Latest

ለደብዳቢ የተፃፈ ደብዳቤ (በላይ በቀለ ወያ)

በላይ በቀለ ወያ

ለደብዳቢ የተፃፈ ደብዳቤ 

(በላይ በቀለ ወያ)


እንዴት ነህ ኢህአዴግ ፣ እኛ አለን በደህና
ባመቻቸህልን ፣ የልማት ጎዳና
ተገናኘን ስንል ፣ እየተጠፋፋን
ተቃቀፉ ሲባል ፣ እየተገፋፋን
ራዕይ አንግበን ፣ አላማ ቀልሰን
በውሳኔዎች ላይ ፣ አቅቶን መወሰን
ዘር እየገነባን
በልማቱ ምክንያት ፣ ሰዎችን አፍርሰን
ነፃ ወጣን እያልን
ያስተሳሰሩንን ፣ ገመዶች በጥሰን
አለን ህግ አክብረን ፣ አለን ህግ ጥሰን።

አንተ ግን እንዴት ነህ
ምርጫ በሌለበት ፣ ምርጫ ያሳተፍከን
አባባነት እድሜ
ወዛችንን መጠህ ፣ ቀስመህ ያነጠፍከን
ንብ ነህ ብለን ስንቀርብ ፣ ፈጥነህ የነደፍከን
ማሩን ማሩን ስንል ፣ ምሬት ያሳቀፍከን
ግብርህ እየጠፋ ፣ ስምህ የተረፈን
እንዴት ነህ ኢህአዴግ
ምነው ሳንገናኝ ፣ አራት ወር አለፈን?

እኛማ ይኸውልህ 
ማንም ለራሱ ግብ ፣ ጠልዞ ሚሰደን
ከግር ወጣን ስንል ፣ መረብ የሚጠምደን
ኳስ ህዝቦች እንደሆን ፣ ቢገባንም ቅሉ
"ሁሉ ቀርቶልናል" 
ለማለት ባንደፍርም ፣ ባይገልፀውም ቃሉ
ከበፊቱ አንፃር ፣ ጭቆና ቀንሷል
ከበፊቱ አንፃር ፣ ዛሬ ፍቅር ነግሷል
እርግጥ ነው አንክድም
ዛሬም መግደል አለ ፣ 
ከህይወት ያረፈደ ፣ ሞትን ይተኩሳል
አፈ ሙዝ ይመስል...
ደና ነገር ካፉ ፣ አለ የማይወጣው
አልጠፋም አፈናው 
አልጠፋም ዘረፋው ፣ አልጠፋም ረገጣው
ግን ደሞ ግን ደሞ
ከትናንቱ አንፃር ፣ ዛሬ ላይ ቀንሷል
ግን ደሞ ግን ደሞ
ከትላንቱ ዛሬ ፣ ስጋታችን ብሷል ።

የሆነው ሆነና 
እንዴት ነህ ኢህአዴግ ፣ እኛ አለን በደህና
ያመቻቸኸውን ፣ የልማት ጎዳና
ወስነን ለማጥፋት
በጀመርነው መንገድ ፣ በዝቶብን እንቅፋት
አላራምድ ሲለን 
ለአንድ ሀገር መኖር ፣ አንዳንዶች ተገድለን
ለአንዲት ሀገር ፈውስ ፣ አንዳንዶች ቆስለን
እንደ ድሮ ዘንቢል ፣ ተስፋ አንጠልጥለን
ካቆምከው ጨለማ
የምንወጣበትን ፣ ፀሐይ ሐሳብ አዝለን
ካለመኖር መኖር
በሚል አዲስ መንገድ ፣ እኛ እንዳለን አለን።

አንተ ግን እንዴት ነህ ?
ኖረህ እንደሌለህ ፣ የምትናፍቀን
የምትጨልም በቀን
በምርጫ ኮሮጆህ ፣ ልክ እንደበቀቀን
ድምፅ የምትነጥቀን
ከእለት እንጀራ ላይ
የአመት ግብር ቆርጠህ ፣ የምታሳቅቀን
ሁሌ መቶ ፐርሰንት ፣ ተመረጥኩኝ ምትል
ስድስት ጊዜ መድቀህ
አንዴ ስትነሳ ፣ እንደያሬዱ ትል
ፅናቴን እዩልኝ ፣ ትግሌን ተመልከቱ
ብለህ የምትፈርድ ፣ በአመተ ምህረቱ
መረጥጠኝ ያልከው ህዝብ
አንድ ዜሮ አክሎ ፣ ከመቶ ፐርሰንቱ
ሺህ ፐርሰንት ሚጠላህ 
እንደምነህ ኢህአዲግ 
አንድ ሙሉ ትውልድ ፣ ቀርጥፈህ የበላህ?!

እኛማ ይኸውልህ
ለካድሬ ግልምጫ
ለፌደራል ጡጫ
ለአጋዚ እርግጫ 
ማንም ሲያቀብለን
ሞት እንደ ጆሮ ጌጥ ፣ የሚያንጠለጥለን
እንደተፋቀ ካርድ ፣ 
ማንም እየሞላ ፣ የትም የሚጥለን
ጭንቅላት የሌለው
በጁ እንደ ጠብመንጃ ፣ የሚያቀባብለን
ለሞት የታጨ ህዝብ ፣ ብንሆንም ቅሉ
"ሁሉ ነገር ቀርቷል"
ለማለት ባንደፍርም ፣ ባይገልፀውም ቃሉ
ጭቆናው ባይቀርም 
መጣል መረገጡ 
ውጣና ውረዱ ፣ ኑሮ ውጥንቅጡ
ቀርቶልናል ብለን ፣ ለማውራት ባንደፍርም
ከትላንቱ አንፃር
የዛሬ ነፃነት ፣ ሳይሻል አይቀርም
ፌደራሎች ስናይ ፣ አንደነብርም
አንፈረጥጥም ፣ አጋዚ ሲመጣ
ጨርሶ ባይነጋም
የንጋት ተስፋ አለን ፣ ፀሐይ እንድትወጣ።
ጨርሰው ባይጠሩም
ሁሉ እንደትናንቱ፣ አልቀሩም ደፍርሰው
ከተኩላዎች መኋል 
በጎች ተገኝተዋል ፣ 
የተኩላዎችን ለምድ ፣ የኖሩ ተላብሰው።
አንተ ግን እንዴት ነህ ፣ 
እንዴት ነህ ኢህአዴግ
የበግ ለምድ ለብሰህ ፣ በግ የምትጨርሰው?!

እኛማ ይኸውልህ
መቅሰፍት ስንጠብቅ ፣ ምህረት ዘንቦልን
አለን እየፀለይን ፣ እንዳትኖርልን።

No comments