Latest

ልዩ ፖሊስ ማነው? የወደፊት ዕጣውስ? (ቢቢሲ)

ልዩ ፖሊስ ማነው? የወደፊት ዕጣውስ?

የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በተደጋጋሚ የመብት ጥሰት እንደሚፈጽም ክስ ይቀርብበታል።

በቅርቡ አምነስቲ ኢንትርናሽናል የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ በኦሮሚያና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅሟል በማለት የፌደራል መንግሥት ቡድኑን በአስቸኳይ እንዲበትን ጥያቄ አቅርቧል።

አምነስቲ ባወጣው መግለጫ ልዩ ፖሊስ ሰዎችን ከመግደል እሰከ መኖሪያ ቤቶችን ማጋየት የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን ይፈጽማል ብሏል።

በቅርቡም በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ሙሉ ሙሉቄ ተብላ በምትጠራው ወረዳ ውስጥ ለ41 ሰዎች መሞት፤ የአካባቢው ባለስልጣናት እና ተጎጂዎች ልዩ ፖሊስን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

የወረዳዋ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ትዝታ አባይ ለ37 ሰዎች ህይወት መጥፋት እና 44 ሰዎች ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂው ልዩ ኃይል ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ ጠቃት ጉዳት ከደረሰባቸው አንዱ የሆኑት የወረዳዋ ነዋሪ አቶ መሃመድ ሲራጅ ''በቤት ውስጥ ተቀምጠን ባለንበት ወቅት የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊሶች በር ገንጥለው ገቡብን። ባለቤቴን፣ ልጄን እና የሁለት ዓመት የጎረቤት ልጅ አጠገቤ ገደሉ'' በማለት የተፈፀመውን ጥቃት በሶማሌ ልዩ ፖሊስ መፈጸሙን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌላው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዋች ከሳምንታት በፊት ባወጣው ሪፖርት፤ በሶማሌ ክልል በሚገኘው ኦጋዴን እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ታሳሪዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች እና የልዩ ፖሊስ አባላት ድብደባ እና የመደፈር ጥቃት እንዳደረሱባቸው ገልጿል።

ራይትስ ዋች ካነጋገራቸው ሴቶች መካከል በእስር ቤቱ ውስጥ ተደፍረው እዚያው በታሰሩበት ክፍል ውስጥ ያለ ህክምና ዕርዳታ ልጆቻቸውን እንደተገላገሉ ገልጸዋል።

ልዩ ፖሊስ እንዴት ተመሰረተ?
የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስን በተመለከተ እስካሁን የሚታወቅ ምንም አይነት ይፋዊ መረጃ የለም። ስለ ልዩ ፖሊስ አመሰራረት እና አደረጃጀት መረጃ እንዲሰጡን የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል፣ የሃገር መከላከያ ባለስልጣንን እና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ተቋምን አነጋግረናል።

አቶ ጀማል ድሪ ሃሊስ የክልሉ ተወላጅ ሲሆኑ ገላዴ የምትባል ወረዳን ወክለው ሁለት ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠዋል። አቶ ጀማል ''የሶማሌ ክልልን እና ፖለቲካውን ጠንቅቄ አውቃለው። እአአ 2007 ላይ በሶማሌ ክልል የሚሰራውን ግፍ በመቃወሜ ሃገር ጥዬ ለመሰደድ ተገድጃለው'' ይላሉ። በአሁኑ ሰዓት አቶ ጀማል መኖሪያቸውን ጀርመን ሃገር አድርገዋል።

አቶ ጀማል የልዩ ፖሊሰን አመሰራርት ሲያስረዱ ''በአካባቢው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) በስፋት ይንቀሳቀስ ነበር። ይህን ኃይል የኢትዮጵያ መከላከያ ሥራዊት ለመደምሰስ ብዙ ጥረት አድርጎ ውጤታማ መሆን አልቻለም'' ይላሉ።

አቶ ጀማል እንደሚሉት ከሆነ፤ ኦብነግን ሲወጉ የነበሩት የሃገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የአካባቢውን ቋንቋ እና ባህል ስለማያውቁ የአማፂውን ኃይል ከሲቪሉ ህዝብ እንኳን ለየተው ማወቅ አልተቻላቸውም ነበር።

''እአአ 2007 ላይ ግን የክልሉን ፖለቲካዊ ምህዳር የቀየር ሁኔታ ተከሰተ። ኦብነግ ነዳጅ ፍለጋ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ከ70 በላይ ቻይናውያንና በርካታ ኢትዮጵያዊያንን ገደለ። በዚህም የፌደራሉ መንግሥት ኦብነግ ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ተነሳ'' በማለት አቶ ጀማል ያስታውሳሉ።

ለዚህም ሁነኛ አማራጭ የነበረው በሶማሌ ክልል ችግር ሆኖ የቆዩትን ሥራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ሰልጠና ሰጥቶና አስታጥቆ ኦብነግ ላይ ማዝመት ነበር ይላሉ።

የአምንስቲ ኢንተርናሸናል የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አጥኚ የሆኑት አቶ ፍሰሃ ተክሌ፤ ልዩ ፖሊስ የተቋቋመው እአአ ከ2007-2008 ባሉት ዓመታት እንደሆነ አስታውሰው፤ "በአካባቢው ይንቀሳቀስ የነበረውን መንግሥት በወቅቱ የሽብር ቡድን ብሎ የሚጠራውን ኦብነግን ለመቆጣጠር ነው" በማለት ከአቶ ጀማል ጋር ልዩ ፖሊስ ስለተመሰረተበት ምክንያት ተመሳሳይ ሃሳብ ይሰጣሉ።

አቶ ፍሰሃ እንደሚሉት ከሆነ ልዩ ፖሊስ ሲቋቋም በክልሉ መንግሥት እንደሚተዳደር እና ለክልሉ መንግሥት ተጠሪ የሆነ አካል ነው ተብሎ ነበር።

ጨምረው በሃገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሰረት ድንበር ዘለል ታጣቂ ኃይልን የመከላከል ግዴታ እና ሃላፊነት ያለበት የመከላከያ ሠራዊት ነው። ስለዚህ ልዩ ፖሊስ ሊቋቋም የሚችልበት የህግ አግባብ የለም በማለት ያስረዳሉ።

''የልዩ ፖሊስ አደረጃጀትን ስንመለከት በክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ አይደለም ያለው። ልዩ ፖሊስ የራሱ አዛዥ አለው። ያ አዛዥ ደግሞ ተጠሪነቱ ለቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት ለነበሩት አቶ አብዲ ሙሃመድ ኡመር ነው'' ይላሉ አቶ ፍሰሃ።

አቶ ጀማልም የልዩ ኃይል አወቃቀር ህጋዊ መሰረት የለውም በማለት በአቶ ፍሰሃ ሃሳብ ይስማማሉ። እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ልዩ ፖሊስ የክልሉ ፖሊስ ውስጥም ይሁን የሚሊሻ መዋቅር ውስጥ የለም።

በሃገር መከላከያ የኢንዶክትሬኔሽን እና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሜጀር ጀነራል ሞሃመድ ተሰማ ግን የልዩ ፖሊስ አመሰራረት ምንም አይነት የሕግ ከለላ የለውም የሚለውን ሃሳብ አይቀበሉም።

ሜጀር ጀነራል ሞሃመድ ''ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት ሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት አለ። መደበኛ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻዎች አሉ። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልም እንደማንኛውም ክልል የልዩ ኃይል ፖሊሶችን አሰልጥኖ እና አቋቁሞ ካሰማራ በኋላ ከፌደራል ኃይል ጋር የፀጥታ ማስከበር ሥራን ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም በአካባቢው የተሻለ መረጋጋት ተፍጥሯል። ከህጋዊ ዕውቅና ውጪ የተቋቋመ አልነበረም'' ይላሉ።
የልዩ ፖሊስ አወቃቀር

''አብዲ ሙሃመድ ኡምር የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ሃላፊ ሆነው፤ እንዲሁም ፕሬዝዳንት ከሆኑም በኋላ ልዩ ፖሊሰ ተጠሪነቱ ለእሳቸው ነበር'' በማለት አቶ ፍሰሃ ይናገራሉ።

አቶ ፍሰሃ እንደሚሉት እአአ መስከረም 2017 ላይ ልዩ ፖሊስ ጥቃት አድርሶ በህይወት የተረፉትን አምነስቲ ባነጋገረበት ወቅት የልዩ ፖሊስ አባላት ከፕሬዝዳንት አብዲ ጋር በቀጥታ በስልክ ሲነጋገሩ መስማታቸውን ነግረውና ይላሉ።

አቶ ጀማል በበኩላቸው ''ልዩ ፖሊስ በቀጥታ ትዕዛዝ ይቀበል የነበረው ከቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝደነት አብዲ ሙሃመድ ኡመር ነበር። አብዲ ሙሃመድ ኡመር ደግሞ ከምሥራቅ ዕዝ አዛዦች እና አዲስ አበባ ካሉ ባለስልጣናት ትዕዛዝ ይወስዳሉ'' በማለት የዕዝ ተዋረዱን ያስረዳሉ።

አቶ ጀማል ጨምረው እንደሚናገሩት ''የልዩ ፖሊስ አባላት ሲመለመሉ ሆነ ተብሎ የትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ እና ሥራ አጥ የነበሩ ወጣቶች ናቸው። በጦር ስልጠናቸው ወቅትም የሰብዓዊ መብት አያያዞችን በተመለከተ የሚሰጣችው ምንም አይነት ስልጠና የለም'' ይላሉ።


የልዩ ፖሊስ የሠራዊት ብዛት እና የታጠቀው መሳሪያ
አቶ ፈሰሃ ''በሶማሌ ክልል ውስጥ ምንም አይነት ነግር ግልጽ ስለማይደረግ ትክክለኛ አሃዝ ማስቀመጥ አይቻልም'' ይላሉ። በክልሉ ውስጥ ምን ያህል የክልል ፖሊስ፣ ልዩ ፖሊስ እና ሚሊሻ እንዳለ እና በጀታቸውን ማወቅ አስቸጋሪ ነው ይላሉ።

አቶ ጀማል ደግሞ ''አቶ አብዲ ሙሃመድ በተለያየ ወቅት ሲነገሩ እንደሰማሁት ከሆነ፤ የጦሩ ብዛት ከ30ሺ እሰከ 40ሺ ድረስ ሊሆን ይችላል'' ሲሉ፤ የታጠቁት የጦር መሳሪያ አይነትን በተመለከተ ደግሞ አቶ ጀማል ሲያስረዱ ''ተራ ፖሊስ ከሚይዘው መሳሪያ የተሻለ እና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ናቸው'' ይላሉ።

አቶ ፍሰሃም በበኩላቸው ''በምሥራቅ ኦሮሚያ ከልዩ ፖሊስ ጋር ግነኙነት ካደረጉ ግለሰቦች በሰበሰብነው መረጃ መሰረት ልዩ ፖሊስ የታጠቀው መሳሪያ የሃገር መከላከያ ከታጠቀው ጋር የሚመጣጠን መሆኑን ተረድተናል'' ይላሉ።

ሜጀር ጀነራል ሞሃመድ ደግሞ በሶማሌ ክልል የፀጥታ ችግር እንደነበርና ይህን ችግር ለመቅረፍ ከፌደራል የፀጥታ ኃይል ጋር በመሆን ልዩ ኃይሉን የማጠናከር እና የማዘጋጀት ሥራ መሰራቱን በዚህም ፀጥታ ችግሩን ለመቅረፍ እንደተቻለ ይናገራሉ።


የልዩ ፖሊስ ዕጣ-ፈንታ
የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ የቀጥታ ትዕዛዞችን የሚቀበለው ከቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ሙሃመድ ኡመር እንደሆነ ይታመናል። የአቶ አብዲ ከስልጣን መውረድ ጋር ተያይዞ የልዩ ፖሊስ ዕጣ-ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል ስንል አቶ ጀማልን ጠይቀናል።

እንደ አቶ ጀማል እምነት ከሆነ የልዩ ፖሊስ አባላት አቶ አብዲ ከስልጣን መውረዳቸው እርግጥ መሆኑን ሲረዱ ትጥቅ ለመፍታት ፍቃደኛ ይሆናሉ ይላሉ። ነገር ግን አባላቱ በሕዝብ ላይ የተለያዩ በደሎችን ሲፈጽሙ የቆዩ ስለሆኑ ወደ ሕዝብ እንዲቀላቀሉ ከመደረጋቸው በፊት የተሃድሶ ስልጠና ያስፈልጋቸዋል ባይ ናቸው።

አቶ ፍሰሃ ግን በቅርቡ በምሥራቅ ሃረርጌ ልዩ ፖሊስ ፈጽሞታል የተባለውን ጥቃት በማስታወስ ''ምንም እንኳ ለልዩ ፖሊስ ትዕዛዝ ይሰጡ የነበሩት አቶ አብዲ ከስልጣን ቢወርዱም ልዩ ኃይሉ በድርጊቱ እንደቀጠለ ነው። አምነስቲም ጥፋተኛ የሆኑት ለህግ እንዲቀርቡ ይጠይቃል '' ብለዋል።

ሜጀር ጀነራል ሞሃመድ ተሰማ ደግሞ ''የፌደራል የፀጥታ ኃይል የሶማሌን ልዩ ኃይል ትጥቅ የማስፈታት ዓላማ ይዞ አልተንቀሳቀሰም። ልዩ ኃይሉ ቀድሞም እንዲታጠቅ እና እንዲሰለጠን ያደረገው የፌደራሉ መንግሥት ነው። ልዩ ፖሊሱ የፀጥታ ማስፈን ሥራ አካል ሆኖ እንዲሰራ የማድግ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው እንጂ እነሱን ትጥቅ የማስፈታት ዓላማም ሆነ ዕቅድ የለም'' ብለዋል።

No comments