Latest

“ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት አንድም የረባ ጄኔራል አላፈራችም” ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (ክፍል ፩)



ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለህክምና ወደ አውሮፓ ተጉዞ በነበረበት ወቅት በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሰላማዊ ትግል መድረክ ለዴሞክራሲና ለሕግ የበላይነት ያደረገውን ጉልህ አስተዋፅዖ እንዲሁም በነፃው ፕሬስ ዘርፍ የከፈለውን መሥዋዕትነት ከግምት በመክተት ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል፡፡  


የተጓዘበትን ጉዳይ አጠናቆም ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል፡፡ የባህር ማዶ ቆይታውን፣ የሀገሪቱን የተለያዩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችና በቀጣይነት ሊሠራቸው ስላሰባቸው ጉዳዮች በስፋት አነጋግረነዋል፡፡ መልካም ቆይታ፡፡

ግዮን፡- በቅርቡ ወደ አውሮፓ ከተጓዝክበት ጉዳይ ቆይታችንን ብንጀምርስ?
ተመስገን፡- መልካም:: በቅድሚያ የመጽሔታችሁ እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ:: ወደ አውሮፓ የሄድኩት ለህክምና ነው፤ ሁላችሁም እንደምታስታውሱት ከእስር ቤት ስፈታ ከፍተኛ የሆነ የወገብ ህመም ያሰቃየኝ ነበር። ይሁንና በሀገር ቤት በወሰድኳቸው የተለያዩ ህክምናዎች ቀስ በቀስ ሙሉ በሙሉ ሊያስብል በሚችል መልኩ ተሽሎኝ ነበር። ወደ አውሮፓ የተጓዝኩት ቀደም ተብሎ የተያዘ ፕሮግራም ስለሆነ ነው። ህመሙ ከፍተኛ መሻሻል በማሳየቱ በየቀኑ እወስደው የነበረውን ማስታገሻ መድኃኒት መጠቀም ካቆምኩ ሁሉ ቆየት ብሏል::

ግዮን፡- ሆላንድ በቆየህባቸው ቀናት በርካታ የነፃ ፕሬስ ባልደረቦችን አግኝተሃል፤ እዚያ የነበረው አቀባበል ምን ይመስላል?
ተመስገን፡- እውነት ነው። ሀገር ቤት በነበሩበት ጊዜ መልካም ግንኙነት የነበረን የአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረቦች ዐቢይ ተ/ ማርያም፣ መስፍን ነጋሽ፣ ግርማ ተስፋሁን፣ ማስርሻ ማሞ እና ተስፋዓለም ወልደየስን የመሰሉ ጋዜጠኛ ጓደኞቼን አግኝቼ በጣም ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል:: በወቅታዊ ጉዳዮች ላይም በስፋት ተወያይተናል።  

በቀጣይም ሀገር ቤት ገብተው በሚወዱት ሙያ ተሰማርተው ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን እንደሚያገለግሉ ነግረውኛል። ከዚህ በተጨማሪ ለእኔ ጉዞ ማሳካት እና ቆይታ በዋናነት መመስገን ያለባቸው ሁለት ሰዎች አሉ:: 

የመጀመሪያው ከሀገሩ ከወጣ በኋላም በጋዜጠኝነት ሕይወት የቀጠለውና ረዥም ጊዜ በኢንተርኔት ሜዲያ የምናውቀው አንጋፋው ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋና ባለቤቱ ቲጂ ሲሆኑ፤ በሁለተኛ ደረጃ አክቲቪስት ታሪኳ ጌታቸው በእኔ ጉዞና ቆይታ ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጋለች:: 

እንዲሁም የግብዣ ወረቀት የላከልኝን አምንስቲ ኢንተርናሽናልን በዚሁ አጋጣሚ ላመሰገን እውዳለሁ። በተለያየ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በቤታቸው፣ በተለያዩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሬስቶራንቶች ግብዣዎችን በማድረግ ቆይታዬ መልካም እንዲሆን አድርገውልኛል::

ግዮን፡- ሆላንድ ላይ ኢትዮጵያውያን ያዘጋጁልህ ለየት ያለ ፕሮግራም እንደነበረም ሰምተናል፤ ምን ነበረ?
ተመስገን፡- ከዚህ ወደ ሆላንድ ስሄድ እዚያ ጉዳዩን ከሚያስተባብሩት ሰዎች ጋር ተነጋግረን ነበር፤ የምመጣው ለውይይትና ለስብሰባ ሳይሆን ለህክምና ብቻ እንደሆነ አስረድቻቸዋለሁ:: አምስተርዳም አየር ማረፊያ ላይ ምንም ዓይነት አቀባበል እንዳይኖር ያደረግሁት በራሴ ጥያቄ ነው፤ ‘የምመጣው ለህክምና ብቻ ስለሆነ፣ ለአቀባበል ሰው እንዳታስቸግሩ’ በማለቴ ጉዳዩን በምስጢር ይዘውት ነበር።  

እዛ ያሉ ኢትዮጵያውያን ያወቁት አምስተርዳም ከገባሁ በኋላ ነው:: የአምስተርዳም የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ ግንኙነት ስለነበረን ሐሳቤን ተረድተው ያዘጋጁትን ሕዝባዊ ውይይት ሰርዘውታል። ነገር ግን ሁኔታውን ያላወቁ ዘ ሄግ ወይም ደናሀግ በሚባል ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እኔን ሳያማክሩ የቴአትር ቤት አዳራሽ በመከራየት ፕሮግራም አዘጋጅተው ሲያበቁ ለፕሮግራሙ አንድ ቀን ሲቀረው ጥሪ አቀረቡልኝ::  

ለኮሚኒቲው አመራሮች፣ አመጣጤንና ዕቅዴን ብነግራቸውም፣ ‘ግድ የለም፤ አንተ ብቻ ዝም ብለህ ፕሮግራማችን ላይ መገኘትህ በቂ ነው፤ ለከፈልከው ዋጋ ለማመስገን ብቻ ነው የጠራንህ’ የሚል ምላሽ ሰጡኝ:: መቼም አንዴ የአዳራሽ ኪራይ ከፍለዋል፤ ፖስተሮች ሰቅለዋል፤ ስለዚህ አማራጭ ስላልነበረኝ በቀረችኝ ጥቂት ሰዓታት አጠር ያለች የመወያያ ፁሁፍ አዘጋጅቼ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ።  

ከእኔ ፅሁፍ በኋላም ጥያቄና መልስ አካሂደን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መልካም ሊባል የሚችል ውይይት አድርግናል:: በዕለቱም የሙዚቃና የእራት ግብዣም ነበር:: ፕሮግራሙንም ጋዜጠኛ ደረጀ ሀብተ ወ/ልድና ጋዜጠኛ ገሊላ መርተውታል። በነገራችን ላይ አምስተርዳም ላይ ስብሰባና ውይይት ባይኖርም፣ ሁለት ቦታዎች በሬ ታርዶ ትልልቅ ግብዣዎች ተደርገው ነበር::  

አንዱ ለጊዜው ስሙን የዘነጋሁት በከተማ ውስጥ የሚገኝ ትልቅ ፓርክ ውስጥ ነው፤ ሌላው ደግሞ ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ በስደት ያሉ እህትና ወንድሞቼ፣ በሚኖሩበት ካምፕ ውስጥ ባለ አዳራሽ ቆንጆ ግብዣ አዘጋጅተው፣ ክብራቸውንና ፍቅራቸውን ገልፀውልኛል:: በዚህ አጋጣሚ ሁሉንም አክባሪዎቼን ‘እግዚአብሔር ያክብርልኝ’ እላለሁ::

ይቀጥላል...

No comments