Latest

ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነን - አቢ ጌቱ (Natnael Getu)

ኢትዮጵያዊ ነን

ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነን!!!

አቢ ጌቱ (Natnael Getu) 


አይንጋላችሁ ተብለን ፥ ጸሀያችንን ቢያጠልቁት
ፋኖሳችንን ባህር ውስጥ ፥ እያሰጠሙ ቢያርቁት
ለጨለማው ቀልድ ነግረን ፥ አስቀነው ፈገግ ይላል
የጽልመቱ የሳቅ ፍንጥቅ ፥ ከጻይ ይልቅ ያማልላል
ጨለማውን አናነጋም ፥ ብርሀን ነው እንላለን
ለጨለመች ህይወታችን ፥ ከጽልመት ጧፍ እንሰራለን
ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነን !

ለአርባ ቀናት ዝናብ ቢወርድ ፥ የሰማይ መስኮት ተከፍቶ
ምድሪቷን ውሀ ቢሞላት ፥ ሀያል ፈጣሪ ተቆጥቶ
ልክ እንደ ኖህ አንለፋም ፥ ያቺን ቀን ግን እናልፋለን
አንድም መርከብ ሳንሰራ ፥ አሳ ሁነን እንተርፋለን
ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነን !!!!

ዘጠኝ ሞት ሲደረደር ፥ ከቤታችን መግቢያ በራፍ
አንዱን ግባ ብለን ከፍተን ፥ ከህይወታችን አንድ ምእራፍ
የሞትን ስም እንጽፋለን!
የጻፍነውን መጻፍ ደግሞ ፥ ለጠላቶች እንልካለን :)
ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነን !

በአሽሙር በትር ለሚነካን ፥ በወግ ሆዱን ለሚነፋ
ያላየውን ለሚያወራ ፥ ሀሰተኛ ቱሪ_ናፋ
ልክ እንደ እባብ ተጠምጥሞ ፥ " ልቀፋችሁ ኑ" ለሚለን
ጭንቅላቱን አንመታም !
በቅኔያችን ስውር በለቅ ፥ አይምሮውን እንነካለን
ምክንያቱም ኢትዮጲያዊ ነን

ልጆቻችን አለት አይተው ፥ ተስፋ ቆርጠው ሲተክዙ
ጠላታቸው ሲበረታ ፥ ዶማቸውን እንደያዙ
" ድሮ ድንጋይ ዳቦ ነበር ፥ 
እያቦካን የምንሰራው ፥ የእናታችን የሊጥ ቅጂ
እኛ አክሱምን አልተከልንም ፥ ግዙፍ ሙልሙል ጋገርን እንጂ "
በምንለው ተረታችን ፥ የሰሙንን አሳምነን
ከአለት ጋር እያታገልን
የአለቶችን ጽኑ ብርታት ፥ በአንዲት ተረት እንጥላለን
ከዶማችን ብረት በላይ 
ተረታችን ጠንካራ ነው ፥ ይሄን እውነት እናውቃለን
ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነን

ራብ ሊጥለን ሲመጣ ፥ ሲሞክር ሊበታትነን
በሌማታችን ሳንኮራ ፥ እምነታችንን ቀጥለን
ከተልባ በዳቦ ይልቅ ፥ ተልባ ማሻ አቦን ተማምነን
ስንጠግብ ባናድር እንኳ ፥ ከሞት ሰይፍ እናመልጣለን
ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነን!!

በጉልበቱ የሚበልጠን ፥ የማንችለው በጦር አቅሙ 
ልናፈሰው ያልተቻለን ፥ የወፈረ ትኩስ ደሙ
ቀብራችንን አመቻችቶ ፥ ከጉድጓድ ላይ እንደጣለን
አጋም ሁነን እየበቀልን ፥ ሰውነቱን እንወጋለን
ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነን !

ተደናግጠን አንወድቅም! ፥ ስጋት ደፍሮ አይገድለንም
ሩጫ ላይ አንደኛ ነን ፥ ፈሪዎች ግን አይደለንም
የደቀንነው መዋጊያ ጦር ፥ በጠላት ፊት ቢኮላሽም
የሚያስነውር ድርጊት እንጂ ፥ ሞትን ፈርተን አንሸሽም
በአፍሪካ ቀንድ ብንኖርም ፥ ቀንድ የለንም እንደ ሰይጣን
የነካንን ባላንጣ ግን ፥ አስበርግገን ስንቴ ቀጣን
ጥቁረታችን ምልክት ነው ፥ ከሩቅ አይቶ ለሚለየን
መልካችን ነው ባንዲራችን ፥ ልንቀይረው 'ማይቻለን 
ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነን !!

No comments