Latest

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ባጋጠመ ደራሽ ውሃ ጉዳት ደረሰ - ቢቢሲ

አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ

ዛሬ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ገደማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አቅራቢያ በሚገኝ ድልድይ ገንፍሎ የወጣ ደራሽ ውሃ ጉዳት አድርሷል።

ወንደወሰን ውቤ የአካባቢው ነዋሪ ሲሆን በቦታው ጠዋት 12፡30 ገደማ በአካባቢው እንደነበር ገልጾ "ጎርፉ በግምት እስከ ዘጠኝ ሜትር ጥልቀት ነበረው" ብሏል።

በመኪና ጣራ ላይ የሙጥኝ ያሉ ሰዎችም በውሃው ለመዋጥ የግማሽ ሜትር ከፍታ ያህል ሲቀራቸው እንዳየ ወንደወሰን ተናግሯል።

ድልድዩ ሳይደረመስ ውሃው ወደ ላይ ገንፍሎ በመውጣቱ የአካባቢው መንገዶች እንደማይታዩ ነግሮናል።

አደጋውን አስመልክተን ያነጋገርናቸው በእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ንጋቱ ማሞ፤ ወደ ስራ ቦታ በመጓዝ ላይ የነበሩ የቼራሊያ ብስኩት ፋብሪካ ሰራተኞች ድልድዩን አልፎ በወጣ ደራሽ ጎርፍ ይጓዙበት የነበረው ተሽከርካሪ መንገዱን አስትቶ ወደ 400 ሜትር ወስዶታል ብለዋል።

በተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩ 10 ሴትና 10 ወንድ ሰራተኞች በውሃው እሰከ መኪናቸው ተገፍተው ተወስደዋል።

ዋና የሚችሉ ሁለት ሰራተኞች የተሽከርካሪውን መስኮት በመክፈት ዋኝተው ሊወጡ ችለዋል።

ቀሪዎቹ ግን የሚያመልጡበት መንገድ ባለመኖሩ የአደጋ ሰራተኞች በቦታው እስኪደርሱ እርስ በርስ ተረዳድተው ከመኪናው በላይ 'ኮርቶ መጋላ' ላይ መቀመጥ ችለዋል።
አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በቦታው ላይ እንደደረሱም ህይዎታቸውን ለመታደግ አዳጋች በመሆኑ ከአየር ሃይል ሔሊኮፍተር ጠይቀዋል።

ሆኖም ግን ከሔሊኮፍተሩ የሚወጣው የነፋስ ሃይል ያለምንም ድጋፍ መኪናው ጣራ ላይ የተቀመጡት ሰዎችን ሊጥላቸው ተቃርቦ ስለነበር ሁለት ሰዎችን ካነሳ በኋላ የመታደጉን ስራ ማከናወን እንዳልቻለ ባለሙያው የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን ዋናተኞች ሰዎቹን ለማትረፍ ተጠሩ። ሰዎቹን አንድ በአንድ በማውጣት 10 አደጋው ውስጥ የነበሩ ሰዎችን በዋና ታደጉ።

ቀሪዎቹ 6 ሰዎች ደግሞ በአካባቢው በነበረ የኮንስትራክሽን ክሬን ሊወጡ እንደቻሉ አቶ ንጋቱ ማሞ ገልፀዋል።

በዚሁ በተከሰተው ደራሽ ውሃ እዚያው አቅራቢያ ሌላ አደጋ አጋጥሞ 2 የአንድ ዓመት ህፃናትን ጨምሮ 9 ሰዎችን ከመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር በመሆን በጀልባና በዋናተኞች እንዲወጡ መደረጉን ባለሙያው ጨምረው ተናግረዋል።

19 የሚሆኑ እንስሳት በአደጋው ሞተዋል።

ሰዎቹ የከፋ ጉዳት ባያጋጥባቸውም በውሃ ውስጥ ለሰዓታት ቆይተው ስለነበር በአካባቢው በሚገኝ ጤና ጣቢያና በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል።

አቶ ንጋቱ የአደጋውን ምክንያት አስመልክቶ፤ "ደራሽ ውሃው እንዴት እንዳጋጠመ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም፤ ውሃው ግን በከባድ ዝናብ ያጋጠመ አይመስልም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በባለስልጣኑ የክረምት ወራትን ተከትሎ ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቀድሞ የተዘጋጀ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት ችግር ሲያጋጥም የሌሎች መስሪያ ቤቶችን እርዳታ መጠየቃችን ግድ ነው ብለዋል።

ክረምት በመጣ ቁጥር "አዲስ አበባን ሳይጎበኛት አያልፍም" ያሉት ባለሙያው እንዲህ ዓይነት ችግር ግን በስራ ዘመኔ አላገጠመኝም ሲሉ ተናግረዋል።

No comments