Latest

የከንቲባነቱ ሹመት (ደረጀ ሐብተወልድ)


ይህ ለለውጡ “ሆ!”ብሎ በልዩ ፍቅር የወጣው የአዲስ አበባ ነዋሪ ቢያንስ ከንቲባውን የመምረጥ መብቱ ሊጠበቅለት ወይም ሊከበርለት ይገባል።

ሹመቶችን አስመልክቶ ከወዲሁ ቅሬታዎች እየተሰሙ ባሉበት ወቅት ” የአዲስ አበባ ከንቲባነት ከኦህዴድ ውጭ አይሆንም” የሚለውን የሕወሓት ዘመን አሠራር ማስቀጠል ፍትሀዊ አይደለም። በሕወሓት ዘመንማ ጠቅላይ ሚኒስትርነትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ከሕወሓት ውጭ አይታሰብም ነበር።ዛሬ ዕድሜ ለሕዝብ ትግል ሕወሓት ለዓመታት “አልለቅም” ካለበት ቦታ ተገፍቶ ለቋል። ወርዷል።

ታዲያ ከሕወሓት ጠቅላይ ሚኒስትርነትንና ሌሎች ታላላቅ ቦታዎችን ያስለቀቀው ኦህዴድ፣ ቢያንስ የመዲናዋን ከንቲባነት ቦታ ለሌሎች የማይለቅበት ምክንያት ምንድነው?

ዛሬ የኦህዴዱ ሰው በምክትል ከንቲባነት የተሾሙት፣ የምክር ቤት አባል ስላልሆኑ ተብሎ ተነግሯል። ያም ሆኖ እስከመጪው ምርጫ ድረስ ከንቲባ ሆነው ያገለግላሉ ተብሏል ። እርሳቸው ከውጭ መጥተው የተሾሙት፣ከምክር ቤቱ ውስጥ የእርሳቸውን ያህል ብቃት ያለው ሰው ጠፍቶ ነው? ወይስ የኦህዴድ አባል ስላልተገኘ?

ከምክር ቤት አባል ውጭ ብቃት ያለው ተፈልጎ ከሆነስ፣ ከዛሬው ተሿሚ የተሻለ ብቃት ያላቸው ሰዎች ከሌሎች ፓርቲዎች ማግኘት ስላልተቻለ ነው?

እንደ እኔ ሃሳብ፣በመዲናዋ ከንቲባነት ቦታ ላይ ከተቻለ ከፖለቲካ ውጭ የሆነ ሙያዊ ተሿሚ የሚቀጠርበት አሠራር ይፈጠር።አይ፣ የብሔር ተዋጽዖው ሹመት መቀጠል አለበት ከተባለ ደግሞ ኦሕዴድ ቢያንስ ይህን ቦታ ይልቀቅ።

ጀነራል ብርሃኑ ዱላ ሰሞኑን ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የመከላከያ የታችኛው ክፍል የተመጣጠነ ቢሆንም፣ በላይ በአዛዦች ዘንድ ግን እስካሁን ሊመጣጠን እንዳልቻለ መግለፃቸውን አንብቤያለሁ።የዚህ ምክንያቱ ቀደም ባሉት ዓመታት ሕወሓት የራሱን ሰዎች ብቻ በጀነራልነት ሹመት ማንበሽበሹ ነው።እነሆ የዚያ አሠራር ችግር ዛሬ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለአዲሱ አመራርም ጭምር ተርፏል።

በዚህ ረገድ ሕወሓት የፈጠራቸውን ችግሮች መቅረፍ ባልተቻለበት ሁኔታ፣ መሪውን የያዘው ኦህዴድ ሌላ ተመሣሳይ ችግር እንዳይደርብብን ያሰጋል።

የዚህ ዐይነት ችግሮች እንዲቀረፉ ፣ በመከላከያው፣በደህንነቱም ሆነ በፌዴራል ተቋማት ፍትሀዊ የስልጣን ክፍፍሎች እንዲደረጉ ሕዝብበተስፋ ሰንቆ እየጮኸ ባለበት ወቅት፣ ሕወሓታዊ አሠራር ማስቀጠል የትም ስለማያደርስ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል።

በዚህ ጉዳይ እንዳንወያይ በሀጫሉ ጉዳይ ሰረቁን።

No comments