Latest

የኢትዮዽያ አየር መንገድ ያልተሰሙ ጉዶች - ከውስጥ አዋቂዎች



የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ኤርፖርቶች ድርጅት ያለ በቂና ገለልተኛ ጥናት ከአየር መንገዱ ጋር የመቀላቀሉን በማንኛውም መመዘኛ አግባብ ያልሆነ ውሳኔ መሰረት ተጠቂዎች ከሆኑት በርካታ የኤርፖርት ሰራተኞች መካከል አንዱ እንደመሆኔ ይህንና ሌሎች ጉዳዮችን ለህዝብ ይፋ ማደረግ ነው::

የአቶ ሃይለማርያም መንግስት ሊወቀስባቸው ከሚገቡ ብዙ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ይህ በተወልደ በራሱ ዋነኝ ጥናት አቅራቢነት ተመስርቶ ውሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ ሲሆን ይህም ያለፈው የኢሕአዴግ አስተዳደር ለተወልደ የጠቅላይነትና የጠርናፊነት አገዛዝ ምቹ መሳሪያ መሆኑን አንድ ማሳያ ነው::
 

በማንኛውም ጥናት መርህ መሰረት ይህ ጉዳይ በገለልተኛ ወገን እንዲሁም በባለሙያዎች ሳይጠና የመቀላቀሉ ቀጥተኛ ተዋናዮች የኤርፖርቱ ማህበረሰብ ሳይሳተፉበት እንደ ሲቪል አቪየሽን ባለ ስልጣን ያሉ የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤቶች ምንም አይነት ተሳትፎ ሳያደርጉበት ተወልደ ራሱ ከሳሽ ራሱ ዳኛ የሆነበት የውሳኔ ሀሳብን የአቶ ሃይለማርያም ካቢኔ አፅደቆ ያለ በቂ ዝግጅት በድንገት የመቀላቀሉ ጉዳይ እውን ሊሆን ችሏል::

በኤርፖርቶች ድርጅት ከፍተኛ አመራር ከሚባሉ ሰዎች ውስጥ አንዱ የነበርኩ ሲሆን አየር መንገዱ በእኔ ላይ እንዲሁም በሌሎች ሰዎች ላይ የሚያደርሳቸውን በተጨባጭ ያረጋገጥኳቸውን ጉዳዮች ላካፍላችሁ እወዳለሁ:: ከዩኒቨርሲቲ ተመርቄ በተማርኩበት የሙያ መስክ በኤክስፐርትነት ደረጃ በኤርፖርቶች ድርጅት ከተቀጠርኩበት ቀን ጀምሮ በተለያዩ ደረጃዎች አገልግዬ ለሃላፊነት ከውስጥ አድጌ ድርጅቱን በቅንነት እያገለገልኩ ነበር::
 

የውህደቱ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ እኔን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ሃላፊዎች ሙያችንንና ደረጃችንን በማይመጥን ሁኔታ በተወልደ ውሳኔ (በነገራችን ላይ የውህደቱ ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ተወልደ ተሰጥቶት የነበረው መመሪያ (በኋላም ተወልደ የኤርፖርቶችን ሰራተኞች ሰብስቦ በግልፅ ቃል የገባው) ማንም ሰራተኛ በውህደቱ ምክንያት እንደማይቀነስ ሲሆን አሁን የምነግራችሁ ጉዳይ ግን ከስራ ተቀንሰን የሚገባንን የካሳና ሌሎች ክፍያዎች ተከብሮልን ከድርጅቱ ብንሰናበት እጅግ የሚሻል ነበር) አየር መንገዱ ያለምንም መመዘኛ(በብቃት እና ስነምግባር ቢሆ ኖሮ የኤርፖርት ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነው እና በብሄር መለኪያ ብቻ ቦታውን ይዞ ከውህደቱ በኋላም የቀጠለው ሰው እርምጃ በተወሰደበት ነበር) ከነበረኝ ደረጃ አንስተው እጅግ ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ የመንገደኞች ረዳት (Passenger Assistant) የስራ መደብ መድበውኝ ከሌሎች በርካታ ተጠቂ ባለደረቦቼ ጋር በመሆን ኤርፖርት ውስጥ ለመንገደኞች ያልጠፋቸውን ሽንት ቤትና ካፌ አመላካች አድርገውኝ አረፉ:: የዚህ ጉዳይ ሰለባ እኔ ብቻ ሳልሆን በርካቶች ስለሆኑ ከነዚህ ሰራተኞች በቀላሉ ማረጋገጥ የሚቻል እውነታ ነው::

በሌላ በኩል በኤርፖርቶች ስራ ከማውቃቸው የአየር መንገዱ ሰራተኞች÷ በሃላፊነት ካሉ የኤርፖርቶች ሰራተኞች÷ እንዲሁም ከተቆጣጣሪው ባለ ስልጣን የኢትዮዽያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ሰራተኞች ጋር ባለኝ የስራ ቅርርብ ምክንያት ያየኋቸውና ያረጋገጥኳቸው መረጃዎች የሰውዬውን (ተወልደ) የማናለብኝነት አሰራር ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው::
አየር መንገዱ በሚገዛበት የልማት ደርጅቶች ህግ መሰረት አንድ የድርጅት ስራ አስፈፃሚ የስራ ሃላፊዎችን በሚሾምበትና በሚሽርበት ጊዜ ለቦርዱ አሳውቆ የማስጸደቅ ግዴታ የሚጥልበት ቢሆንም ሰውዬው ግን በማናለብኝነት ለኔ በቀላሉ ይታዘዙልኛል አይቃወሙኝም የሚላቸውን አቋም አልባ የስራ አስፈጻሚዎች ያለማንም (በተለይም ስልጣን ባለው የአየር መንገድ ቦርድ) ይሁንታና አፅዳቂነት ይሾማል የሾማቸውንም በራሱ በሆነ እጅግ ግብዛዊ ውሳኔ (አሁንም ለማንም አካል የማስረዳት  የማማከር ወይም የማስወሰን ሂደት ውስጥ ሳይገባ) ይሽራል::
 

ለአብነት ባለፉት 3 አመታት ብቻ የሰው ሃብት አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ቦታ የተለያዩ ግለሰቦች (ኤልሳቤጥ ጌታቸው መሳይ ሽፈራው አዚዛ መሐመድ ዋሲሁን አስረስ እንደገና መሳይ ሽፈራው) እየተፈራረቁበት ይገኛሉ::
በሌላ በኩል የሚሾሙት የስራ ሃላፊዎች በአብዛኛው በብሄር የተመረጡ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ተወልደን የመሞገት እድልና መብት የላቸውም::የስራ አስፈጻሚዊቹ ሰለ አጠቃላይ የአየር መንገዱ ሁኔታ የሚተላለፉ እጅግ ከፍተኛ ተፅእኖ (Consequences) ያላቸው ውሳኔዎች ውስጥ ምንም አይነት ድርሻ የላቸውም:: 

የሁሉም ጉዳዮች የሃሳብ አመንጪ አርቃቂና አፅዳቂ ተወልደ ብቻ ሲሆን የስራ አስፈፃሚዎቹ በራሳቸው ክፍል ላይ እንኳን ያለሱ ፍቃድ የረባ ውሳኔ እንዳያሳልፉ ሽባ አድርጓቸዋል:: ለዚህም መሰለኝ እነዚህ ስራ አስፈፃሚዎች በአየር መንገዱ ሰራተኞች “follow-me” የሚል ቅፅል ስም የተሰጣቸው (follow-me በጉዞ ወቅት መንገደኞች ወደ አይሮፕላኑ ውስጥ ይዘዋት የሚገቡት አነስተኛ ሻንጣ ናት):: አየር መንገዱ በየሳምንቱ አርብ አርብ የሚያደርገው የማኔጅመንት ስብሰባ (WST) ተወልደ ከራሱ ጋር የሚያደርገው “shouting match” የሆነው ለዚህ ነው::
የአየር መንገዱ ቦርድ ሆን ተብሎ ተወልደን በማይቃወሙና የራሳቸው ችግር ሰለባ በሆኑ ሰዎች የተደራጀ ነው:: ላለፉት አመታት የቦርድ ሰብሳቢው አቶ አባዱላ ገመዳ ሲሆን አቶ አባዱላም ስለአቪየሽን ኢንደስትሪ ይቅርና ስለቢዝነስ ተቋማት አሰራር “ጨዋ” የሆነ ግለሰብ ከመሆኑም በተጨማሪ ይህ ሰው ብልጣብልጡ ተወልደ ወስኖና ፈፅሞ የሚያመጣለትን ሃሳብ ለመሞገት እንዲሁም በርካታ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስበት የህዝብ ሃብት በአንድ ሰው ግብዛዊ ውሳኔ እንዳይባክን ለመቃወም የእውቀትም የሞራልም ዝግጁነት እንደሌለው ግልፅ ነው:: 

በተለምዶ እንደምናውቀው በቦርድና በስራ አስፈፃሚው መካከል ያለው ተቋማዊ ግንኙነት ቦርዱ ለስራ አስፈፃሚው ስራ እንቅፋት ሳይሆን ነገር ግን እያንዳንዷን ስትራቴጂካዊ ውሳኔ የመሞገት ለዝርዝር ጥናት የመላክ ውድቅ የማድረግ መሆን ቢኖርበትም በተጨባጭ ግን የቦርዱ ሚና የተወልደን ውሳኔ ህጋዊ (Legalize) ከማድረግ የዘለለ አይደለም::
 

ውሳኔዎች ለቦርድ ሲቀርቡ ተቃውሞ እንደማይገጥመው ስለሚታወቅ ድርጅቱ በተወልደ ውሳኔ አስቀድሞ ወደ አፈፃፀም ከገባ በሗላ ነው ለማጸደቅ የሚቀርበው:: ተወልደ ማንም ሳያውቅ (በተለይ በቀጥታ የሚመለከተው ክፍል) ተደራድሮ እና ኮሚሽኑን ከቦይንግ ወይም ኤርባስ ወስዶ በSwiss  ባንክ አካውንቱ ካደላደለ በኋላ ቦርዱ በየወሩ እየተሰበሰበ የአውሮፕላን ግዥ ሲያጸድቅ ይውላል:
:
አየር መንገዱ ከሚያነሳቸው የስኬት ምንጮች አንዱ በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እየተሳተፈባቸው ያሉት አክስዮን በመግዛት ሌሎች አየር መንገዶችን የማቋቋም ስራ ለሚድያ ፍጆታ የሚውል የወሬ ርእስ ከመሆን ባለፈ ለአየር መንገዱም ሆነ ባለቤቱ ለሆኑት የኢትዮዽያ ህዝብና መንግስት ያስገኙት ትርጉም ያለው ጥቅም የለም::
 

በቅርብ ጊዜ እየተቋቋሙ ያሉት የሞዛምቢክ÷ ዛምቢያ÷ ቻድና ጊኒ አየር መንገዶችን እንተውና (እነዚህ ለወሬ የሚበቃ ፋይዳ እንኳን የላቸውም)  በኢትዮዽያ አየር መንገድ ከተቋቋሙ ከአምስት አመት በላይያ ስቆጠሩትና የኢትዮዽያ አየር መንገድ ግማሽ ፈር የድርሻ ባለቤት የሆነባቸው የማላዊ አየር መንገድና የቶጎ አየር መንገድ አፈፃፀም ብናይ÷ ማላዊ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት በኪሳራ ውስጥ ያለ አየር መንገድ ሲሆን የማላዊ መንግስት ባለስልጣናትና የፓርላማ አባላት ከኢትዮዽያ አየር መንገድ ጋር የተደረገው የትብብር ስምምነት ምንም አይነት ጥቅም ባለማምጣቱ ግንኙነቱን ደግመን ልናስብበት ይገባል በሚል በርካታ ጥያቄዎችን እያነሱበት ሲሆን÷ የቶጎ አየር መንገድም ቢሆን ምንም እንኳን ኪሳራ ውስጥ ባይሆንም ያወጣውን ወጪ ያህል ገቢ ለማስገባት ዳገት ሆኖበታል::
 

የእነዚህ አየር መንገዶች አፈፃፀም ላይ የሚነሱትን ቅሬታዎች በቀላሉ ጎግል በማድረግ አንባቢ በይበልጥ ሊረዳ ይችላል:: ሌላው ጆሮአችን እስከሚደነቁር (በነገራችን ላይ አየር መንገዱ ሽልማቶችን (Awards) በግዥ እንደሚያገኝ የአደባባይ ሚስጥር ነው) በየቀኑ በሚባል ደረጃ አየር መንገዱ የተጋነነ ውጤታማ ጉዞ ላይ እንደሆነ አድርጎ የሚያስነግረው ዜና ሲሆን በእኔ እምነት አየር መንገዱን ወይም የስራ ሃላፊዎቹን ከማወደሳችን በፊት (በእርግጥ መካድ የሌለብን አንድ እውነት ዋና ስራ አስፈፃሚው ተወልደ ግብዝነቱና እኔ ብቻ አዋቂ ባይነቱ እንጂ በአየር መንገዱ ውስጥ ከሻንጣ ተሸካሚነት እስከ ኤርያ ማናጀርነት ረጅም ዘመን ከማገልገሉ አንፃር የአየር መንገድን ቢዝነስ በቂ መረዳት አለው ባንል ፍትሃዊ አይሆንም)
 

አየር መንገዱን እንደ ብቸኛና አይነኬ ልጅ በመቁጠር ከዚህ ቀጥሎ በትንሹ የምንመለከታቸውን ያልተገደቡና ኢፍትሃዊ የሆኑ ዘርፈ ብዙ የድጋፍ ማእቀፎችን ማስታወስ ያስፈልጋል:- አየር መንገዱ ምንም አይነት የንግድ ትርፍ ግብር÷ የጉምሩክ ቀረጥ÷ እንዲሁም የቴምብር ቀረጥ አይከፍልም ሀገር ውስጥ ያሉ አየር መንገዶች በሀገር ውስጥ ገበያ እንኳን ከአየር መንገዱ ጋር መወዳደር እንዳይችሉ አፋኝ የሆኑ የህግና የአሰራር ስንክሳሮች ተጥለውበታል (ይህንን በተወሰነም ደረጃ ቢሆን ተቆጣጣሪው የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ለማስቀረት በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ተወልደ ከላይ ያሉ ሰዎችን በመላክ ባለስልጣኑ እጅና እግሩን አጣጥፎ እንዲቀመጥ ተደጋጋሚ ተግሳፅ ይደርሰዋል÷ ይህንንም ጉዳይ በተመለከተ የባለስልጣኑን ሃላፊዎች ቀርቦ ማረጋገጥ ይቻላል)
 

በውጭ ሀገር ያሉ አየር መንገዶችም ወደ ኢትዮዽያ የበረራ አገልግሎት እንዲጀምሩ ወይም ነባሮቹ ደግሞ ተጨማሪ የትራፊክና የበረራ መብት ለማግኘት የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንን ሲጠይቁ ተወልደ ጣልቃ በመግባት ባለስልጣኑ በህግ የተሰጠውን ሃላፊነት አንዳይወጣ አድርጎታል:: በዚሁም መሰረት በቀጥታ ሌሎች አየር መንገዶችን ያገለለና ጥቅም ያሳጣ አሰራር ከመሆኑም በተጨማሪ ህዝብና መንግስትም በፍትሃዊ የገበያ ፉክክር ሊያገኙ ይችል የነበረውን ጥቅም አጥተዋል::
አየር መንገዱ መንገደኞችን ከማመላለስ ባሻገር የምግብ ማቅረብ (Catering) አገልግሎት÷ እንዲሁም የምድር ላይ አገልግሎት (Ground Handling) ስራዎችን የሚሰራ ሲሆን÷በነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ የግል ባለሃብቶች ላይ ያለአግባብ ተፅእኖ በማድረግ ገበያውን እንዳይፎካከሩት የማይፈነቅለው ድንጋይ የሌለ ሲሆን የግል ባለሃብቶችን ማንኛውም አካል ቀርቦ ቢያናግር እዚህ የተገለፀው ጉዳይ በእጅጉ ያነሰው እንደሚሆን አልጠራጠርም::
በሌሎች የመንግስት የልማት ድርጅቶች እንደተለመደው ድርጅቶቹ ከሚያገኙት ገቢ ውይም ትርፍ ለመንግስት ፈሰስ ያደርጋሉ:: ለምሳሌ የባቡርን ፕሮጀክት እዳ የሚከፍለው የኢትዮ ቴሌኮም ፈሰስ ነው እንደሚባለው ማለት ነው:: አየር መንገዱ ግን ለመንግስት ሰባራ ሳንቲም ፈሰስ አያደርግም:: ስለዚህ የኢትዮዽያ ህዝብና መንግስት በአየር መንገዱ (ቢያንስ በቀጥታ) ምንም አይነት ተጠቃሚዎች ካለመሆናቸውም ባለፈ ጭራሽ የሁሉም ዜጋ ግዴታ የሆኑትን ግብርና ታክስ ሳይቀር ነፃ ተደርጎ የሚያገኘውን ገንዘብ ያለከልካይ ይጠቀምበታል::

አየር መንገዱ የትርፍ ሰዓትና ሌሎች ተያያዥ ክፍያዎችን ለሰራተኞቹ ይከፍላል ከተባለ ተዓምር ነው:: የአየር መንገዱ ሰራተኞች ካለባቸው ከፍተኛ የስራ ጫናና ዘርፈ ብዙ ሃላፊነቶች አንፃር አየር መንገዱ ለሰራተኛው የሚከፍለው ደመወዝ ከሌሎች አየር መንገዶች አንጻር እጅግ ዝቅተኛ ሲሆን÷ በሌላ በኩል ሰራተኛው እንደ መብት ሊያነሳቸው የሚችላቸው የትርፍ ሰዓት ክፍያዎች አይከፈሉትም÷ ስራውን በትርፍ ሰዓቱ ሰርቶም ቢሆን ካልተወጣ ደግሞ የማያዳግም እርምጃ ይወሰድበታል::

ከላይ በጨረፍታ ያነሳኋቸውን መነሻ ሃሳቦች ከግምት ውስጥ በማስገባት የህዝብና የመንግስት ሃብት ከዚህ በላይ እንዳይባክን÷ዜጎች በፍትሃዊነት የመቀጠርና የመስራት እንዲሁም የስራ ዋስትና የማግኘት መብት በድርጅቱ ውስጥ እንዲኖራቸው÷ ዋና ስራ አስፈፃሚው ተጠያቂነትና ከቦርዱ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ የስልጣን ተዋረድ ያለበት ስራ እንዲሰራና ተቆጣጣሪ አለኝ ብሎ እንዲያምን የሚያስችል ተቋማዊ ባህል እንዲሰፍን÷ የአየር መንገዱን ህልውና ለመታደግ÷ ሌሎች የኢንደስትሪው ተዋናዮች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል÷ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ ስልጣኑ ያላቸው አካላት ጉዳዩን በሚገባ መርምረው አፋጣኝና የማያዳግም እርምጃ ሊወስዱ ይገባል::

ድል ለብዙሃን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ለጎለበተ ተቋማዊ አሰራር!!!

No comments