Latest

በወጣቶች መካከል እየተፈጠረ ያለውን ግጭትና ህገ ወጥ ተግባር ከዚህ በኋላ እንደማይታገስ የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ

ፌደራል ፖሊስ

(ኤፍ.ቢ.ሲ) ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ የድርጅት አመራሮችን ለመቀበል በሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ላይ በወጣቶች መካከል እየተፈጠረ ያለውን ግጭትና ህገወጥ ተግባር ከዚህ በኋላ እንደማይታገስ የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል ከአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ኢብሳ ነገዎ ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይም ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል በትናንትናው እለት እና ዛሬ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ የድርጅት አመራሮችን ለመቀበል በሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ላይ በወጣቶች መካከል ግጭት መፈጠሩን አስታውቀዋል።

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራውን የኦነግ ቡድን ለመቀበል እየተደረገ ባለ ቅድመ ዝግጅት ወቅት ወጣቶች የድርጅቱን አርማ ለመስቀል ዝግጅት እያደረጉ ነበር፤ ይህንን የከለከላቸው አካል የለም ያሉት ኮሚሽነር ዘይኑ፥ ሆኖም ግን አስፋልትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትን እንዳያቀልሙ ተከልክው የነበረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይም የሃሳብ ልውውጥ ከተደረገ በኋላ ወጣቶቹ የቀረበውን ሀሳብ ተቀብለው የነበረ መሆኑን ተናግረዋል።


ሆኖም ግን ማንም ያልፈቀደላቸው አካላት የእነሱን አርማ አውርደው የሌላ ለመስቀል ሲሉ ግጭት ተፈጥሯል ሲሉም ገልፀዋል።

ግጭቱ ለማንም ጠቃሚ አይደለም ያሉት ኮሚሽነር ዘይኑ፥ ችግሩን በውይይት መፍታት ሲቻል ወደ አላስፈላጊ ግጭት መግባት ተገቢ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።

ፖሊስ የህግ የበላይነትን የማስከበር ሀላፊነት ስላለበት ከዚህ በኋላ እንዲህ አይነት ግጭቶችን በትእግስት እንደማያልፍም ኮሚሽነር ዘይኑ አሳስበዋል።

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፥ የዴሞክራሲ ስርዓትን እንገንባ ብለን ስንነሳና ስርዓቱን ለመገንባት የሚያስፈልጉ ባህሪያትን ተቀብለን ካልተነሳን ግን ስርዓቱን መገንባት እንችልም ብለዋል።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ልዩነቶችን መቀበል የግድ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፥ ልዩነቶቹ ደግሞ ሀሳቦችን፣ አርማዎችን እና ባንዲራዎችን ሊያጠቃልል ይችላል ብለዋል።

ትናንትና እና ዛሬ በአዲስ አበባ የተስተዋሉ ችግሮች ደግሞ ከዚህ ጋር የሚፃረሩ ናቸው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፥ ማንኛውም አካል ስሜቴን ይገልፅልኛል ያለውን አርማ የመያዝ እና የማውለብለብ መብት አለው ሲሉም ተናግረዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ኢብሳ ነገዎ በበኩላቸው፥ ሰሞኑን በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ የተስተዋለው ችግር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አንስተዋል።

ወጣቱም ከዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች ሊቆጠብ እንደሚገባም አቶ ኢብሳ ጥሪ አስተላልፈዋል።

አሁን ላይ እየታየ ያለው ግጭት እና ያልተገባ ፉክክር ድርጅታቸውን የማይወክል መሆኑንም ነው አቶ ኢንብሳ የተናገሩት።

No comments