በቡኖ በደሌ የተከሰተው ምንድን ነው? ቢቢሲ
ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ በኦሮሚያ ክልል በቡኖ በደሌ ዞን የተደረገ ሰልፍን ተከትሎ በተከሰተው ሁከት እና ግጭት በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ከተለያዩ ምንጭች እየወጡ ያሉ መረጃዎች እስካሁን ድረስ አወዛጋቢ ሆነዋል።
ቢቢሲ ጉዳዩን ለማጣራት እና ተጨባጭ መረጃ ለማግኝት የተለያዩ አካላትን አነጋግሯል።
የበደሌን ከተማን ጨምሮ በዞኑ በተለያዩ ስፈራዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀናት ላይ ሰልፎች ተካሂደው ነበር። ሰልፉን ተከትሎ በተነሳ ግርግር በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አረጋግጠናል።
ከኦሮሚያ እና አማራ ክልል ሃላፊዎች የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በግጭቱ ምክንያት እስካሁን የጠፋው የሰው ህይወት ቁጥር አስራ አንድ ሲሉ፤ ያልተረጋገጡ ምንጮች ግን ቁጥሩን ከዚያ በላይ ያደርጉታል።
ክስተቱን ተከትሎ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመሸሽ በፖሊስ ጣቢያ እና በእምነት ተቋማት ተጠልለው እንደሚገኙ ያነጋገርናቸው ግለሰቦች ገልፀዋል።
በጥቃቱ ንብረታቸው የወደመ እና ለህይወታቸው ሰግተው በዲጋ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች መካከል ቢቢሲ ያናገራቸው ግለሰቦች የትግራይ ተወላጆችም ከሞቱት መካከል ናቸው ቢሉንም፤ የፖሊስ ጣቢያው ምክትል ኮማንደር ሳጅን ኢተፋ መዝገቡ ግን ሟቾቹ ከኦሮሞና አማራ ወገን መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሳጅን ኢተፋ ጨምረው እንደገለፁት በዲጋ ወረዳ ብቻ የ9 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሰባት መቶ የሚሆኑ የትግራይና የአማራ ተወላጆች በፖሊስ ጣቢያው ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ከአቶ ተመስገን አያና የቡኖ በደሌ ዞን የፀጥታና አስተዳደር ጉዳዮች ሃላፊ እንዲሁም ከዞኑ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ሃላፊን አቶ ሌይኩን ተካልኝ ጋር ባደረግነው ቆይታ በበደሌ ከተማ፣ በጮራ እና ዴጋ ወረዳዎች ማን እንደጠራቸው የማይታወቁ ያሏቸው ሰልፎች ተካሂደው እንደነበር አረጋግጠውልናል።
ከፀጥታ ቢሮ እና ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊዎች መረዳት አንደቻልነው በሰልፉ ምክንያት የተፈጠረው ሁከት ወደ ዘረፋ እና ንብረት ማውደም መሸጋገሩን ተናግረዋል።
አቶ ተመሰገን እንደሚሉት ግለሰቦች ንብረታቸውን ከዝርፊያ እና ከጥፋት ለመጠበቅ ሲሉ በከፈቱት ተኩስ አንዲሁም በዞኑ በተለያዩ አከባቢዎች በተፈጠሩ ሁከቶች የ11 ሰዎች ህይወት አልፏል።
የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በቡኖ በደሌ ዞን ጮራ እና ዴጋ ወረዳዎች በተከሰተው ሁከት 8 የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች እና 3 የአማራ ብሔር ተወላጆች መሞታቸውን አረጋግጠዋል።
''ይህን አስነዋሪ ድርጊት እናወግዛለን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለፅን ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን እንመኛለን'' ብለዋል።
አቶ አዲሱ ይህን ጥቃት የሚፈፅሙት እናማን እንደሆኑ በግልፅ ባያስቀምጡም ''የኦሮሚያ ክልል የህዝብን ጥቅም ለማስከበር እየወሰደ ያለው ተግባር ያላስደሰታቸው አካላት ናቸው'' ሲሉ ይገልጿቸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በፌስቡክ ገፃቸው በቡኖ በደሌ የተከሰተውን ግጭት የክልሉ መንግሥት በቅርበት እየተከታተለው እንደሆነ አመልክተው ሟቾቹን በተመለከተ ከአቶ አዲሱ ጋር ተመሳሳይ መረጃ ሰጥተዋል።
አቶ ንጉሱ ጨምረውም ግጭቱን የብሔር መልክ በማስያዝ እውነታውን በማዛባት የሚደረገው ዘገባ የበለጠ ጉዳት እንጂ ሌላ ጥቅም የለውም ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ጥቅምት 11/2010 ለኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ በሰጡት መግለጫ ''በክልሉ እየተስተዋሉ ያሉት ግጭቶችን እናወግዛለን። እንዲህ አይነቱ ድርጊት የኦሮሞን ህዝበ የሚጠቅም አይደለም፤ ፈፃሚዎቹም የኦሮሞ ህዝብ ጠላት የሆኑ ቡድኖች ናቸው'' ብለዋል።
ችግሩን ለመፈታት የክልሉ መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነ አቶ ለማ ጨምረው ተናግረዋል።
No comments