Latest

ኢትዮጵያውያን የሀጅ ተጓዦች በመካ እየተንገላቱ ነው - ቢቢሲ

ኢትዮጵያውያን የሀጅ ተጓዦች በመካ እየተንገላቱ ነው

ዘይኑ ሻፊ መሀመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መካ ያቀኑት ከ 14 ዓመታት በፊት ነበር። ስፍራው ካለው የላቀ ሀይማኖታዊ ዋጋ አንጻር በመጓዛቸው ደስ ቢላቸውም፤ ለሀጃጆች የሚገባ መስተንግዶ ባለማግኘታቸው ቅር ተሰኝተው ነበር።

ከዓመት ዓመት ለውጥ ይመጣል ብለው ተስፋ ማድረጋቸው ባይቀርም፤ ከ14 ዓመታት በኃላ ዘንድሮ ዳግም ወደ መካ ሲሄዱም ከበፊቱ የባሰ እንጂ የተሻለ መስተንግዶ አላገኙም።

በዘንድሮው ጉዞ ከኢዲስ አበባ ተነስተው መዲና ከደረሱ በኃላ የጠበቃቸው መኝታ የማይመች ነበር። ለሁለት ቀናት በመዲና ቆይተው ወደ መካ ሲያመሩ ሁኔታዎች ተባባሱ። እንዲያርፉበት በተዘጋጀላቸው ጠባብ ክፍል ከስምንት ሰዎች ጋር መዳበል ግድ ሆነባቸው።

ዘይኑ እንደሚሉት አንሶላና ትራሱ የነተበ፣ መጥፎ ሽታ ያለው አልጋ ላይ እንዲያርፉ ሆነ። ሁኔታው እንደሳቸው በእድሜ የገፋ ሰውን ብቻ ሳይሆን ወደ ስፍራው ይዘዋቸው የሄዱት ቤተሰቦቻቸውንም አስቀይሟል።

ስለ ማረፊያ ክፍላቸው አማረው ሳይጨርሱ ለመዋጥ የሚተናነቅ፣ የቆየና ሽታ ያለው ምግብ ቀረበላቸው። ለቢቢሲ ከመካ እንደተናገሩት በአካባቢያቸው ንጹህ መጸዳጃ የለም። ድንገት የሚታመም ሰው ከህመም ማስታገሻ ያለፈ አያገኝም።

ከኢትዮጵያ ሲነሱ ለሀጅ ጉዞና ሙሉ መስተንግዶ የከፈሉትን ገንዘብ ሲያሰሉ ሁኔታው የበለጠ ያሳዝናቸዋል።

በምጽዋት ለመመገብ ተገደዋል
የመካ ጉዞ የበርካቶችን ኪስ የሚፈትሽ ነው። የእርሻ መሬታቸውን ሸጠው፣ ሀብት ንብረታቸውን አሟጠው ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ጥቂት አይደሉም። ክፍያቸውን የሚመጥን መስተንግዶ ግን አያገኙም።

ከሁሉም የከፋው ምግብ ለማግኘት መቸገራቸው ነው። "እናቶቻችንን፣ ሚስቶቻችንን ይዘን የመጣን አለን። ቤተሰቦቻችንን ምን እናብላ?"በማለት ሁኔታውን በሃዘን ይገልፃሉ።

ሀጃጆች የምጽዋት ምግብ ተቀብለው ሲመገቡ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችና ቪድዮዎች በማህበራዊ ሚዲያ ተለቀዋል። "ኢትዮጵያውያን ስማችን ይህ አልነበረም። ክብራችን ተነክቷል" የሚሉትም ለዚህ ነው።

ለዘይኑ፤ ኢትዮጵያውያን እየደረሰባቸው ያለው እንግልት ከሌሎች ሀገር ዜጎች የበለጠ ነው።

እሮሮው የሳቸው ብቻ ሳይሆን የተቀረው ሙስሊም ማህበረሰብ ጭምርም ሲሆን፤ ጉዞውን የሚያስተባብረውን የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ተጠያቂ ያደርጋሉ። በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉዳዮች ዙሪያ ምክረ ሀሳብ ለማቅረብ በጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ የተዋቀረው ኮሚቴ ከሚያያቸው ጉዳዮች አንዱ ይህ ጉዞ ስለሆነ ነገሩ እንደሚቀየር ተስፋ ያደርጋሉ።

ኮሚቴው መፍትሄ ያበጅላቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ችግሮች መካከል የሀጅና ኡመራ ጉዞ ይገኝበታል።

"መጅሊሱ መለወጥ አለበት። እንግልቱ በኛ መብቃት አለበት። ለቀጣዩ ትውልድ መተላላፍ የለበትም" ይላሉ ዘይኑ።

ሀሳባቸውን የሚጋራው አቡበከር አለሙ ከሳምንት በፊት ነበር ወደ መካ ያቀናው። ለደርሶ መልስ የአውሮፕላን ትኬት፣ ለምግብ፣ ለአልጋ፣ ከማረፊያ ወደ መስጅድ ለሚደረግ ጉዞ ባጠቃላይ 95,000 ብር ከፍሏል። ብዙዎች ምክር ቤቱ በሚሄዱበት ሀገር ምቹ መቆያ እንደሚያሰናዳላቸው በማመን ቢከፍሉም የሚገጥማቸው ከእውነታው የራቀ ነው ይላል።

በመዲናና መካ በብዛት ኢትዮጵያውያን የሚያርፉባቸው ቦታዎች አልዛሂር፣ አልቤክ፣ ማፊል፣ ሰአድ ሲሆኑ፤ የተሻለው ሰአድ እንደሆነ ይናገራል። እንደየ አማኙ ፍላጎት ከሁለት ሳምንት እስከ አንድ ወር የሚቆዩም አሉ።

በኢትዮጵያ ገንዘብ ያደረጉት ክፍያ ወደ ሳዑዲ ሪያል ሲመነዘር ማግኘት ከሚችሉት መስተንግዶና ከሳዑዲ ኑሮ አንጻር ፍትሀዊ እንዳልሆነም ብዙዎች ይገልፃሉ። ገንዘብ ያላቸው ለተጨማሪ ወጪ ሲዳረጉ፤ አብዛኛው ማህበረሰብ በአንጻሩ የስቃዩ ሰለባ ነው።

አቡበከር እንደሚለው "ለብዙ ዓመታት ስለችግሩ ቢወራም መፍትሄ አልተሰጠንም። የሀጂ ጉዞ ችግር ከሙስናና የመልካም አስተዳዳር እጦት ጋር ይገናኛል።"

ለሀጅ ጉዞና ሌሎችም የሙስሊሙ ማህበረሰበብ ጥያቄዎች መፍትሄ ያመጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ኮሚቴ ህዘዝብ ግንኙነት ካሚል ሸምሱ፤ የአቡበከርና ዘይኑን ቅሬታ ይጋራል። "ሀጃጆችን ብቻ ሳይሆንም ኢትዮጵያንም ያሳፈረ ነው" ይላል።

ካሚል እንደሚለው ችግሩ የሚጀምረው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካለው መስተንግዶ መጓደል ነው። ከጥቂት ቀናት በፊት ሀጃጆች በአየር ማረፊያው መጉላላታቸውን መናገራቸው ይታወሳል።

አየር መንገዱ በበኩሉ፤ በሶማሌ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለጉዞ ዘግይተው የሄዱ ሀጃጆች በሳውዲ አረቢያ አየር መንገድ ሊስተናገዱ ባለመቻላቸው፤ በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ባይኖረውም ጉዟቸውን አመቻችቷል ሲል መግለጫ ሰጥቷል። ከሳዑዲ ሲቪል አቪየሽን የበራራ ፍቃድ እስኪገኝም ምግብና መሰል መስተንግዶ ቀርቧል ተብሏል።

የሀጅና ኡምራ ጉዞ ማስተባባሪያ የሚካተትበት መጅሊስ መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ካሚል ይናገራል። ከአዲሱ ኮሚቴ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ለጉዞው የሚጠየቀውን ክፍያ ፍትሀዊ ማድረግ፣ ጉዞ ምቹ ማድረግና ተገቢ መስተንግዶ መስጠት ይገኙበታል።

ዘጠኝ አባላት ያለው ኮሚቴው በሌሎች ሀገሮች ስላላው የሀጂ ጉዞ ጥናት በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ። ኮሚቴው ውጤታማ እንዲሆን ከሚጠብቁ አንዷ ሙኒራ አብድልመናን ናት።

ሙኒራ ትላንት ምሽት ከሶስት ሰአት እስከ አምስት ሰአት ድረስ በትዊተር ላይ ዘመቻ እያደረገች ነበር። የዘመቻው ዋነኛ ማጠንጠኛ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሀጃጆች ከተጉላሉ በኃላ የሰጠው መልስ እንግልቱን የሚመጥን አይደለም የሚል ነው።

አየር መንገዱ ለተነሳው ቅሬታ ተመጣጣኝ ምላሽ አልሰጠም የምትለው ሙኒራ፤ ሀጅ አድራጊዎች ሲጉላሉ የመጀመሪያው ባይሆንም ተቃውሞው በተደራጀ መልከ እንዳልነበር ታስታውሳለች።

ኢትዮጵያ ውስጥና እንደሷ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የትዊተር ዘመቻው፤ አየር መንገዱ ተጓዦቹን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅና በቀጣይ ዓመታት ተመሳሳይ እንግልት እንዳይከሰት ማሳሰቢያ ጭምርም ነበር።

ጉዳዩ በዋነኝነት የሚመለከተው የሀጅ አዘጋጅ ኮሚቴ እንደመሆኑ "ለኛ መብት የሚቆም ጠንካራ ተቋም መኖር አለበት" ትላለች።

በአሁን ወቅት በመካ ያሉትን እንዲሁም ሀገር ውስጥ የሚገኙትን የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አባላት ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

No comments