የአዲሳባ ወጣትና ቄሮ! «ዘውድአለም ታደሠ»
አሁን አሁን ፌስቡክ ላይ ሎግኢን ብዬ ስገባ መፍራት ጀምሪያለሁ። እኛ አዲስ አበባ ቁጭ ብለን ያላየነውን ነገር የምንሰማው ውጭ ሐገር ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች ሆኗል። ዛሬ ራሱ ከቤቴ ለመውጣት ፈልጌ ካሊፎርኒያ የምትኖር ጓደኛዬ ጋር ደውልኩና «ሰፈራችን ሰላም ነው ወይ?» ብዬ መረጃ ጠየቅኋት።
«ነክር ሱቅ ጋር ሁለት ኦራል ቆሟል። ግን ሰው እየነኩ አይደለም መውጣት ትችላለህ» ስትለኝ ወጣሁ።
ለረጅም ሰአት ፌስቡክ ላይ ስለቆየሁ ከቤቴ ስወጣ የሆነ ተባራሪ ጥይት ግምባሬን ብሎ ሚያሰናብተኝ ሁሉ መስሎኝ ተሸብሬ ነበር። ከኛ ግቢ ራቅ ብለው የሰፈራችን ወጣቶች የመስቀልን በአል ለማክበር አካባቢውን በባንዲራ እያስጌጡት ሽር ጉድ ይላሉ። (ባይ ዘ ዌይ ከመስቀል አደባባይ ቀጥሎ የመስቀልን በአል በደመቀ ሁኔታ ሚከበረው እኛ ሰፈር ነው)
ነክር ሱቅ ጋር ስደርስ ሁለቱን ኦራሎች በአይኔ ፈለግኳቸው። ኦራሎቹ የሉም። ነገር ግን ሁለት አሮጌ የሽንትቤት መጣጭ መኪኖች ቆመዋል። የካሊፎርኒያዋ ወዳጄን ብነግራት «ኦህ ማይ ጎሽ ..መንግስት አፈሳው አልበቃ ሲለው ያዲሳባን ልጅ ሊመጠው ነው ማለት ነው» ብላ ይበልጥ እንደምታስቦካኝ እርግጠኛ ነኝ።
ወደአስፓልት ወጥቼ አንዷ ካፌ በረንዳ ላይ ተቀመጥኩ። ውስጤ ካሁን አሁን አፈሱኝ በሚል ፍርሃት እንደተሸበረ ነው። ማኪያቶዬን እየተጎነጨሁ ጎዳናውን ስቃኝ ከሩቅ ግድንግድ ዱላ የያዙ ባለባርኔታ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ሲመጡ ተመለከትኩ ...
ጭንቅላቴ ላይ «ቄሮ» የሚል ድምፅ አቃጨለብኝ። ቲሽ ተበላሁ አልኩ። እንደተቀመጥኩ ብሔሬን ለማስታወስ ሞከርኩ። ወላጆቼ ቁቤ ስላላስተማሩኝ ተፀፀትኩ። ልሩጥ አልሩጥ እያልኩ ከራሴ ጋር ስማከር ሰዎቹ ካፌዋን ከበው ይጨፍሩ ጀመር። ነገር አለሙ ተምታታብኝ። ዱላቸውን እየተደገፉ ወደላይ እየዘለሉ በእጃቸው የያዙትን እርጥብ ሳር በረንዳው ላይ እየበተኑ ካፌዋን በጭፈራ አደመቋት። (አይ ፌስቡክ ጉድ ሰራኝኮ)
ካፌዋ ውስጥ ያለው ሰው በሙሉ እየሳቀና ከኪሱ ብር እያወጣ ሰጣቸው። እነዚህ የተቀደሱ ሰዎች ምርቃታቸውን አዥጎድጉደውት እየጨፈሩ ጉዟቸውን ቀጠሉ። ሁሉም ወጣቶች ነበሩ። በኦሮሚኛ አጠራር ደግሞ «ቄሮ» ይባላሉ። ሰሞኑን ቄሮ እየተባለ በጅምላ እንደጭራቅ የተዘመተው እንግዴ እነዚህ ምስኪኖች ላይ ነው።
ባለፈው አዲሳባ ለመጡት ቄሮዎች ምግብና ውሃ ያቀረብን ቀን የተዋወቅሁት የአምቦው ቄሮ ጀማል ዳውድ ዛሬ ደውሎልኝ ነበር። ጥቂት ካወራን በኋላ ስለህይወቱ አጫወተኝ። አንደበቱ ይጣፍጣል። ንግግሩ ውስጥ ቅንነቱ በጉልህ ይታያል። የኦሮሚያ ቄሮ ከታጣቂው ሃይል ጋር የሞት ሽረት ትግል በሚያደርግበት ወቅት የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን አቋርጦ ለነፃነቱ እንደተፋለመ ነገረኝ።
ለአዲስአበባ ሰው ያለውን ፍቅርና አክብሮት ገልፆልኝ ወደፊት ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈፀም ቄሮ ከአዲስ አበባ ወጣት ጋር በጋራ ቢሰራ ጥሩ እንደሆነ አወራን። ቄሮን በሙሉ በኮመንሴንስ የሚመራ ማገናዘብ የማይችል አርጎ የሚያስብ ሰው ይሄን የቄሮ ወጣት ቢያየው ደስ ይለኝ ነበር። እርጋታ ጨዋነቱና ስለፖለቲካ ያለው ንቃት አስገራሚ ነው።
ቡራዩ ስለተፈጠረው ነገር ማዘኑን በዚያ በሚጣፍጥ ቋንቋው አውርቶኝ የተፈጠረው ነገር በምንም ተአምር ለነፃነቱ ሲዋደቅ በኖረው እውነተኛ ቄሮ አንዳልተፈፀመ እርግጠኛ ሆኖ አወጋኝ። ለጃዋር ያለውን ፍቅርም ገልፆልኝ ጃዋር ለአመታት ለቄሮዎቹ ብሔር ለይተው ማንንም እንዳያጠቁ ደጋግሞ ሲያስጠነቅቃቸው እንደከረመ አጫወተኝ።
የሸገር ልጅ ሆይ! ቄሮ ማለት ሚሊየን ወጣት ነው። በኦሮሞ ባህልና ስነምግባር ተኮትኩቶ ያደገ ታሪካዊ ትውልድ! ቄሮ ማለት አንባገነኑን ስርአት በድፍረት ወጥቶ ከላዩ ላይ ያንከባለለ የባልቻ ሳፎ የመንፈስ ልጅ ነው። ቄሮ ማለት የአብዲሳ አጋ ደም ያለበት፣ የማሞ መዘምርና የታደሰ ብሩ ወኔ ወራሽ፣ ኢትዮጵያ ስትነካ ፈረሳቸውን ቼ ብለው አድዋ የዘመቱ የነኛ ሃያላን የኦሮሞ ጀግኖች ፍሬ ነው። ቄሮ ማለት ጣሊያንን በአፍላ እድሜው መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣው የአብቹ አብራክ ክፋይ ነው። ቄሮ ማለት ጭቆናን እንቢኝ ብሎ ነፍሱን ለሐገሩ የሰጠ ታሪካዊ ትውልድ ነው!
ሰብሰብ ብሎ ንፁሃንን የገደለና የጨፈጨፈ ወንበዴ በፍፁም ይሄን ድንቅ ትውልድ ሊወክለው አይችልም።
ሸገር ሆይ አድምጠኝ ..... ቄሮ እንኳን አሁን ያኔ በኢህአዴግ ጥይት ሲረግፍ እንኳ በኦሮሚያ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ሰዎችን ነክቶ አያውቅም። ቄሮ በሁሉም የኦሮሚያ ክልል አለ። እልፍ አእላፍ ነው። አዲሳባን በአራቱም አቅጣጫ በሚያዋስኗት የኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ በሙሉ ይሄ ጀግና ትውልድ አለ።
ቄሮ ብሔር ለይቶ የመግደል እርካሽ አላማ ቢኖረው ታዲያ የቡራዩን አይነት ተመሳሳይ ወንጀል ለምን ከሌሎቹ አቅጣጮች አንሰማም? የቡራዩ ወንጀለኞች በቄሮ እዝ ስር የሚመሩ ከሆኑስ አሰላና ዱከም ላይ ላይ ተመሳሳይ ወንጀል ሊፈፅሙ ከወጡ ወንጀለኞች ጋር ተፋልሞ ንፁሃንን ወገኖቹን የታደገውስ ማን ነው?
ቄሮም ሆነ በኦሮሞ ስም የተደራጀ ሃይል የአዲሳባን ህዝብ ለማጥቃት ይፈልጋል ማለት የማይመስል ነገር ነው ጓድ! አዲስ አበባ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ከኦሮሞ ወላጆች የሚወለድ ግን ኦሮሚኛ መናገርም ሆነ መፃፍ የማይችል ህዝብ ሞልቷል። ታዲያ ማን ነው ማንን ሚያጠቃው?
ስማኝ የሸገር ህዝብ .... ኦሮሞ አቃፊ፣ ኦሮሞ የሰለጠኑት አለማት በቀለምና በዘር በተከፋፈሉበት ዘመን በሞጋሳና በጉዲፈቻ ራሱን ከሌላው ብሔር ጋር ሲቀላቅል የኖረ።
አንድ ሰው ኦሮሞ መሆን ከፈለገ ብሔርና ጎሳውን ሳይጠይቅ ኦሮሞ አርጎ ሲቀበል የኖረ ፣ አለም የመሰከረችለትን የገዳ ስርአት ገንብቶ ለአለም ያስተዋወቀ፣ አለም የሰው ልጆችን መብት ከማክበሩ አስቀድሞ አውሬ ተጠምቶ ከመጣ ከነጥማቱ እንዳይመለስ በማሰብ የትኛውም ኦሮሞ ደጁን ከመዝጋቱ በፊት ንፁህ ውሃ በሩ ላይ እንዲያስቀምጥ የሚያዝ ከሰብአዊነት ያለፈ ህግ በገዳ ስርአቱ ውስጥ ያኖረ፣ ለእንግዶቹ ያለስስት ወተትና ቅቤውን የሚያቀርብ፣ ወይፈንና ጤፉን ተሸክሞ አዲሳባ ያሉ ዘመዶቹን ሊጠይቅ በፀሃይ እየተንቃቃ የሚመጣ፣ ቅንና ደግ ህዝብ ነው።
ቄሮ ከዚህ ጀግናና ትሁት ህዝብ መሃል የፈለቀ ትውልድ ነው። ፌስቡክ ላይ በጥላቻ ሰክረው ብሔር እየለዩ ሲሳደቡና ሲራገሙ የሚውሉትን አንዳንድ ሰዎች እያዩ አንድን ህዝብ በነሱ ጫማ መለካት በምንም ሚዛን ልክ ሊሆን አይችልም።
ቄሮ ከዚህ ጀግናና ትሁት ህዝብ መሃል የፈለቀ ትውልድ ነው። ፌስቡክ ላይ በጥላቻ ሰክረው ብሔር እየለዩ ሲሳደቡና ሲራገሙ የሚውሉትን አንዳንድ ሰዎች እያዩ አንድን ህዝብ በነሱ ጫማ መለካት በምንም ሚዛን ልክ ሊሆን አይችልም።
በየማህበራዊ ሚዲያው ከሁሉም ብሔር የተውጣጣውን የአዲሳባን ህዝብ ከዚህ ድንቅ ህዝብ ጋር ሊያላትሙ በሚፈልጉ ረባሾችም መሸበር የኦሮሞን ባህልና እሴት አለማወቅ ነው።
ስለዚህ ባለፈው የተፈጠረው ትርጉም የሌለው ሰጥአገባ ዳግም እንዳይከሰት የአዲስ አበባ ወጣትና ቄሮ ነገ ማየት ለሚናፍቃት ሐገር በጋራ መስራት አለበት! እኔ ሚባል ነገር የለም። ሁላችንም «እኛ» ነን! ለዚህ ነው ቡድን እየለዩ ሊያባሉን የሚሞክሩ ሟርተኞችን ወግዱልን ማለት ያለብን!
No comments