Latest

የጎንደሩ ቼጉቬራ! (አሌክስ አብርሃም)



የጎንደሩ ቼጉቬራ! (አሌክስ አብርሃም)

መፍትሄ የማይወደው ኢህአዴግ የመፍትሄ አፈላላጊ ያለውን ሁሉ በሃይል እያነቀ እስር ቤት መወርወርና ማሰቃየት በል ሲለውም መግደል የማንነቱ መገለጫ ይስልጣኑ ዘላለማዊነት ማረጋገጫ መንገዱ ነበር !  


የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ከየቤታቸው እያነቀ ሲወስዳቸው ህግ አለ ፍትህ አለ ብለው በሰላም እጃቸውን ሰጡ የሆነው ግን ታሪክ የማይረሳው ግፍ ሆነ ! አሰቃቂ እስር ቤት ከመወርወር አልፎ  እጃቸውን በሰንሰለት አስሮ በህዝብ ሚዲያ እያሳየ አላገጠባቸው! 

አንዳንዶቹ በእስር ቤት በቂ ህክምና በማጣት ሲሰቃዩ አንዳንዶቹ በእምነታቸው በማንነታቸው ሲቀለድባቸው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲጮህ ቢከርምም ዝሆኑን ማንም ሃይ አላለውም ! የሚገባው ቋንቋ ሌላ ነበርና !

ጋዜጠኛ ነሽ ጦማሪ ነሽ እንደጥሬከመሃላችን እየለቀሙ ማእከላዊ በሚባል ይግፍ መስፈሪያ ሰፍረው ለባርነት ሲሽጧቸው የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ፣የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ሁሉ ሲጮህ ዝሆኖቹ ከመጤፍ አልቆጠሯቸውም የሚገባቸው ቋንቋ ሌላ ነበርና !

አገር አቀፍም ዓለም አቀፍም ህግ ተላለፎ እናዳርጋቸው ጽጌን ከየመን አፍኖ ስር ቤት ሲወረውር አራት ዓመታት አንዴ ሆቴል አንዴ ብቻውን ለይቶ እስር ቤት ሲያሰቃያቸው ለአንዳርጋቸው ዜግነት ከሰጠችው ከታላቋ እንግሊዝ ጀምሮ አፋኙን ዝሆን ማንም ሃይ አላለውም ! 

ማንም!! አገሩ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቹን ባዶ እጃቸውን ለሰልፍ ስለወጡ ብቻ ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ ሲረሽን ሬሳቸውን እንደውሻ ሬሳ በየመንገዱ ሲጥልና ማታ በራሱ ልሳን ለሟቾች አሸባሪ ፣ባንክ ዘራፊ የሚል ስም ሲለጥፍ እናቶች ደም እያለቀሱ ቻሉት ! ዝሆን ጋር ማን ይጣላል? !

ይህን ግፍ የለመደው አፋኝ ጀሌ አንድ ቀን ትጥቁን አሳምሮ ወደአንድ ግለሰብ ቤት ተግተልትሎ ሄደ! የቤቱ ባለቤት አገር ሰላም ብሎ ቤተሰቡ ጋር በተኛበት ሌሊት የማያውቃቸው ሰዎች የግቢውን በር አንኳኩ ! እናም ውጣ ለጥያቄ ትፈለጋልህ አሉት ! የግለሰብ ቤት ነው ! 

የቤት ቁጥር ያለው እስከሚነጋ ቢጠብቁት ቤቱ በሮ ከቦታው የማይጠፋ ! እሱም አገር ያወቀው ጸሃይ የሞቅው አገሩን አገልግሎ በክብር በጡረታ የተሰናበተ ባለከፍተኛ ማእረግ ኢትዮጲያዊ! እናም በሁለት ከልሎች መሃል በተነሳ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ብሎም መሬቱ ላይ በሚኖሩ ሰዎች ማንነት ጥያቄ ላይ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ አፈላላጊ ብሎ ህዝቡ የመረጠው ሰው! <<በህግ ትፈለጋለህ >> ያሉት ሰዎች በህገወጥ መንገድ በህገወጥ ሰዓት ቤቱን አንኳኩ . . . ጧት እንዲመለሱ በወጉ በደንቡ በመጥሪያ እንዲጠሩት ነገራቸው !

ሰዎቹ ግን ሲጀመርም ታምነው የመጡት ሃይላቸውን ነበርና ያን በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን በግፍ የጨፈጨፈውን፣ ያን ለሶስት አስርት ዓመታት ህዝብን ረግጦ የገዛውን ፣ ያን ሲዘርፉ ሲገድሉ ጠባቂያቸው የነበረውን ግፈኛ አፈሙዝ ወደሰውየው ቤት አዞሩ ፣ ማዞር ብቻ አይደለም ወደሰላማዊ የግለሰብ ቤት ህጻን አለ ሴቶች አሉ ሳይሉ በጭካኔ ተኩስ ከፈቱ ! ግኡዙ የግቢ አጥርና መስተዋት ላይ ጥይት ዘነበ !! የጎንደር ሰማይ እንደለመደው በማለዳ ቅዳሴ ሳይሆን በነብሰበላዎች ተኩስ ተሞላ !!

እንደሌላው ጊዜ ከተኩሳቸው በኋላ ኮሌታውን ይዘው እየጎተቱ የሚወስዱት ቁስለኛ ከቤት አልወጣም ፣ ለካቴና ሲሳይ ሊሆኑ እጆች ወደላይ ተሰቅለው ከግቢው አልወጡም፣ ከግቢው ውስጥ የሴቶችና ህጻናት ለቅሶ አልተሰማም ፣ በደም የጨቀየ የውሸት ዜና የሚሰራበት ሬሳም አልነበረም !! 

የተሰማው የኢትዮጲያን የነገ እጣ ፋንታ ከአምባገነኖቹ እጅ ላይ ያረገፈ ፣ ዝሆኖቹን አሸማቆ ድምቢጥ ያሳከለ ፈጽሞ ያልታሰበ የመልስ ተኩስ ድምጽ ነበር !! ታምቆ የኖረው የኢትዮጲያ ብሶት ከዛ ግቢ እሳት ሁኖ ወጣና የአምባገነኑን አፋኞች በላቸው! እንደዝንብ አረገፋቸው !! 

ድፍን ጎንደር ሆ ብሎ ወጣ ፣ ድፍን ኢትዮጲያ እምቢተኛውን ተከትሎ እምቢ አለ ! ድፍን ዓለም ላይ የሚኖር ኢትዮጲያዊ ሁሉ የነጻነት ጸበል ከዛ ግቢ መንጭቷልና የተጫነበትም የባርነት አጋንት ተጠምቆ ሊያላቅቅ ነብሱ ወደጎንደር ገሰገሰች ! 

የታጠቁ ብዙ መቶዎች ጎንደር ከተማ ላይ አምባገነኑ በሚገባው ቋንቋ ማናገር እንደሚችሉ ያይ ዘንድ ታጥቀው ወጡ ! እስካሁን አልገቡም !!
ከዛን ቀን በኋላ ከዛን ቀን ጀምሮ 

ዛሬም ዛሬ ሆነ ድሮም ቀረ ድሮ !!

No comments