አዲስ አበባ ላይ የሚደረግ ሹም ሽር (መሳይ መኮንን)
አዝማሚያው ጥሩ አይደለም:: ተስፋ አድርጎ ከዳር እስከዳር ድጋፍና ፍቅር እየሰጠ ባለ ህዝብ ልብ ውስጥ ሽንቁር መፍጠር እንዳይሆን እሰጋለሁ:: የአዲስ አበባ ጉዳይ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ሁኔታ አንፃር ንዑስ ጉዳይ ቢሆንም ወሳኝና ትኩረት የሚሰጠው ነው:: የሀገሪቱን ፖለቲካና ኢኮኖሚ በበላይነት በሚዘወርባት አዲስ አበባ ላይ የሚደረግ ሹም ሽር አጠቃላይ የሀገሪቱን እድል እጣፈንታ ከመወሰን ጋር የሚቆራኝ ነው:: ለዚህም ነው ስለአዲስ አበባ ጉዳይ ሁሉም በእኩል በስስት የሚከታተለው:: የእስከዛሬው ሆኗል:: በለውጥ ሰሞን ተመሳሳይ መንገድ መከተል ግን አደገኛ እርምጃ ነው::
የዶ/ር አብይ አካሄድ የብዙዎችን ቀልብ የገዛው ዘር ቆጥረው: አጥንትና ደም መዝነው ሹመትና ስልጣን የሚሰጥበትን አሳፋሪና አስከፊ ምዕራፍ ለመዝጋት ቁርጠኛ ናቸው በሚል ነው:: ይህንንም እሳቸው በአንድ ንግግራቸው ላይ ፍንጭ ሰጥተዋል:: ብቃትና እውቀት ከእንግዲህ ዋጋ ይሰጣቸዋል የሚለው ንግግራቸው እኔንም ስለዶ/ር አብይ የነበረኝን አመልካከት ወደአወንታዊ ካደረጉ ገፊ ምክንያቶች አንዱ ነበር:: ለውጥ እየመጣ ነው የሚል ተስፋም ያሳደርነው እንዲህ ዓይነት አመራር ቤተመንግስት በመግባቱ ነው:: በእርግጥም የሚታዩት አንዳንድ ነገሮች ስሜት ይገዛሉ:: የለውጥ ሂደት መጀመሩን ያመለክታሉ::
የአዲስ አበባ ከንቲባ በርስትነት በኦሮሞ ተወላጆች መያዙ የህወሀት የዘር ካርድ ጨዋታ አንዱ ገፅታ ነበር:: ለውጥ እየመጣ ነው ሲባል እንደነዚህ ዓይነት ካርዶች ተቀደው: ተቃጥለው ይጣላሉ ከሚል ተስፋ ጋር ነው:: ከንቲባ ሹመት ላይ በዶ/ር አብይ የተወሰደው እርምጃ ከዘር ቆጠራ የፀዳ ለመሆኑ ምን ማረጋገጫ መስጠት ይቻላል? አካሄድ ተጥሶ: አሰራር ተዛንፎ የአዲስ አበባ ም/ቤት ያልሆነ ሰው እስከመሾም የሚያደርስ እውቀትና ልምድ እኚህ ሰው ዘንድ ተገኝቶ ነውን?
ስለግለሰብ የጀርባ ታሪክ የምሰማው እንደእነ ለማና አብይ ከዘር አቀንቃኝነት ነፃ የሆኑ ሰው ስለመሆናቸው አይደለም:: በግል የፌስቡክና አንዳንድ መድረኮች የሚፅፏቸውንና የሚናገሩትን ከመረመርን አዲሱ ከንቲባ አዲስ አበባን የሚመለከቱበት መንፅር አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ከሚያቀነቅኑት የተለየ አይደለም:: የአዲስ አበባን ችግር ስር ከያዘውና መተንፈሻ ካሳጣት የመዋቅርና የመልካም አስተዳደር እጦት ይልቅ የማንነት ጥያቄ አድርገው የሚያምኑ እንደሆነ ይነገራል:: የአዲስ አበባ ማንነት ምን ማለት ነው? እንዲህ ዓይነት አመለካከት ደሙ ውስጥ ለሚመላለስ ሰው አዲስ አበባ መሰጠቷ ከየት ያደርስ ይሆን?
ሹመቶች ከህወሀት ወደኦህዴድ እየተዛወሩ ነው የሚለው ክርክር ሰሞኑን ጦፏል:: ዶ/ር አብይንና አቶ ለማን ለተመለከተ ሰው ይህ ስጋት ላያድርበት ይችል ይሆናል:: ግን ስጋቱ የተፈጠረበት ሰው ቢኖር ሊኮነን አይገባውም:: ነገሮች ይመስላሉና:: የአዲስ አበባ ከንቲባ ሹመት ደግሞ ይህን ስጋት የሚያጠናክር ነው:: ለአፍሪካ መዲና: ዓለምዓቀፍ ቅርፅ ለያዘች ከተማ: ለኢትዮጵያውያን መናገሻ ለሆነችው አዲስ አበባ ከንቲባ ጠፍቶላት ህግና አሰራር ተፋልሶ ከብሄርተኝነት አቀንቃኝነት ውጭ የተለየ የስራ ልምድ ለሌለው ሰው መሰጠቱ ጅምሩን የለውጥ ሂደት ለጥርጣሬ ያጋልጣል::
ለምን ዘሩን ታያላችሁ? እውቀትና ችሎታው እንጂ የሚል በቀድሞ ህወሀቶች የሚሰነዘር የሁል ጊዜ ጥያቄ አይነት አሁንም በኦሮሞ ብሄርተኛ አቀንቃኞች ዘንድ እየተነሳ ነው:: ይህ ነገርም ለውጥ የለም: ለውጡ የድርጅት ነው ለሚሉ ሰዎች ጥሩ መማቺያ ዱላ ሆኗል:: በፊት ህወሀት የትኛውንም ውሳኔ ይወስን: ሰው ይግደልም ይሰርም እንደመንጋ ግር ብለው ጥብቅና የሚቆሙትና ወንጀሉን ምክንያታዊ አድርገው ለመሞገት የሚፈጥኑት የትግራይ ተወላጆች ነበሩ:: እንዲህ ዓይነት አዝማሚያ አሁን እያቆጠቆጠ ይመስላል:: ከንቲባ የተደረጉትን ሰው ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ የኦሮሞ ተወላጆች በአንድ መስመር ተሰልፈው ተመሳሳይ ሙግትና እንካሰላንቲያ ውስጥ ተጠምደው ሳያቸው አካሄዱ ምቾት የሚነሳ እየሆነብኝ ነው:: ቤተመንግስት የገቡት መሪ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንጂ የአንድ ብሄር ተወካይ አይደሉምና ነው::
ዶ/ር አብይ አስተዳደር ላይ ፍርድ ለመስጠት ጊዜው በእርግጥ ገና ነው:: የሽግግር ወቅት ከመሆኑ አንፃር ሰከን ያለ አካሄድ ግድ ይላል:: ካለው ፖለቲካዊ ውጥረት ጋርም ከተመዘነ ነገሮችን በትዕግስት መከታተሉ የሚበጅ ሊሆን ይችላል:: በህወሀት የተጨማለቀውን ቤት ለማፅዳት በቂ ትንፋሽና ጊዜ ያስፈልግም ይሆናል:: ነገር ግን ህዝቡ ለውጥ መጣ ብሎ በተስፋ የተሞላባቸው መሰረታዊ ጉዳዮችን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ እርምጃዎች ላይ የአብይ አስተዳደር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት:: ለውጡ ላይ ውሃ የሚቸልሱ: የሰውን ልብ የሚሰብሩ እርምጃዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው:: የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሀት ተወግዶ ኦህዴድ እንዲነግስበት አልታገለም:: ከእንግዲህ ደምና አጥንት እየተቆጠረ ስልጣን የሚሰጥ ከሆነ አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ? ለሚል ወቀሳ የሚያጋልጥ ነው::
በአጭሩ በአንዳንድ አክራሪዎች የሚስተጋባው “ጊዜው የእኛ ነው : ተራችንን እንጠቀም” የሚለው ትርክት በአብይ መንግስት ውስጥ ቦታ አለው ብዬ ባላምን እመርጣለሁ::
No comments