‹‹አማኝ የሌላውን እምነት ያከብራል፡፡›› የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሙስሊም ማኅበረሰብ አባላት
ባሕር ዳር፡ መስከረም 15/2011 ዓ.ም (አብመድ) በጎንደር ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በጎ ፈቃደኞች የመስቀል በዓል የሚከበርባቸውን አካባቢዎች እያጸዱ ነው፡፡
የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮቹ የመስቀል በዓል ዕለት ደመራ የሚለኮስበትንና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የሚያከብሩበትን የጎንደር መስቀል አደባባይ በዛሬው ዕለት እያጸዱ ነው፡፡
የጽዳት ዘመቻቸውን ንጋት 12፡00 የጀመሩ ሲሆን በመስቀል አደባባይ አካባቢ የነበሩ ቆሻሻዎችን አጽድተዋል፤ የግንባታ ቁሳቁሶችንም አንስተዋል፡፡
በጎንደር ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ከዚህ ቀደም የኢድ-አልአድሃ አረፋ በዓል ከመከበሩ አስቀድሞ በዓሉ የሚከበርበትን አካባቢ አጽድተው ነበር፡፡
በጎንደር ከተማ የሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ከዚህ በፊትም በጅግጅጋ ከተማ ቃጠሎ የደረሰባቸውን አብያተ ክርስቲያናት ለመጠገን የሚውል የ60 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮቹ የመስቀል አደባባይን ሲያጸዱ ‹‹አማኝ የሌላውን እምነት ያከብራል›› በሚል መልዕክት ነው፡፡ ‹‹መቻቻልና መከባበር የቆየ ሃይማኖታዊ ሥርዓታችን ለማስቀጠል ብቸኛ መሣሪያችን ነው›› ሲሉም አስተያዬታቸውን ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የሰጡት የጽዳት ዘመቻው ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ኃይሉ ማሞ
ዘጋቢ፡-ኃይሉ ማሞ
No comments