Latest

ኮማንደር ተክላይ መብርሃቱ ከሀገር ሊወጣ ሲል ተያዘ ሲባል በሰማሁ ጊዜ (ጌታቸው ሺፈራው)


የዚህን ሰው ስም  የሰማሁት የዞን ዘጠኝ አባላት ታስረው አራዳ የመጀመርያ ፍርድ ቤት በሚቀርቡነት ወቅት ነበር። አባላትን የፍርድ ቤት ውሎ ለመከታተል የሄደውን ታዳሚ ሁሉ ያሸማቅቅና "ፎቶ አንስተሃል" እያለ ወደ ማዕከላዊ አንቆ ይወስድ የነበር ነው ኮማንደር ተክላይ።
 

በዚህ ተግባሩም ማሕበራዊ ሚዲያው ላይ  ጭራቅ ተደርጎ ይፃፍበት ነበር። ማዕከላዊን ሲታሰብ ኮማንደር ተክላይ አብሮ የሚወሳበት አጋጣሚም ተፈጥሮ ነበር። 

በ2008 ዓም  ማዕከላዊ በታሰርኩበት ወቅት ያለፈ ያገደመውን ተክላይ ስለመሆኑ እገምት ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን፣አጠርና ቀላ ያለ ወፍራም ሰው  ሌሎች ፖሊሶችን አስከትሎ ወደ  እስር ቤት ክፍላችን መጣ። "ምን ችግር አለ?" ብሎ ጠየቀን። በአካል አይቶት የማያውቀውን የክፍሉን እስረኛ ችግሩን ሲነግረው "አንተ እንትና ነህ?" ብሎ ይጠይቃል፣ እስከ አባቱ ስሙን ይጠራል።
 

የመቶ  እና ሁለት መቶ እስረኛን  ስም ለይቶ ያውቃል ማለት ነው። ጠይቁኝ ባለው መሰረት፣ ጠበቃዬን እንዳላገኝ መከልከሌን ፣ መርማሪዎቹ  እኛ የምንፈልገውን ካልነገርከን ጠበቃህ ጋር አናገናኝህም እንዳሉኝ አቤቱታዬን አቀረብኩ። ኦብሱማን ኡማ የተባለ የአምቦ ልጅ ሕክምና እንደተከለከለ እንቅጩን ነገረው። ከዱላ በማይተናነስ ግልምጫው ሙልጭ አድርጎ ሰድቦን ተመለሰ።

ከወጣ በኋላ ተክላይ መሆኑን አረጋገጥን።  እድለኞች ነን። ከአራዳ ፍርድ ቤት ታዳሚዎችን አንጠልጥሎ ወደ ማዕከላዊ የሚያመጣ ሰው ማዕከላዊ ጨለማ ቤት ያገኘውን ሰው በዚህ መልኩ ማለፉ ተክላይን መጥፎ ሰው አያስብለውም። ተክልዬ  ቀርበውት ነው ለማለት ቢከብድም  እንደሚታወቅ ስሙ ተመስገን የሚያስብል ነበር። ተክላይ ያየሁበት ሌላኛው አጋጣሚ ሸራተን እስር ቤት ነበር።
 

ከጨለማ ቤቶቹ አንፃር ፀኃይና አየር በከፊል ስለሚገኝበት በዘመናዊ ሆቴል ስም የተሰየመው አስቀያሚ የእስር ቤት ክፍል በየሳምንቱ ሰኞ እስረኞችን ሰብስቦ ያወያያል። አብዛኛው እስረኛ ከማዕከላዊ መፈታት ቀላል እንዳልሆነ ስለሚያውቅ "ክሰሱን" ብሎ ይማፀነዋል። ወይ ግደሉን፣ መረሸን ነው የቀራችሁ ብሎ በግልፅ የሚናገርም አይጠፋም። ለምሳሌ ኢብራሂም ሳዳም ለተክላይ መሰል ጥያቄ አቅርቦለታል።"ወይ ግደሉ፣ ብትረሽኑን ይሻላልኮ" ብሎታል ደፋሩ ኢብራሂም።

ኢብራሂም የአወዳይ ልጅ ነው።  በደሉን ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ጨዋታው ግልፅ ነው። ከታሰረ በኋላ ወዲያውኑ ወደማዕከላዊ አላመጡትም። አይኑን ሸፍነው ወዳልታወቀ ቦታ ወሰዱት። ከግምት ያለፈ የት ታስሮ እንደነበር አያውቀውም። በዚህ እስር ቤት ደሕንነቶች ልብሱን አስወልቀው ገርፈውታል። ብልቱን ይዘው ጎትተውታል። በዚህም ምክንያት ተኮላሽቷል።

ኮማንደር ተክላይ ሰኞ ሰኞ እስረኞችን ሰብስቦ "ምን ችግር አለ?" ብሎ ይጠይቃል። የፀረ ሽብር አዋጁ ከሚፈቅደው ውጭ ለአራት ወር በላይ ማዕከላዊ ታስረው "ኧረ ክሰሱን" የሚሉትን ጨምሮ የተወሰነ እስረኛ ሲሰበሰብ ቀሪው መፍትሔ እንደማያገኝ ስለሚያውቅ "ስብሰባ፣ ስብሰባ" እየተባለም ከቤት አይወጣም። ፀኃይ ሲሞቅ እግረ መንገዱን የሚሰማ ይኖራል። ኢብራሂምን ጨምሮ ብሶታቸውን ለመናገር የፈለጉ በስብሰባው ተገኝተዋል።
 

ኢብራሂም "ደርግ ምን አደረገ? እየው ብልቴን አኮላሽታችኋል። ለምን አትገድሉኝም? ለምን አትረሽኑኝም። ደርግ ምን አደረገ? ደርግስ እናንተ ናችሁ!" ብሎ የሚሰማውን ተናገረ። "ምን ችግር አለ" ብሎ እስረኛ የሰበሰበው ኮማንደር ተክላይ ይህ ልጅ ችግሩ ምንድን ይሆን ብሎ አላጣራም።  ንግግሩን እንኳ አላስጨረሰውም። ስብሰባው አልቆ፣ እነ ተክላይ ከሄዱ በኋላ የኢብራሂም ስም በ"ሚዲያ"  ተጠራ። እቃህን ይዘህ ውጣ ተባለ። ሊፈታ አይደለም። ተክላይን እንደዛ ተናግሮ? ወደጨለማ ቤት ነው።

(የሰቆቃ ድምፆች መፅሐፌ ላይ የቀነጨብኩት ነው፣ ይህ አንደኛው ተክላይ ነው። ብዙ ተክላዮች አሉ። መፅሃፉም ላይ)


No comments