Latest

ፌስቡክ የስፔን ላ-ሊጋ ውድድሮችን ቀጥታ ሊያሳይ ነው

ፌስቡክ የስፔን ላ-ሊጋ ውድድሮችን ቀጥታ ሊያሳይ ነው

(ቢቢሲ) ከመጪው አርብ ጀምሮ በህንድና በአካባቢዋ ባሉ ሃገራት ያሉ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች የስፔን ላ ሊጋን ለመመልከት ያላቸው ብቸኛው አማራጭ ፌስቡክ እንደሚሆን ተገለፀ።

የማህበራዊ መገናኛ መድረክ የሆነው ፌስቡክ በሕንድ፣ በአፍጋኒስታን፣ በባንግላዴሽ፣ ቡታን፣ ኔፓል፣ ማልዲቭስ፣ ሲሪ ላንካ እና ፓኪስታን ውስጥ በቀጣይ ሦስት የውድድር ወቅቶች በስፔን ላ ሊጋ የሚካሄዱ ሁሉንም ጨዋታዎች በብቸኝነት ለማሳየት ስምምነት ተፈራርሟል።

ቀደም ሲል በእነዚህ ሃገራት የስፔን ላ-ሊጋ ውድድሮችን የማሳየቱ መብት በሶኒ ፒክቸርስ ኔትወርክ ተይዞ ቆይቷል።

አዲሱ ፌስቡክ የተፈራረመው ስምምነት ምን ምን እንደሚያካትት እስካሁን ይፋ አልተደረገም። እንደሮይተርስ ዘገባ ከአራት ዓመታት በፊት ይህ መብት ለገበያ ቀርቦ በነበረት ጊዜ 32 ሚሊዮን ዶላር ተሽጧል።

በተጠቀሱት ሃገራት ውስጥ 348 ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ሲኖሩ 270 ሚሊዮኑ የሚገኙት ሕንድ ውስጥ ነው።

ይህ አዲስና ከፍተኛ ገንዘብ ሊያስገኝ ይችላል የተባለው በኢንተርኔት ውድድሮችን በቀጥታ የማስተላለፍ አገልግሎት ላይ መዋዕለ ነዋይን የማፍሰስ ስምምነት ለፌስቡክ በአጠቃላይ ደግሞ ለዘርፉ ኢንዱስትሪ አዲስ ነው ተብሏል።

የፌስቡክ ዓለም አቀፍ የስፖርት ቀጥታ ስርጭት ሃላፊ የሆኑት ፒተር ሃተን ለሮይተርስ እንዳሉት የላ-ሊጋው የቀጥታ ስርጭት በመጀመሪያ ላይ ምንም አይነት ማስታወቂያ አይኖረውም። ነገር ግን ለወደፊቱ በምን መልኩ ማስታወቂያ ሊስተናገድበት እንደሚችል እያሰቡበት ነው።

የስፖርት ውድድሮችን በቀጥታ ማስተላለፍ በሳተላይትና በገመድ የሚተላለፉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዋነኛ የገቢ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። አሁን ግን የአዲስ ቴክኖሎጂ ተቋማት ቀስ በቀስ ወደዚህ ዘርፍ መግባታቸው ለቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስጋት እየፈጠረ ነው።

ፌስቡክ ከላ-ሊጋ ጋር የፈፀመው ስምምነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለው የለውጥ አካል ነው። በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥም ባለፈው ሳምንት የተጀመረው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ሁሉም ጨዋታዎች በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት የሚታዩበት የመጨረሻው ውድድር እንደሚሆን እየተነገረ ነው።

በዚህም በቀጣዩ የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ወቅት ከሚካሄዱ ጨዋታዎች መካከል 20ዎቹ በኢንተርኔት አማካይነት ብቻ በአማዞን በኩል የሚታዩ ይሆናሉ። በኢንተርኔት የሚያስተላልፈው ኩባንያም ጨዋታዎቹን የተለየ ክፍያ በማስከፈል የሚያቀርብ ይሆናል።

No comments