመር:: የሉሲ አገር ኢትዮጵያም የመቶ ዓመት ብላቴና ተደርጋ አረፈችው! የሰው ልጆች ያለፈ ሁለንተናዊ የሕይወት ልምድ ታሪክ መባል ያለበት መቼ ነው የሚለው ነገር የሚያከራክረው ከቅርቡ ወደ ሩቁ ሲቆጠር ነው:: 

ታሪክ እንደ ጥናት መስክ የሩቁን ለማጥናት ይጓጓል እንጅ የቅርቡን በአያሌው የሚወስነውን የሩቁን ታሪክ ጥሎ የቅርቡን አንጠልጥሎ አይደናበርም:: የአገራችንን ፖለቲካ ቅጥ አምባር ያሳጣው ይኼው ብዙውን ጥሎ ጥቂቱን አንጠልጥሎ የመንጎዱ የእብድ እሩጫ ነው:: በደንባራ በቅሎ ቃጭል ሲጨመር ደግሞ በዚህ ላይ ስነልቦናችን ታክሎበት መመለሻችንን በሚያስናፍቅ የቁልቁሊት ሩጫ ውስጥ ዶሎናል፤ ላለመደማመጥ አማምሎናል፤ ምክንያታዊነትን ለዘረኝነት አሰውቶ ፖለቲካችንን የሥነ ልቦና ቀውስ በሽተኞች መድረክ አድርጎታል::
 

የፊት አውራሪው ሕወሓት ወደ ሥልጣን መምጣት ገበያ ያደራለት የተበድየ ፖለቲካ በዚሁ ሥነ ልቦና የተጠቁ አባብሉኝ ባይ ፖለቲከኞችን እያፈላ ይገኛል:: ቀደምት የበደል ፖለቲካ ቄሰ-ገበዞች፣ የሕወሓት ባለንጀሮች እነ አቶ ሌንጮ ለታ እና ጓዶቻቸው ከሕወሓትም ተፋተው፣ ዕድሜ ብቻ ያደረጋቸውን፣ እንደስማቸው የሚታወቁበትን የበደል ትረካ ፖለቲካ ጥቅም ጉዳት መዝነው፣ ዛሬ የተለየ መንገድ ይዘናል ቢሉም የዘሩት ዘር ግን እነሱ የተቀየሩ ዕለት የሚቀየር አይደምና በዝቶ ተባዝቶ በቦታው አለ:: 

የነ ሌንጮ ለታ የበደል እየየ ስብከት ዛሬ መምህሩን የሚያስከነዱ የጥላቻ ደቀመዛሙርትን አምርቷል:: በእንዲህ ያለው ደዌ የተለከፉ በአብዛኛው የምሁርነትንም ካባ የደረቡ ልሂቃን የሚደውሩት የከረረ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ፖለቲካ የሕመሙን ክፋት ከሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች አንዱ በቅርቡ የተያዘው የአገራችን ዋና ከተማ አዲስ አበባ የአንድ ብሔር (የኦሮሞ) ተቀዳሚ ንብረት ነች የሚለው ጉዳይ ነው::

የብቻ አዲስ አበባ?

የአዲስ አበባ ቀደምት ነዋሪዎች የኦሮሞዎች ናቸው በሚለው እሳቤ እርግጠኛ ተሁኖ አዲስ አበባም መተዳደር ያለባት በኦሮሚያ ክልል ሥር ነው የሚል ክርክር በቅርቡ ተፋፍሞ ማነጋገሩን ቀጥሏል:: ይኼው የአዲስ አበባ ቀደምት ነዋሪነት እና ተቀዳሚ ባለቤትነት ተረክ ሌሎች የዚሁ እሳቤ ውላጅ የሆኑ መብት ጥያቄዎችን ያስከትላል:: 

በአዲስ አበባ ላይ ሕገ መንግሥታዊ የልዩ ጥቅም ባለመብትነት ጉዳይ፣ የአዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ መገኘት ኦሮሚያን በአዲስ አበባ ላይ የባለቤት ፀዳል ለማላበስ በቂ ሁኔታ ነው የሚሉት ክርክሮች መነሻቸው ይኼው የቀደምት ነዋሪነት ጉዳይ ነው::
 

የኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ላይ ጅኦግራፊያዊ እና ታሪካዊ ባለቤት እንደሆነች የሚወተውተው ክርክር ዋናው መሠረቱ ኦሮሞዎች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ኖሩ የአዳም ዘሮች ናቸው የሚለው ተረክ ነው:: በአዲስ አበባ ላይ የኦሮሞዎችን ቀደምት ነዋሪነት ትርክት ተአማኒ/ኢ-ተአማኒነት ማስረገጥ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ባለው “የባለቤት/ባለ ልዩ መብትነት” ጉዳይ ለሚነሱ ንትርኮች በታሪካዊ መዛግብት የተደገፈ ማስረጃ ሊቀርብ ያስፈልጋል:: በታሪክ ምስክርነት ሳይታገዝ የሚቀርብ የኔነው የኔነው ሽሚያ ያደገን ሰው እንደ ሕፃን ልጅ ሁሉን ነገር ለእኔ የሚያስብል የሥነ ልቦና ቀውስ ምልክት እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም!

“ተው ማነህ ተው ማነህ..”!

ባለፈው ሳምንት OMN በተባለው ቴሌቭዥን የተጋበዙት ፀጋዬ አራርሳ “በ1800 ዓ.ም. መቶ ፐርሰንቱ የአዲስ አበባ ነዋሪ ኦሮሞ ነበረ፤ አሁን ግን በወራሪዎች ግፍ ተገፍቶ ተገፍቶ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውስጥ ዐሥራ ዘጠኝ በመቶው ብቻ ኦሮሞ እንዲሆን ተደርጓል ይላሉ::” የዚህ ክርክራቸውን ታሪካዊ ማስረጃ አብረው አልጠቀሱም::
 

ሆኖም ክርክሩ አዲስ አበባ ሰው ማኖር ስትጀምር ለመጀመሪያ ጊዜ የኖሩባት ኦሮሞዎች ናቸው የሚለውን ተረክ ለማጠናከር የተመዘዘ ሐሳብ እንደሆነ መረዳት አይከብድም:: በ1800 የአዲስ አበባ መቶ ፐርሰንት ነዋሪ ኦሮሞ ብቻ እንደ እንደሆነ ያውም ምሁር በተባለ ሰው አፍ ተሞልቶ ሲነገር ታሳቢ መደረግ ያለበት ነገር ይህን ያህል አስተማምኖ የሚያናግር የሕዝብ ቆጠራ በ1800 ያካሄደው አካል ማን ነው? 

ድሮ ቀርቶ ዛሬ የአገራችን የሕዝብ ቆጠራ የትክክለኝነት ደረጃ እከሌ የእንትን ምድር ባለቤት እንቶኔ ደግሞ መጻተኛ የሚያስብል ነው ወይ? ያኔ ይቅር ዛሬ በኮምፒውተር ዘመን የአገራችን ሕዝብ ቆጠራ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የገባበት ጠፋ የሚባልበት፣ የበዛው አንሶ ያነሰው በዝቶ የሚቀርብበት እንደሆነ በደንብ የምናውቀው የቤታችን ጉድ ነው:: 

ታዲያ በ1800 አዲስ አበባ ላይ የታየ የአዳም ዘር ሁሉ አንድ ሳይቀር ኦሮሞ ነበር ማለት ሊበሉ ያሰቧትን አሞራ ጅግራ የማለት የሥነ ልቦና ቀውስ ካልሆነ ትርጉሙ ምንድን ነው? ደግሞስ እንዴት ባለ ምትሃት ነው በአንድ ምድር ላይ በስህተት እንኳን አንድ ሰው ሳይደባለቅ ኦሮሞ ብቻ ሊሰፍር የሚችለው? እሽ ይሄም በሆነ ምትሃታዊ ኀይል ምክንያት ሆነ እንበልና የ1800 አሰፋፈር የአሁኗን አዲስ አበባ የባለቤትነት መብት ሊወስን የበቃው እንዴት ነው?
 

ዛሬ ላይ ተቁሞ፣ ሁለት ሦስት ምዕተ ዓመት ወደኋላ ተጉዞ፣ የከተማ ባለቤትነትን መብት መወሰን ከተቻለ በዚሁ ስሌት ከዐሥራ ስምንተኛው ምዕተ ዓመትም ወደኋላ መሄድና የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት ሊቻል ነው ማለት ነው:: ከዐሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ወደኋላ ሲኬድ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ቀርቶ መላ ኦሮሚያ ላይም የኦሮሞ ሕዝብ እንዲህ በገፍ አልሰፈረም ነበርና በአሁኗ ኦሮሚያ ላይ ልዩ ጥቅም ሊጠበቅለት የሚገባ ሌላ ቀደምት የመሬት ባለቤት ሕዝብ ፍለጋ መኳተን ሊያስፈልግ ነው:: 

ነፍሱን ይማርና ጋሼ አሰፋ ጫቦ “ተው ማነህ ተው ማነህ የተኛው አለ ትቀሰቅሳለህ” ይል የነበረው እንዲህ ያለውን ነገር ነበር:: ዛሬ ሀብታምነቷ፣ ለምለምነቷ፣ ስፋቷ፣ የሕዝብ ብዛቷ እየተጠቀሰ በአክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች ዘንድ “ዋ! እንዳንገነጠል” ዓይነት ማስፈራሪያነት የምትውለዋ የኦሮሚያ ምድር ከማንም ዘር ጋር አብራ ያልተወለደች፣ ይልቅስ በፊተኛው ዘመን ሌሎችን ሕዝቦችን ይዛ እንደኖረችው ሁሉ ከጊዜ በኋላ ደግሞ በተፈጥሯዊው የሰው ልጆች የመውረር መወረር አይቀሬ ክስተት ኦሮምኛ ተናጋሪ ወገኖችንም ተቀብላ ያስተናገደች ምድር እንደሆነች ታሪክ አገላብጦ ማወቅ ያስፈልጋል::

ታሪክ ምን ይላል?

የመካከለኛውን ዘመን የአገራችን ታሪክ ግልፅ አድርገው ከጻፉ ጸሐፍት አንዱ አቶ ይልማ ደሬሳ ናቸው:: ጸሐፊው “የኢትዮጵያ ታሪክ፤ በዐሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ ለኦሮሞ ሕዝቦች ወደ መሃል እና ሰሜን ኢትዮጵያ የመስፋፋት ታሪክ የመደቡት ገፅ አነስተኛ ቢሆንም በጥሩ ሁኔታ አቅርበውታል:: እግረመንገዴን ይህን መጽሐፍ ያላነበበ አንባቢ ቢያነበው እመክራለሁ::
 
አዲስ አበባ
በያዝነው አጀንዳ ላይ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ግንዛቤ እንዲኖር ስለሚያስፈልግ ሰፋ ተደርጎ የተቀመጠውን ማስረጃ ከሥር መሠረቱ ማቅረብን መርጫለሁ:: አቶ ይልማ የኦሮሞን ሕዝብ የመስፋፋት ታሪክ ሲያስረዱ በምሥራቅ አፍሪካ ከታየበት ዘመን ጀምረው እንዲህ ይተርካሉ::
 

“ኦሮሞዎች ከመቼ ጀምሮ በምስራቅ አፍሪካ መኖር እንደ ጀመሩ፣ እነሱ በዛ ስፍራ ከመስፈራቸው በፊት በቦታው የነበሩ ሰዎች ማንነት በውል ባይታወቅም በዐሥረኛው ክፍለ ዘመን ሶማሌ የተባለው ነገድ ከታጁራ ሰርጥ አቅጣጫ ባነሳባቸው ተግዳሮት የተነሳ ወደ ደቡብ እና ምሥራቅ በመጓዝ በዋቢ ሸበሌና ጁባ ወንዞች መሃከል ቤናዲር በተባለው ስፍራ እና በቆላማው ባሌ ሰፈሩ:: 

ኦሮሞዎች ጥንታዊውን አገራቸውን ለቀው ከቤናዲር በቆላው ባሌ ከሰፈሩ በኋላ የፀጥታ ኑሮ ለማግኘት አልቻሉም:: … ከሰሜን ወደ ደቡብ በተጓዙ ጊዜ በሰፈሩበት አገር በስተ ደቡብ ባንቱ የሚባሉ አርበኛ ነገድ ጎረቤት ሆኗቸው:: ስለዚህ ከሰሜን የሱማሌዎች፣ ከደቡብ ባንቱዎች የሚያደርባቸው ጦርነት ምንም ጊዜ ሰላም የሰጣቸው አይመስልም:: ስለዚህ ከዚህም ከአዲሱ አገራቸው እንደገና መሰደድ ግዴታ ሆነባቸው::

… ጠብ አጫሪ ከሆኑት ከሶማሌዎች እና ከባንቱዎች ለመራቅ ይህ ሰላማዊ የነበረው ሕዝብ ዋቢንና የገናሌን ወንዝ ተከትሎ ወደ ደቡባዊ ኢትዮጵያ ወይናደጋ መሰደድ ጀመረ:: … የኦሮሞ ሕዝብ በስጋ እና በወተት የሚመገብ [አርብቶ አደር] ስለነበረ ድርቅ ከሆነው ከቤናዲር አውራጃ ተጉዞ ወላቡ ወይናደጋ በገባ ጊዜ ይህች ምድር ማርና ወተት ታፈሳለች እንደተባለችው እንደ ምድረ ከነዓን የምትቆጠር ሁና አገኟት:: 

ኦሮሞዎች ወላቡ ብለው የሰየሙት አዲሱ አገራቸው ብዙ ዝናብ የሚዘንብበት፣ ለምለም ምድር በመሆኑ ነድተው ላመጧቸው መንጋዎች ወሰን የሌለው ጦሽ የሚበቅልበት ሆኖ ተገኘ:: በወረዳውም ውስጥ ለሰውና ለከብት ወሰን የሌለው ውኃ የሚገኝበት አገር ነው::… ከአገሪቱ ልምላሜ ሌላ ይህ አውራጃ ጠብ ጫሪ ከሆነው ከሱማሌ ጎሳ፣ ከባንቱዎች ጉርብትና የራቀ በመሆኑ የወላቡ ሰፈር ለኦሮሞ ሕዝብ ምድረ-ገነት ሆኖ በሰላም፣ በምቾት ትዳራቸውን የሚያስፋፉበት ፋታ ሰጣቸው::
 
አዲስ አበባ
ኦሮሞዎች በወላቡ የነበሩበትን ዘመን በማያቋርጥ ናፍቆት በታሪካዊ ግጥማቸው እና ዝሙራቸው መዝግበውታል:: ወደ ደጋው በመሰደድ ምክንያት ከጦረኞች ስለራቁ ወደ ወይና ደጋው ከገቡ ዘመን አንስቶ እስከ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ጦርነት እና ውጊያ አልነካቸውም” (ይልማ ደሬሳ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ገፅ፣ 212-216) ከዚህ ታሪክ የምንረዳው ኦሮሞዎችም እንደማንኛውም ሕዝብ በሰዋዊው የመግፋት መገፋት፣ መወረር መውረር፣ ማሰደድ መሰደድ ማኅበራዊ ሕግ እየተገዙ የሰፈሩ ሕዝቦች እንጁ አሁን ያሉበትን የኦሮሚያ ክልል መሬት ይዘው የተወለዱ ልዩ ፍጡራን እንዳልሆኑ ነው::
 

በምክንያት ለሚያምን ይህ በራሱ ማንም ሰው የሚኖርበት መሬት ባለቤት የመሆን መብት እንዳለው አስረጅ ነው:: ምክንያቱም ያኔ ከቤናዲር መገፋት አብርሮ ያመጣው የኦሮሞ ሕዝብ የሰፈረበት መሬት ባለቤት ሆኖ እየኖረ ነው:: የኦሮሞ ሕዝብ በሰፈረበት መሬት ላይ ባለቤት ሆኖ፣ ከመሬቱ ስባት እያረሰ እያረባ ከኖረ ሌላው ህዝብ የሰፈረበት መሬት ባለቤት የማይሆንበት ምክንያት ምንድን ነው? ኦሮሚያን እንገነጥላለን የሚሉ ፖቲከኞች ደግሞ ጭራሽ የኦሮሞ ሕዝብ በሰፈረበት ለም መሬት ማረስ ማርባቱ ስለማይበቃው መሬቱን ይዞ ይገንጠል ባዮች ናቸው:: 

እነዚህ ሰዎች የመገንጠሉን ነገር ሲያመቻቹ ኦሮሞ ያልሆነ በተለይ ደግሞ ኦሮሚያን ወሮ ያዘ የሚሉት አማራው ከኦሮሚያ ምድር መውጣት እንዳለበት ሲያስገድዱ ሰው ወደ ገደል እስከመወርወር በደረሰ ጭካኔ ነበር:: የዛሬው አዲስ አበባ የኦሮሞ ንብረት ነች ዜማም የዚሁ ምክንያት አልቦ ተረክ ቅጅ ነው::
 

ለራሱ ጎሳ ሲሆን ሰፋሪው ወገን የሰፈረበትን መሬት ሙሉ ባለቤትነት አንሶት መሬቱን ጠቅልሎ ይዞ የመገንጠል መብት እንዳለው የሚከራከር አካል ሌላ ሰፋሪ ለፍቶ ደክሞ ባያቀናው ከተማ ባይትዋር እንዲሆን የሚፈልግ ከሆነ እንዴት መግባባት ይቻላል? ወደ ታሪኩ ስንመለስ ኦሮሞዎች ቀደም ብለው ያደረጉት መስፋፋት መዳወላቡ እንዳደረሳቸው የሚነግሩን አቶ ይልማ ከቤናዲር በረሃ ወደ በመዳወላቦ ምድረ-ገነት መጥቶ የሰፈረው የኦሮሞ ሕዝብ አሁንም መስፋፋትን ግድ የሚል የሕይወት ሕግ ስለገጠመው መስፋፋቱን እንደቀጠለ እንዲህ ከትበዋል፡-

“ኦሮሞዎች ከላይ በተመለከትነው አኳኋን በወላቡ ዙሪያ ብዙ ትወልድ ካሳለፉ በኋላ ከልክ ያለፈ ተራብተው ምድር ጠበባቸው ከደረቁ ቤናዲር ይዘዋቸው ወደ ወይናደጋው ያመጧቸው የቦረና ዘር ላሞች ግጦሽ ከመላበት ከለምለሙ ወይና ደጋ በደረሱ ጊዜ አለመጠን ረቡላቸው:: ስለዚህ ኦሮሞዎች ከወላቡ ከመንቀሳቀሳቸው በፊት በግጦሽም መሬት እንደጠበባቸው አይጠረጠርም::
 

ከዚህ ሌላ በጥንት ዘመን  ከቀድሞ መኖሪያቸው ከአፍሪካ ቀንድ ወግቶ ያስወጣቸው የሶማሌ ሕዝብ ዐሥራ አምስተኛው መቶ ሲጋመስ ከወይናደጋው ድረስ እየመጣ አዲሱን አገራቸውን መውረር ጀመረ:: በዚህ አኳኋን የኦሮሞ ሕዝብ ለመከላከል እና ለግጦሽ የሚፈልገውን መሬት አስፍቶ ለመያዝ ከሰላማዊ አኗኗር ወደ አርበኝነት ሐሳቡን መለሰ::… በዚህ ዘመን ኦሮሞዎች ከረዩ፣ ቱለማ፣ ሜጫ፣ ወሎ በሚባል ትልልቅ ነገድ ተከፍለው ይገኙ ነበር:: 

ስለዚህ ከረዩ የተባለው ነገድ ባሌን ፈጠጋርን ደዋሮን እንዲወር፣ ቱለማ ወደ ሰሜን ተጉዞ ዛሬ የሸዋ ኦሮሞ ምድር የተባለውን እንዲይዝ ሜጫ በስተምዕራብ እና በስተደቡብ የሚገኘውን የኢናሪያዎችን አገር እንዲወስድና ወሎ የተባለው ነገድ በሸዋ በስተምሥራቅ ተጉዞ ከወሎ አውራጃ እስከ ትግሬ ተዘረጋውን አንጎት የተባለውን አውራጃ እንዲይዝ የተቀየሰው ኦዳ ነቤ በነበሩ ጊዜ ነው::
 
አዲስ አበባ
ነገዶቹ ሁሉ ወረራውን በአንድ ጊዜ አለመጀመራቸውን ስንመለከት የጦሩ ስልት የታቀደበትን አኳኋን በማስተዋል ስንመረምር ከወረራው አስቀድሞ ጉዳዩ በስርአት የታሰበበት መሆኑን ልንገነዘብ እንችላለን::” (ገፅ 225-226):: ይህ ታሪክ ወደ ተነሳንበት የአዲስ አበባ ባለ ልዩ ጥቅም ባለመብትነት/ባለቤትነት ጥያቄ ሥረ ነገር ይመራናል::
 

ከላይ ያነበብነው ታሪክ በአፍሪካ ደረጃ ሳይቀር በታላቅነቱ የሚነሳው የኦሮሞ ሕዝብ ወደ ሰሜን መስፋፋት ብዙ ሰው እንደሚያስበው በግብታዊነት የተደረገ የግፋኝ ጉዞ ሳይሆን በወቅቱ በሰፊው ኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የነበሩ ጎሳዎች ተከፋፍለው፣ የቀዳሚ ተከታዩ የጊዜ ምጥነት ተደርጎለት፣ ማን በየት አቅጣጫ እንደሚሄድ በጥንቃ ድልድል የተደረገበት መስፋፋት ነበር::በዚህ ድልድል መሠረት የዚህ ጽሑፍ ሥረ ነገር የሆነው በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ በመሃሉ የከተመችበት የሸዋ ኦሮሞ ክልላዊ ግዛት የተወረረው ቱለማ በተባለው የኦሮሞ ነገድ እንደሆነ ነው ከላይ ይልማ ደሬሳ የከተቡት ታሪካዊ ድርሳን የሚያስረዳው:: 

ሌላው የታሪክ ጸሐፊ ተክለጻዲቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ልብነድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ (ገፅ 94-95) አቶ ይልማ በሰፊው ያቀረቡትን ታሪክ እንዲህ ያጠቃልላሉ፡- “ነገር ግን ኦሮሞዎች እንደ ሱማሌዎች የኢትዮጵያ ሰፊ ግዛት ነው እያልን በምንመካበት በደቡብ ኢትዮጵያ ከብዙ ዘመን ዠምሮ መኖራቸው የታወቀ ነው:: ነገር ግን በየምክንያቱ በመዠመሪያ ጊዜ በጥቂቱ፣ በአፄ ልብነድንግልና በግራኝ መካከል በተደረገው ጦርነት ጊዜ ግን በየነገዳቸው እየተከፈሉ ኦሮሞዎች ቁጥራቸውን አበርክተው ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ማኽል ሸዋ ወደ ዳሞት እና ወደ ጎጃም ወደ በጌ ምድር መግባታቸው የታወቀ ነው::”
 

ስለዚህ የዛሬዋ አዲስ አበባ የተንጣለለችበት ግዛት ከኦሮሞዎች ጋር በመካከለኛው ዘመን (ከ1562 በኋላ) የተዋወቀ እንጅ የዘመናችን አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች አዳም ሲፈጠር በኤደን ገነት እንደተገኘ እንደዛው ሁሉ በአዲስ አበባ ምድር የሰው ፍጡር ሲታይ ቀድሞ የታየው ኦሮሞ ነው እንደሚሉት ዓይነት አይደለም! እንዲህ ታሪክ ተድበስብሶ ነው እንደግዲህ አዲስ አበባ ለኦሮሞ ቤት ለሌላው የሰው ቤት ነች እየተባለ አስተዛዛቢ ሙግት እየተነገረ ያለው:: 

አዲስ አበባ የኦሮሞ ንብረት በመሆኗ እንደ ማንኛውም በኦሮሚያ ክልል እንደሚገኝ ከተማ ትተዳደር የሚለው ክርክር በአስረጅነት የሚጠቅሰው በታሪክ በውል ያልተደገፈው የኦሮሞ ሕዝብ ቀደምት የአዲስ አበባ ነዋሪነት ታሪካዊ መብት አለው የሚለው ተረክ ከላይ በተጠቀሰው፣ ሸዋ ራሷ መቼ እና እንዴት በኦሮሞዎች እንደተያዘች በሚያስረዳው ታሪካዊ ማስረጃ ከእውነት የራቀ እንደሆነ አይተናል::
 

ሆኖም ለግራቀኙ ክርክር ንፅፅር እና ፍርድ እንዲመች አዲስ አበባ የኦሮሞ ቀደምት ቤት ነች የሚሉ ወገኖችን ማስረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል:: አስረጅ ሲያቀርቡ ያጋጠመኝ የዚህ ክርክር ባለቤቶች “በ18ኛው ክፍለ ዘመን የአዲስ አበባ ነዋሪ ሁሉ መቶ ፐርሰንት ኦሮሞ ነበር” የሚል ከላይ የተጠቀሰው የፀጋዬ አራርሳ ገራሚ ክርክር ሲሆን ሌላው ዶ/ር ነጋሶ ሐምሌ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ከወጣው የአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ታሪክ ጠቅሰው ያቀረቡት ክርክር ነው:: 

ዶ/ር ነጋሶ ጋዜጠኛው “የአዲስ አበባ እና ኦሮሞዎች በታሪክ ያላቸው ግንኙነት መቼ ነው የሚጀምረው?” ለሚለው ጥሩ ጥያቄ የመለሱት መልስ በአፄ ምኒልክ አባት እና አያት ዙሪያ የሚያጠነጥን፣ የተለመደው ታሪክን ከወገቡ የሚጀምር የኦሮሞ እና የትግራይ ብሔርተኞች (ኦነግ እና ሕወሓት) ውሸትን ደጋግሞ እውነት የማስመሰል፣ ከምክንያታዊነቱ ይልቅ ማደናቆሩ የበዛ የብልጣብልጥነት መልስ ነው::
 

ብዙ የሚዞረው የዶ/ር ነጋሶ መልስ ነጥብ ያለው እንዲህ በሚለው ማሳረጊያው ላይ ነው “….አፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥታቸውን አሁን ወዳለበት ያመጡት ለፍል ውኃ ቅርብ ለመሆን ነው፤ እንጅ ቦታው ላይ ኦሮሞዎች በ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምረው ይኖሩበት ነበር:: … ቦታውን ምኒልክ ሲይዙት ብዙ የጎሳ መሪዎች ተገድለዋል:: ጎሳ መሪዎቹ ተገድለው መሬታቸው ለቤተ መንግሥት ሰዎች፣ ለውጭ አገር ዲፕሎማቶች ነው የተከፋፈለው:: 

በሕይወት የተረፉት ሸሽተዋል:: ሆን ተብሎ በማፈናቀልም ወደ አርሲ፣ ባሌ፣ አካባቢ እንዲሰፍሩ የተደረጉ አሉ:: ባሕሉና ቋንቋውም በክርስትና መስፋፋት ጠፍቷል::” የዶ/ር ነጋሶ መልስ ከላይ ለተነሳው የቀደምትነት ጥያቄ ልከኛ ማስረጃ የሚሆነው ዓለም የተፈጠረው፣ታሪክ የተቆጠረው ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ቢሆን ነበር::
 

እውነታው ግን ያ አይደለም! አፄ ምኒልክ ፍውኃውን ከጓሯቸው ለማድረግ፣ ለባሕር ማዶ ወዳጅ አገራት ኢምባሲ ለመሥራት የአገሬውን ሰው አፈናቅለው ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን እነዚህ ተፈናቀሉ የሚባሉ ሰዎች ኦሮሞዎች ብቻ ስለመሆናቸው ምን ማስረጃ ይቀርባል? የተፈናቀሉት ሰዎች ኦሮሞዎች ብቻ ነበሩ የሚለውን ብንቀበልስ ለመላው አዲስ አበባ 2ኛ ዓመት ቁጥር 15ሐሳብ የኦሮሞ ቀደምት ርስትነት ማስረገጫ በምኒልክ ዘመን በፍል ውኃ አካባቢ ኦሮሞዎች የነበሩ መሆናቸው እና በምኒልክ መፈናቀላቸውን ብቻ ማስረጃ አድርጎ ማረብ ማንን ያጠግባል? ዶ/ር ነጋሶ ሲቀጥሉ 

“… ሰሜን ሸዋ አሁን ላሎ ተብሎ ሚጠራው አካባቢ ለአዲስ አበባ እጅጉን ቅርብ ነው፤ ስለዚህ አዲስ አበባ አካባቢ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኦሮሞዎች እንደ ነበሩ የሚታወቅ ነው ማለት ነው::” ዶ/ር ነጋሶ በሰሜን ሸዋ አካባቢ ላሎ የሚባል ቦታ ላይ ኦሮሞዎች ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ መኖራቸው በምን ስሌት አዲስ አበባን የኦሮሞ ንብረት ያደርጋታል ብለው እንዳሰቡ ለኔ ግራ ነው::
 

ኦሮሞዎች ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምረው የአሁኑን የሸዋ ኦሮሞን ግዛት እንደያዙ ታሪክም ከዶ/ር ነጋሶ ሐሳብ ጋር ይስማማል:: እዚህ ላይመነሳት ያለበት ጥያቄ ግን 16ኛው ክፍለ ዘመን የዘመን ጅማሬ አይደለምና በዚህ ሰዓት የወረረ አካል የአገር ብቸኛ ባለቤት ነው ከተባለ ከዚያ በፊት በቦታው የነበሩ የሰው ዘሮች ባለቤት የማይሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው ነው:: 

ለዚህ ክርክር አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ፖለቲከኞች ሲያነሱ የሚያጋጥመኝ መልስ ኦሮሞ በሚስፋፋበት ዘመን የሚይዘው መሬት ሰው ያልሰፈረበት ምድረበዳ እንደሆነ ነው:: ይሄም የሚያስኬድ አይደለም:: የታሪክ መዛግብትን እንፈትሽ:: የኦሮሞን ታሪክ የጻፉ ሌላው ጸሐፊ አለቃ አፅሜ “የኦሮሞ ታሪክ ክፍል አንድ” በሚለው መጽሐፋቸው (ገፅ 171) ላይ ይህን ጽፈዋል፡–
 

“…ኦሮሞ አማራን አባሮ ፈጅቶ፣ኢትዮጵያን ከትግሬ በቀር ወረሳት::” ይህ ማስረጃ እኛ ከምናውቀው አባራሪ ተባራሪ ምድብ ያፈነገጠ፤ አባራሪን (ኦሮሞ) ተባራሪን (አማራ) አድርጎ የዘመናችን ፖለቲካ በደመነፍስ ያስቀመጠውን የበዳይ ተበዳይ ድልድልን ያቀያየረ ነው:: ታሪክን ከወገቡ ጎምዶ የሚያቀርበው ወቅታዊ ፖለቲካችን የአገራችን ብቸኛ ወራሪ አማራ የዘወትር ተባራሪ ደግሞ ኦሮሞን አድርጎ ያቀርባል::
 

ከጎማዳው ታሪክ እልፍ ሲሉ ያለው እውነታ ግን ሌላ ነው:: የኑሮ ስንክሳር፣ የኀይል ሚዛን እንዲያባርር ያስገደደው ሁሉ ያባርራል፣ ያፈናቅላል::ሁሉም መውረር መወረር፤ መስማማት መጣላት የኢኮኖሚ ጥያቄ፣ የኀይል ሚዛን ጉዳይ ነው! ባለበት ተገትሮ የሚቀር ነገር የለምና አባራሪም የተባራሪነት እጣ ይገጥመዋል:: በዚህ ውስጥ ጎሳዊ ቅድስናው ተባራሪ፣ ጎጣዊ እርኩስነቱ አባራሪ የሚያደርገው የሰው ልጅ የለም:: 

ስለዚህ ሁኔታ አለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ በፃፉት እና ዶ/ር ሥርግው ገላው አርትኦት በሠሩበት “የኢትዮጵያ ታሪክ” የሚል ርዕስ ባለው መጽሐፍ (ገፅ 156) ላይ ይህን ጽፈዋል፡- “… ያን ጊዜ አማራ እና ኦሮሞ ሞጋሳ ተባብለው ቃል ኪዳን ተገባቡ:: አማራ እና ኦሮሞ ከዚያ ወዲህ ተደባለቀ::
 
አዲስ አበባ
ያን ጊዜም ለሚመጣው ለኋለኛው ዘመን ንግር ተነገረ:: ንግሩም እንዲህነው:: ኦሮሞ አማራን እያሳደደ ግቤን ወንዝ ባሻገረው በአማራ በዘጠነኛው በኦሮሞ በዐሥረኛው ትውልድ ሲሆን ግፍ ብድር አይቀርምና ፈንታውን አማራ ኦሮሞን 2ኛ ዓመት ቁጥር 15 ያሳድደዋል ተብሎ ተነገረ:: ይህም ንግር ጊዜው በደረሰበት ላይ በኋላ ይጻፋል”:: ለማከል ያህል ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ “የአባ ባሕርይ ድርሰቶች” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ (ገፅ 123) እንዲህ ይላሉ፡-
 

“ኦሮሞዎች ወደ መሃል ኢትዮጵያ ገብተው የያዙት አገር ግራኝ ባዶ ያደረገውን ነው የሚሉትን የዛሬ ኦሮሞ ታሪክ ጸሐፊዎችን የአባ ባሕርይ ጥናት አይደግፈውም:: ኦሮሞዎች አገር ሲወሩ ነባሩን ሕዝብ እያጠፉና ኦሮሞ እያደረጉ ነበር…” አባ ባሕርይ ለዚህ ያቀረቡትን ነባራዊ አስረጅ እዚህ ለመጻፍ ስለማልችል አንባቢዎቼ መለስ ብለው እንዲያነቡ እመክራለሁ:: 

ከላይ የተጠቃቀሱት ታሪካዊ ማስረጃዎች በኦሮሞዎች መስፋፋት ወቅት በአገራችን የነበረውን አጠቃላዩን ነባራዊ ሁኔታ የሚያስረዱ ናቸው:: የዚህ ጽሑፍ ዋና ጉዳይ የሆነው የአዲስ አበባ እና የኦሮሞ ሕዝብ ታሪካዊ መስተጋብርን ከዚህ ከትልቁ ምስል የማይወጣ በመሆኑ አንባቢ ከትልቁ ምስል አንጻር ደግሞ እንዲያየው በማሰብ ያመጣሁት ነው:: የአጠቃላይ ነገሩን ማስረጃ እዚህ ላይ ልግታና የጽሑፉ ልብ የሆነው አዲስ አበባ የምትገኝበት የአሁኑ የሸዋ ኦሮሞ ግዛት በ16 ክፍለ ዘመን ኦሮሞዎች ሲወረር ባዶ መሬት ነበር/አልነበረም የሚለውን ወደመመርመሩ እንለፍ::
 

የአቶ ይልማ ደሬሳን መጽሐፍ (ገፅ 245) እንመልከት፡- “በ1562 ዓ.ም. የሐንሩፋ ገዳ 8 ዓመት ተፈፅሞ ከአርባ ዓመት በፊት በሙዳና ገዳ ጊዜ ቡታ ያረደው ትውልድ ልጆች ባለገዳ ለመሆን ደረሱ:: ቡታ ባረዱም ጊዜ ገዳውን ሮበሌ ብለው ሰየሙት:: በዚህ በሮበሌ ገዳ ጊዜ ትልቅ ዘመቻ ያደረገው የቱለማ ጎሳ ነው፤ እላይ እንደተመለከትነው ሁሉ ከረዩዎች ወደ ምሥራቅ፣ መጫዎች ወደ ምዕራብ፣ ወሎዎች ወደ ምሥራቅ ሰሜን መጓዛቸውን ስናትት ቱለማዎችን ኦዳ ነቤ ላይ ተውናቸው:: 

በ1562 ዓ.ም. ቱለማዎች ከኦዳ ነቤ ዙሪያ ተነስተው ሸዋን ለመውረር በተጓዙ ጊዜ በአዝማች ዘረ ዮሃንስ የተመራ የንጉሠ ነገሥት ጦር መንገድ ላይ ጠብቆ ገጠማቸው:: ከጦርነቱም ላይ አዝማች ዘረ ዮሐንስ ሞቱ፤ ሠራዊቱም ተሸነፈ:: በዚያን ጊዜ ሮበሌ ባለገዳዎች የሸዋና የጎጃም መንገድ እንደተከፈተላቸው ቆጥረው በግስጋሴ ወደ ፊት ተራምደው ዛሬ የሸዋ ኦሮሞ ምድር ከተባለው አገር ላይ ሰፈሩ::” ከዚህ የምንረዳው ቀላሉ ነገር ኦሮሞዎች የአሁኑን የሸዋ ኦሮሞ ግዛት ሲወሩ በቦታው ሌሎች ሰፋሪ ሕዝቦች እንደነበሩ ነው::
 

ሕዝቦቹ ገዥ ንጉሠ ነገሥት የነበራቸው ነገር ግን የኦሮሞዎቹ ጉልበት ስለጠናበት ወረራውን መቋቋ የተሳነው በመሆኑ ሳይወድ በግድ መወረሩን የተቀበለ እንደሆነም እንረዳለን:: ይህ የመውረር መወረር ክስተት ያለ እና የነበረ በመሆኑ በታሪክ ሁነትነቱ ከመቀበል ሌላ ትርጉም ያለው ነገር የለም:: ኦሮሞዎቹ በሸዋ ምድር ከመስፈራቸው በፊት የነበሩ ሕዝቦችን ማንነት የማፈላለግ ሥራ ፈት ጥያቄ አንስቼ፣ የአዲስ አበባ ባለቤቶች ኦሮሞዎች ሳይሆኑ ከነሱ በፊት በንጉሥ እንቶኔ ሲመሩ የነበሩት የእንትን ጎሳ ሰዎች ናቸው የሚል አዋጭ ያልሆነ ክርክር ውስጥ መግባት አልፈልግምና የታሪክ መዛግብት ምርመራየን እዚህ ላይ ልግታና እስካሁን ያየናቸው የታሪክ መዛግብት የሚያቀብሉን መረጃ ከወቅታዊው የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ጋር ያለውን መስተጋብር ላንሳ::
 

ይኼን ሁሉ ያነጋገረን ጉዳይ አዲስ አበባ በታሪክ ቀደምት ነዋሪዎቿ ናቸው የተባሉት የኦሮሞዎች ንብረት መሆን እንዳለባት የሚነሳው ክርክር ነው:: ይህ በታሪክ መነፅር ሲፈተሸ ኦሮሞዎች እና አዲስ አበባ የምትገኝበት ሸዋ የተዋወቁት በ1562፣ ኦሮሞዎች ቀድሟቸው በአካባቢው ተገኝቶ፣ አገዛዝ መሥርቶ የነበረን የንጉሠ ነገሥት ጦር አሸንፈው አካባቢውን በመውረራቸው ሳቢያ እንደሆነ አረጋግጠናል:: ስለዚህ ኦሮሞ የአዲስ አበባ ቀደምት ነዋሪ ነው በሚለው ከእውነት የራቀ ክርክር ላይ ተቁሞ የሚነሳው ኦሮሞ ሕዝብ የበለጠ የአዲስ አበባ ባለቤትነት መብት ይከበርለት የሚለው ጥያቄ የማያስኬድ ነው ማለት ነው::
 

በነገራችን ላይ በግሌ የቀደምት ነዋሪነት ክርክር ራሱ ሳይንሳዊ አይመስለኝም:: ምክንያቱም ቀደምት የምንለው ታሪክ ራሱ ሌላ ቀደምት አለውና ዘመንን ከሚመች ቦታ ጀምሮ ቆጥሮ እኔ ቀደምት ነኝ የሚለው ክርክር ትርጉም የማይሰጥ ነው:: የሆነው ሆኖ የቀደምትነቱ ጨዋታ ቀደምትነትን ከሚመቻቸው ቦታ ለሚቆጥሩ አካላት ሌላ የቀደምትነት አቅርቦት ስላለው እዳው ገብስ ነው:: 

ከባዱ ነገር የቀደምትነት የታሪክ ልቃቂት ሲጎለጎል፣ የታሪክ ሐቅ ከፈለጉት ቦታ አንስቶ ወዳልፈለጉት ቦታ ሲያስቀምጥም የቀደምትነቱን ዜማ እንደያዙ መቆየቱ ነው:: አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች የቀደምትነት ውሽልሽል ክርክራቸው ላይ ተመሥርተው የአዲስ አበባ ባለቤትነትን ጥያቄ ሲያነሱ የሚወክሉት የራሳቸውን ስስታምነት እና የሥነ ልቦና ቀውስ እንጅ በጉዲፈቻ ላሳደገው ልጅ ሀብት ንብረቱን ከወለደው ልጅ እኩል የሚያካፍለውን የኦሮሞ ሕዝብ ሥነ ልቦና አይመስለኝም::
 

እነዚህ ፖለቲከኞች ቀደምት ነዋሪነትን ጠቅሰው የአዲስ አበባ ባለቤትነት ይገባናል ካሉ ከአዲስ አበባ ቀድመው መጠየቅ ያለባቸው ታሪክ ሲገለጥ የኦሮሞ ሕዝብ ከአዲስ አበባም ከመዳወላቡም ቀድሞ ይኖርበት የነበረውን በረሃማውን የቤናዲርን ግዛት ነው:: ይህን ግን አያደርጉም:: ምክንያቱም ያልሆነውን የቀደምትነት ጥያቄ ያስነሳቸው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የለፋበት የአዲስ አበባ ወቅታዊ መንቆጥቆጥ እንጅ እነሱ የሚሉት፣ ታሪክ ግን የማያውቀው የቀደምትነትን ነገር አይደለም::

ማስታወሻ
ይህንን ጽሁፍ ከአንድ ድህረገጽ ላይ ካገኘሁት ትንሽ ቆየት ብሏል:: አሁን ወቅቱ ይህንን ጽሁፍ ለማውጣት ስላስገደደኝ ምንጭ ለመጥቀስ ያገኘሁበትን ድህረገጽ ሆነ የጸሃፊውን ስም ስለዘነጋሁት የጽሁፉን ባለቤት ከልብ ይቅርታ እጠይቃለው::

No comments