Latest

ኤች አር 128 ዋጋው ስንት ነው? በኦላና ኬኔ



የአሜሪካ ኮንግረስ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባሳለፈው ኤች አር 128 የውሳኔ ሀሳብ ላይ ነፃ የግል አስተያየት በኦላና ኬኔ፤ በፅሁፉ ውስጥ የተነሱት ሀሳቦች ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን አይወክሉም/

የአሜሪካ የኮንግረንስ አባላት ያቀረቡት ኤች አር 128 አልፏል። አንዳንዶቹ ይህ የውሳኔ ሃሳብ በአሜሪካ መንግስት የተጣለ ያደርጉታል፤ ስህተት። አሜሪካ የብዙ ተቋሞች ድምር ናት። ኮንግረንስ፣ ሴኔት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋይት ሃውስ ወዘተ. እነዚህ ተቋማት አንዱ ሌላውን እየተቆጣጠረ ይሰራል።

የአንዱ ውሳኔ የሌላው አይሆንም። ኤች አር 128 የስራ አስፈጻሚው ወይም የትራምፕ ውሳኔ ባለመሆኑ ትርጉም የለውም። ውሳኔው በኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት ምን ተጽዕኖ አለው የሚለው መታየት ይገባዋል። መልሱ ምንም ነው። እኛ የምንፈልጋቸውን ያክል እነሱም ይፈልጉናል።

የሁለቱ አገሮች ግንኙነት
የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግኑኝነት ትናንት የተጀመረ አይደለም። እድሜ ጠገብ ነው። የአገሪቱ ቱባ ባለስልጣናት ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። ባራክ ሁሴን ኦባማ፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ፣ ጀምስ ኤርል ካርተር፣ ሂላሪ ክሊንተን፣ ጆን ኬሪ፣ ኮንዶሊዛ ራይስ፣ ማድሊን ኦልብራይት፣ ሬክ ቲሌርሰን ተጠቃሾች ናቸው።

ሁለቱ አገሮች በዓለም አቀፍ የፀረ ሽብር ትግል (Counter terrorism)፣ በአፍሪካ ቀንድ የፀጥታ ሁኔታ እና የዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር እንዲሁም በልማት፣ መልካም አስተዳደር እና ዴሞክራሲ ማስፈን በኩል በጋራ ይሰራሉ።

አገራቱ በዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብት፣ ሰላም እና ደህንነት እንዲሁም በኢኮኖሚ ንግድ እና ፋይናንስ የሚመክሩባቸው መደበኛ መድረኮች አሏቸው። ለዚህም ንዑስ የስራ ቡድኖች (Three Working Groups) ተቋቁመው ስራውን ያከናውናሉ። ይህ አሰራር ሁለቱ አገሮች ስለፈለጉት የሚካሄድ ነው።

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ግንኙነቱን ለማሳደግ እንቅስቃሴዎች ይታያሉ። በተለይም በአሜሪካ ፖለቲካ ተጽዕኖ ካላቸው ከሴኔትና ኮንግረንስ አባላት ጋር የሚደረገው ምክክር ከዚህ ቀደም ከነበረው ከፍ ብሏል። በጋራ ጉዳዮች ላይ ተደጋጋሚ ግንኙነቶችና ውይይቶች ይደረጋሉ።

አሜሪካ ልበ ቡቡ ወይስ. . .
በዲፕሎማሲ የተለመደ ይትብሃል አለ፥ ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የለም። ሁለቱ አገሮች የሚፈላለጉት ለጽድቅ አይደለም። ለአገራቱ አንዳች ጥቅም እስካገኘ ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ናት። እኛ የምንፈልጋትን ያህል አሜሪካም ትፈልጋናለች።

በአደጉ አገሮች፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ሰብዓዊ መብት ወዘተ የሚባሉት፥ የጥቅም ማስጠበቂያ ቁማሮች እንጂ ለአንዱ አገር የሌላው አገር ህዝብ አንጀቱን በልቶት አይደለም። በሺዎች ከሚቆጠር ማይል እርቀት ላይ ሆኖ ደረስኩልህ የሚለው የራሱ የሆነ የሂሳብ ቀመር ስላለው ነው።

አሜሪካም እንደሌሎች መሰል አገሮች ጨዋታውን ትጋራዋለች። በቅርቡ ዶናልድ ትራምፕ በትረ ስልጣናቸውን እንደያዙ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ያደረጉት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ነው። ሳዑዲ አረቢያ የሰብዓዊ መብት ይገፈፍባታል፣ ዴሞክራሲው በበሯ አያልፍም ተብላ ወቀሳ የሚደርስባት አገር ነች። በሞት ቅጣት ላይ እጇ የማይሳሳው ሳዑዲ፥ እንደ ኦሳማ ቢንላደን አይነቶቹ ቱጃር አሸባሪዎች የሚፈልቁባት ናት። ይሁን እንጂ ሳዑዲ አረቢያ የአሜሪካ ሁነኛ ሸሪክ ናት።

የአገሮች ግንኙነት የሚወሰነው የሰብአዊ ጥሰት መኖር አለመኖር አይደለም። እከከኝ ልከክልህ እስከሆነ ድረስ ነው። የማይወራረድ ልገሳም ሆነ ሙገሳ የለም።

የኮንግረንሱ የውሳኔ ሃሳብና እንድምታው
አንዳንድ የኮንግረስ አባላት የኤች አር 128 በሚል የውሳኔ ሃሳብ አቅርበው አሳልፈዋል። የውሳኔ ሃሳቡ ዋነኛ አቅራቢዎች የኒውጀርስ ምክር ቤት አባል ክሪስ ስሚዝ እና የኮሎራዶው ሚክ ኮፍማን ናቸው። ግለሰቦቹ የኢትዮጵያ መንግስትን ለሚቃወሙ አክራሪ የዳያስፖራ አባላት አንደበት ናቸው ይባላሉ። የአሜሪካው አና ጎሜዝ የሚሏቸው ብዙ ተንታኞች ናቸው።
 

የኮንግረስ አባላቱ የኢትዮጵያ መንግስት የተሃድሶ (Reform) እርምጃ እንዲያደርግ ለማስገደድ በሚል የውሳኔ ሃሳብ እንዲያልፍ ተደርጓል ይሉናል። ማንን ነው የሚያስገድዱት?! ግለሰቦቹ ስለ ኢትዮጵያውያን ታሪክ ያገላበጡ አይመስለኝም፤ እ.ኤ.አ 2012 አሜሪካ ከሰሀራ በታች ያሉ አገሮችን በተመለከተ የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ ለዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ እና ሰብዓዊ መብቶች መከበር ትኩረት ይሰጣል ይላል። የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ ይጠይቃል። እስከማውቀው ድረስ ይህ የኢትዮጵያ መንግስትም አቋም ነው።

የውሳኔ ሃሳቡ የሰብዓዊ መብት ማክበርን መደገፍና አሳታፊ የአስተዳደር ስርዓት እንዲኖር መደገፍ የሚል ነው። መልካም ሃሳብ። እነዚህን ጉዳዮች ካየናቸው ምንም ችግር የላቸውም፤ ምክንያቱም መንግስት የሰብዓዊ መብት እንዲከበር አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓት እንዲኖር ከነጉድለቶቹም ቢሆን እየሰራ በመሆኑ።

እንደ እኔ እምነት የውሳኔ ሃሳቡ ባይወጣ ነበር ትልቅ ብቻ ሳይሆን ሰበር ዜና መሆን የነበረበት። ምክንያቱም የውሳኔ ሃሳብ ማመንጨት የተለመደ የምክር ቤቱ አሰራር ነው። በአመት ውስጥ በሺዎች በተለያዩ ጉዳዮች ሃሳብ ያወጣል። በያዝነው በጀት ዓመት ብቻ ከ7 ሺህ በላይ አውጥቷል። የውሳኔ ሃሳቡ ስለአገር፣ ግለሰብ፣ ቡድን፣ ውሃና አየር ሊሆን ይችላል። የምክር ቤቱ አባላቱ የሙሉ ጊዜ ስራ ይሄ ነው። እ.ኤ.አ. በ2016 H.R 861 በሚል መውጣቱ ይታወሳል። እንዳለ ቆርጦ መቀጠል ይበዛዋል። ርዕሱ ሳይቀር ተመሳሳይ ነው።

H.R. 128 በኮንግረንሱ እንዲያልፍ ተደርጓል። ይህ ማለት ግን መንግስት አፅድቆታል ማለት አይደለም። የውሳኔ ሃሳቡ አሁን ካለበት በላይ የመሄድ አቅም የለውም። አበቃ። ምንም ህጋዊ ተጽዕኖ የለውም።

ይህ የውሳኔ ሃሳብ የአሜሪካ መንግስት ማዕቀብ እንዲጥል ያስችለዋል ቢልም ከእውነት የራቀ ነው። ውሳኔው ተምሳሌታዊ (Symbolic) ነው። የሚያመጣው ለውጥ የለም። ህግ ሆኖም አይፀድቅም። ማዕቀብ የሚሆን ነገር የለውም። ለስራ አስፈፃሚው አይቀርብም፣ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር አያውቀውም።
 

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬነር በቅርቡ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ያረጋገጡት ይህንኑ ነው። ክሪስ ስሚዝ እና ተባባሪ አባላት፣ እኛ የምናየው እንደዚህ ነው የሚል መልዕክት ከማስተላለፍ የዘለለ ፋይዳ የለውም። ውሳኔው እሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ያሉ ኢትዮ-አሜሪካውያን መራጮችን ለማስደሰት የቀረበ ገጸ-በረከት ነው። ከዚያ ውጪ የተጻፈበትን ቀለም ያህል ዋጋ የለውም።

የውሳኔ ሃሳቡ ጉድለቶች

በውሳኔ ሃሳብ የተሳሳተ ለመሆኑ ማሳያዎችን መጥቀስ ጠቃሚ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይነሳ ይላል። የምዕራቡ ዓለም አጋራቸው ፈረንሳይ፥ ተመሳሳይ አዋጅ አውጥታለች፤ ማንም የተናገራት የለም። ይህ ፍርደ ገምድልነት ይታይበታል። ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ እንዲሁም በላቡ ያገኘው ሃብት እንዳይወድም መንግስት የሚወስደው እርምጃ ነው። ባይነሳ እንኳ ይህ የኢትዮጵያውያን ብቻ መብት ነው። አንዳንዶቹ የሚያነሷቸው ጉዳዮች ከሶስት ዓመታት በፊት የተፈቱ ናቸው። ያለፈባቸው (Outdated) ናቸው። ይህ የመረጃ ጉድለት ሳይሆን ንዝህላልነት ነው። ኢትዮጵያውያንን መናቅም ነው።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ከተቃዊሚ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸውን በጎ መስተጋብሮች የዘነጋ ነው። ውሳኔው በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር አዎንታዊ ጠቀሜታ የለውም። የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብቶች ተለይተው እና ተነጥለው የሚታዩ አይደሉም። መንግስት በእነዚህ መስኮች ረዥም ርቀት ሄዷል። የትምህርት፣ የጤና፣ የመሰረተ ልማት ወ.ዘ.ተ ተደራሽነትን ለማስፋት ሰፊ ተግባር አከናውኗል።

የኢትዮጵያ መንግስት የተለያዩ ህጎችን በማውጣት ተቋማዊ አቅሙን ለማጎልበት እየሰራ ነው። የሰብዓዊ መብቶችና የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋማት እንዲጠናከሩ ሰርቷል። አሁንም ብዙ ይቀረናል።

አገራችን በቅርቡ የተለያዩ አዳዲስ ኩነቶችን አስተናግዳለች። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ለአገሪቱ መረጋጋት ይበጃል በሚል በራሳቸው ፈቃድ ከስልጣን ለቀዋል። ይህ በአፍሪካም ሆነ በአገራችን ታሪክ እምብዛም የተለመደ አይደለም። አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትሯንም ሾማለች ። በማግስቱ በርካታ ታራሚዎች ተፈተዋል፤ የኢንተርኔት አገልግሎትም ተለቋል ።

እነዚህ ለውጦች በመኖራቸው በአገራችን የጠፋው የሰው ልጅ ውድ ህይወትና ከ40 ሺህ በላይ ወጣት ተሰማርቶበት የነበረው የንብረት ማውደም አባዜ ቆሟል። በመሆኑም እርምጃው ለአገሪቱ መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። አገራችን የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ደፋ ቀና እያለች ነው።
ኢትዮጵያ ጣልቃ ገብ አያስፈልጋትም፣ ኢትዮጵያውያንም የሌላ አገርን ጣልቃ ገብነት አናስተናግድም። አይፈቅድምም። ይህ ባህሪ አገራችንን ከሌሎች አገሮች ለየት ያደርጋታል።

ኢትዮጵያ ለአሜሪካም ቢሆን ትምህርት ሊሆን የሚችል የራሷ አኩሪ ታሪክ አላት። የውስጥ ተጋላጭነት ለውጩ አመች ለም አፈር ነው። ለም አፈር ላይ የፈለጉትን ለመዝራት ይመቻል። ይህም ቀደም ሲል የተተነተነ ነው። በመሆኑም የውስጣችን ችግር በራሳችን እንፈታለን። ሌላ ጠበቃ አያስፈልገንም። ሞግዚት አንፈቅድምም።

ያም ሆነ ይህ እንደኢትዮጵያዊነቴ ሳስበው፡ የኮንግረንሱ የውሳኔ ሃሳብ የመጻፊያውን ብዕር ያክል ዋጋ የለውም። እነሱ አስተያየት የመስጠት መብት አላቸው። የመናገር ነጻነት አላቸው እኛን ተክተው ግን ሊስሩ አይችልም። ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ናት።

ከውሳኔው ምን ይጠበቃል?
ውሳኔው ቢያልፍም በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ ለውጥ አያመጣም። ውሳኔው ኢትዮጵያና አሜሪካ ሁለገብ ትብብር ከማድረግ አያግዳቸውም። አንዳንድ ወገኖች የግላቸውን ፍላጎት ለማሟላት ተራ የሚድያ ጨዋታ ሊሰሩበት ቢፈልጉም ሃቁ ይሄ ነው። ከመልካም ወዳጅህ ጋር ያለህን ግንኙነት ጥሩ ለማድረግ አስተያየት ቢመጣ ጉዳት የለውም።

ኢትዮጵያም እንደ አገር ከአሜሪካ ሆነ ከሌላ ወዳጅ አገሮች የሚሰጣትን አስተያየት እስከጠቀማት ድረስ በበጎ ትወስዳለች። የማይጠቅማትን ደግሞ ወደ ጎን በመተው በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ እንደተለመደው በጋራ ትሰራለች። ሳትወድ የምትጋተው አንዳችም ነገር የለም። ይህ አቋሟ የጸና ለመሆኑ በተለያዩ ጉዳዮች በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ ነው። ያም ሆነ ይህ ሁለቱ አገሮች የጋራ ጥቅሞች አሏቸው።
 

በግለሰቦቹ ጫጫታ የሚፈጠር ነገር የለም። የአንዳንድ የኮንገረንስ አባላት የተለመደ ጩኸት ከአገራቱ መሰረታዊ የጋራ ግንኙነት ጋር የሚጠጋጋ ሳይሆን የሚላተም ነው። የኮንግረንስ አባላት ጨዋታና የአገራቱ ወቅታዊ ግንኙነት አራምባና ቆቦ ነው።

No comments