Latest

የመደመር ፖለቲካ – ገለታው ዘለቀ


የተከበሩ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በቅርቡ ባመጡት የመደመር ስሌት መሰረት ብዙ ኢትዮጵያዊ ይህን መርህ ወዶት መፈክር አድርጎት ይታያል። እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረግ የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት ራሴን ደምሪያለሁ ብያለሁ። ታዲያ ዛሬ ይህን ጽሁፍ ሳዘጋጅ ስለዚህ ስለመደመር ጉዳይ ትንሽ ውይይት ለማንሳት አስቤ ነበር።


በርግጥ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ “ተደመሩ” ሲሉ ጽንሰ ሃሳቡ ምን ምን ይዘት እንዳለው በጥልቀት ሊያብራሩ የሚችሉት እሳቸው ራሳቸው ናቸው። እሳቸው በገባቸው ልክ እኔ ሊገባኝ ኣይችልም። ይሁን እንጂ እኔ ራሴን ስደምር የዚህ የመደመር ስሌት በጥልቀት እንዲገባኝና በዚያ መረዳት ላይ ሆኘ ድጋፌን እንድሰጥ ነው የምፈልገውና “መደመር” ሲባል የገባኝን ጽንሰ ሃሳብ ዛሬ ለአንዳንድ ወገኖቼ ባካፍል ጥሩ ይሆናል ብየ አሰብኩ። ይህ የጠቅላይ ሚንስትሩ የመደመር መፈክር በርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ መሰረታዊ የትርክት ለውጦችን (change of narrative) አንግቧል ወይ? የሚለውን መጠየቅ ተገቢ ነውና በዚህ ላይ እንወያይ።

በሃገራችን ሁኔታ የመደመር ፖለቲካ በሚከተሉት መረዳቶች ላይ ቢመሰረት ለወደፊት የለውጥ ርምጃችን ሃይል ይሰጠናል ብየ አምናለሁ። ምን ጊዜም ቢሆን ከግልብ መረዳትና ህዝባዊ ንቅናቄ ታቅበን በተሻለ የመረዳት ከፍታ ላይ ሆነን የምናደርገው ትግል ነው ለውጥ የሚያመጣው። ባለፍንባቸው የህይወት ልምዶቻችን ብዙ ግልጽነት የጎደላቸው መፈክሮችን ስንከተል ኖረን ቆይተን ዛሬ ላይ ሆነን ስናያቸ ጉምን እንደመጨበጥ የሆኑ ነበሩና ማስተዋል ያስፈልጋል ከሚል ነው። ወደ አነሳሁት ሃሳብ ልመለስና “የመደመር” ጽነሰ ሃሳብ ይዘቶች የሚከተሉት ሲሆኑ በነዚህ ማማዎች ላይ ሆነን መደመርን ብንደግፍ ግሩም ይሆናል።

የመደመር (+) ማማዎች


  • ብዝሃነት
መደመር ስንል ማቀፍን ወይም (inclusion) ያሳያል። መደመር ነጠላነትን (homogeneity) የሚያራምድ ወይም የሚያበረታታ ሳይሆን ተገጣጥሞ ሰፋ ያለ መዋቅር መፍጠርን መያያዝን የሚያሳይ ጽንሰ ሃሳብ ነው። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ገዢ ኣሳብ የነበረው ነጠላነትን( homogeneity) የሚያበረታታ ብሄሮች “የራሴ” የሚሉትን ግዛት እያጠሩ የሚኖሩበትን ሁኔታ የሚያበረታታ ነበር። 

መደመር ግን ይህንን የሚያፈርስ ነውና በርግጥ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ይህን ኣሳብ ሲያፈልቁ ሃገራችን ወደ ሌላ የትብብር የመገጣጠም የህብረት ትርክት(narration) ውስጥ እየገባች እንደሆነ ያሳያልና ይህ የመደመር ኣሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካውን ኣይዲዮሎጂና ትርክት የሚለውጥ እንቅስቃሴ ሆኖ እናየዋለን። 

የኢትዮጵያ ህዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄም ይህ ነበር። ቀድሞ የነበረው መደመርን የሚያኮስሰው የፖለቲካ ኣስተሳሰብ ብዙውን ሰው ኣስኮርፎ የቆየ ሲሆን ዛሬ የመደመር ፖለቲካ ሲመጣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በግልም በቡድንም ተደምረናል! ተደምረናል! እያሉ ኣዲሱን ትርክት ሲደሰቱት በአንጻሩ ያለፈውን ትርክት አደባባይ ላይ ሲሰብሩት ይታያል። በመሆኑም መደመር ስንል እንግዲህ እኛ የተደመርን ሰዎች ይህንን መረዳት ብናየው መልካም ነው።
 

የመደመር ፖለቲካ በኢትዮጵያ ውስጥ የትርክት ለውጥ ያሳያል ስንል በተለይም በክልሎች ህገ መንግስታት ያለውን ኣንዳንድ ኣንቀጽ የሚጻረር ኣስተሳሰብ ሆኖ ስለምናይ ነው። ይህ ክልል የነእገሌ ነው የሚለውን ትርክት ሽሮ ኢትዮጵያውያን በዋናው ቤታቸውም ይሁን በስቴቶቻቸው ተደምረው እንዲኖሩ የሚያደርግ በመሆኑ የብሄር ፌደራል ስርዓቱን ራሱን የሚጋፋ ትርክት ይዞ እናያለን። 

የሃገራችን ሶሺዮ ፖለቲካ ጉዞ ወደ መለየት (separation) የመጣ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከፍ ብሎ የመጣው የመደመር ጥሪ ይህንን የመለየት (separation) ፖለቲካ የሚጋፋ ሆኖ እናያለን። ይሄ የሚደገፍ ትርክት ነውና ኢትዮጵያውያን ሁሉ የመደመርን ጽንሰ ሃሳብ ከፍ አድርገው ሊይዙት ይገባል።

  • ክህሎትና እውቀት (skill & knowledge)
መደመር ማለት ማነባበር ማለት ኣይደለም። መደመር ማለት የሚደመረው ነገር ተደምሮ የሚሰጠውን ዋጋ (value) ወይም እሴት በትክክል ማወቅና ማስላት መቻል ማለት ነው። የሚደመሩት ተለዋዋጮች ተደምረው ያላቸውን የጋራ እሴት መረዳት ካልቻልን የመደመር ጽንሰሃሳ ገባን ማለት ኣይቻልም። ስለሆነም እንደመር ስንል ተደምረን የሚኖረን የጋራ እሴት እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ጉዳይ፣ በፖለቲካው መስክ የሚሰጠንን ትርፍ መተመን መቻል ማለት ነው። 

የዶክተር አብይ የመደመር ኣሳብ ጥሩ ደጋፊ መሆናችን የሚለካው ተደምረን የምናገኘውን ዋጋ ቀድመን ባሰላነው መጠን ነው። ስለዚህ ከኛ ከደጋፊዎች ይህንን የመደመር ዋጋ ኣስልቶ የማየት ችሎታ ይጠይቀናል። ዋጋው በታየን መጠን ለትግሉ የሚከፈለውን ዋጋ ለመክፈል እንችላለን። ከሁሉ በላይ ይህ ጽንሰ ሃሳብ በአንድ ጊዜ ቦግ ብሎ የሚጠፋ የስሜት ነገር ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የአብሮነት መርህ በመሆኑ የመደመር ወይም የብዝሃነት ዋጋው በሚገባ ሊገባን ይገባል። ተደምሮ የመኖር ክህሎትንም ልናዳብር ይገባል።
  • ጥምረት (Coalition)
ሌላው የመደመር ጽንሰሃሳብ የሚያመላክተው ነገር በተለይ ለተደራጁ የፖለቲካ ሃይላት የቅንጅት (Coalition) ወይም የመዋሃድ ጥሪ አለው። ሃገራችን ወደ መቶ የሚጠጉ ፓርቲዎችን ይዛ ትወዛወዛለች። የአንድነት ሃይሎች ስለህብረት እያወሩ ነገር ግን ኣይደመሩም። ኣንድ ኣይነት ኣይዲዮሎጂና ፖሊሲ ይዘው የተለያየ ፓርቲ ሆነው ይኖራሉ። አሁን ጊዜው የመደመር የቅንጅት ጊዜ ነው።
 

የመደመር ጽንሰ ሃሳብ ለነዚህ ፓርቲዎች ትልቅ ጥሪ ኣለው። መሰባሰብ መደመር ይጠበቅባቸዋል። የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ዋና ዓላማ ለህዝቡ ኣማራጭ ፖሊሲዎችን መፍጠር ነው። ከመቶ በላይ ፓርቲ ቢኖረን የዚህን ፓርቲ ሁሉ ኣሳብ ለማወቅና ለመምረጥ ራሱን የቻለ የአንድ ኣመት ኮርስ ሊወስድብን ይችላል። 

የፓርቲውን ስም ሸምድደን ለመያዝም አንችልም። ፓርቲዎች ጠጋ ጠጋ ብለው ቅንጅት ፈጥረው ሁለትና ሶስት ሆነው ለምርጫ ቢመጡ ልዩነቱን እየተመንን የተሻለውን ለመምረጥ እንችላለን። ስለዚህ ይህ የመደመር ጥሪ ለነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሰራልና መደመር አለባቸው። በዶክተር አብይ የመደመር ስሌትም ይሄ አሳብ የሚበረታታ ይመስለኛል። የተሻለ መድብለ ፓርቲ ስርዓት እንድንፈጥር ፓርቲዎች ብትደመሩ ከሁሉ በላይ ደግሞ መንግስትም ቢደግፋቸው ተገቢ ነው።
  • ቅርጽ 
ሌላው የዚህ የመደመር ጽንሰ ሃሳብ ትምህርት ሊሰጠን የሚችለው ነገር ከራሱ ከምልክቱ የምንቀዳው ትምህርት ነው። የመደመር ምልክት (+) እንደሚያሳየው በአንድ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ግንኙነት ያሳያል። ወደ ላይ ያለው መስመር በመንግስትና በህዝብ መካከል የጠበቀ ግንኙነትን የሚያሳይ ሲሆን ወደ ጎን ደግሞ ግለሰብ ከግለሰብ (interpersonal relationship) ና ቡድን ከቡድን እጅ ለእጅ መያያዝን ቃልኪዳን መግባትን ያሳያል።
 

ይህ መስቀለኛ ምልክት የኢትዮጵያውያን አብሮ የመኖር የኪዳን ምልክት ሊሆን ይችላልና ይህንን ምልክት ከመንግስታችን ጋር ባለመተማመን የተቆረጠውን መስመር የምንቀጥልበት፣ መንግስታችን በኛ ምርጫ የሚሾምበትና የሚሻርበት፣ ወደ ጎን እኛ ኢትዮጵያውያን ህብረት የምንፈጥርበት፣ ብሄሮች፣ ግለሰቦች በሙሉ ተደምረን የአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ህዝብ መሆናችንን የምናሳይበት ምልክት ሊሆነን ይችላል። መተማመን ወደላይና ወደ ጎን የሚፈስበት የአብሮነታችን ምልክት ነውና::
  • በግድ የሆነ ምስለት (Assimilation) ኣያሳይም
በሂሳብ ጊዜ መደመር የሚከተለውን ጸባይ ያሳያል። ለምሳሌ:-
6 ብርቱካን + 2 ብርቱካን = _________ተብሎ ቢጠየቅ አንድ የአንደኛ ክፍል ተማሪ 8 ብርቱካኖች ይለናል። ልክ ነው። ነገር ግን ፖለቲካዊ መደመርን በዚህ ቀላል ሎጂክ ልናዘው ብንሞክር አይሄድልንም። ለምሳሌ:-
1 ሙዝ + 1 ፓፓያ + 1 ብርቱካን  + 1 ሎሚ =_____ ተብለን ብንጠየቅ ውጤቱን ለመናገር ትንሽ ማሰብ ሊጠይቅ ነው። ምን አልባትም ፣አንድ ሙዝ፣ አንድ ፓፓያ፣ አንድ ብርቱካን፣ አንድ ሎሚ ብለን ልንመልስ እንችል ይሆናል። 

ነገር ግን እነዚህን ፍራፍሬዎች በአንድ ጠቅላላ ስያሜ ውስጥ ከከተትናቸውና ስንት ፍረፍሬ አለ ከተባለ የተለያዩ ፍራፍሬዎች አሉን ልንል እንችላለን። ኦሮሞዎች፣ አማራዎች፣ ትግሬዎች፣ ጉራጌዎች፣ ወላይታዎች፣ አፋሮች ወዘተ ተደመሩ ሲባል አንድ ተደፍጥጦ የተፈጠረ ባህላዊ ቡድን ይሁኑ ማለት ኣይደለም።
 

መደመር ማለት ልዩነቶቻችን እንዳሉ ሆነው ግን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊ እንሁን ማለት ነው። ስለዚህ መደመር ስንል በግድ የሆነ ምስለትን (assimilation) እናምጣ ሳይሆን ብዙህ ሆነን ግን በአንድ የጋራ ማንነት ስር ማለትም ኢትዮጵያዊነት ስር እንደር ማለት ነው። በዚህ የመረዳት ማማ ላይ ሆነን መደመርን ካየነው በርግጥ የሚደገፍ ኣሳብ ነው።
  • የዜሮ ድምር
በመደመር ጊዜ በውጤቱ ላይ ምንም ለውጥ ወይም እድገት የማያሳየው ዜሮን ጨምረን የደመርን እንደሆነ ነው። ዜሮ ባዶ በመሆኑ በድምራቸን ላይ ተጽእኖ የለውም። የዶክተር አብይ የእንደመር ጥያቄ ለእኔ የአስተዋጾ ጥያቄ ነው። ተጨባጭ የሆነ ተፈላጊ ለውጥ እናመጣ ዘንድ የለውጥ ሃይላት ሁሉ የምንችለውን መወርመር አለብን። 

በሌሎች ዋጋ ተጨባጭ ለውጥን መናፈቅ ተደምሪያለሁ ከሚል ዜጋም ሆነ ቡድን አይጠበቅም። እኔ የዶክተር አብይ የእንደመር ስሌት ደጋፊ ነኝ ብያለሁ ነገር ግን ሁኔታውን እያየሁ የምደግፍ (conditional) ደጋፊ ነኝ። የመደመርን ኣሳብ እደግፋለሁ ስል የምደግፈው ግለሰብን ሳይሆን ኣሳቡን ነው። በለውጡ ሂደት ዶክተር ኣብይ ቢደክሙ ወይም ለውጡን ከዳር ባያደርሱ ተደምሪያለሁ ብየ ሲያጠፉ ሁሉ ስደግፋቸው ኣልኖርም። ይህ የመደመር ስሌት የመርህ ጉዳይ ነው። ሃገራችንን ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓት የሚወስዳትን አመራር ሁሉ እየደገፍን የምንሄድበት መርህ እንጂ የግለሰብ ደጋፊ አይደለሁም። 

ስለሆነም ለመደመር ጽንሰሃሳብ ሁኔታ የማያግደው (Unconditional) ደጋፊ ስሆን ለዶክተር አብይ ግን ሁኔታ እያየሁ (Conditional) ደጋፊ መሆኔን ከአክብሮቴ ጋር እገልጽላቸዋለሁ። በርግጥ ግለሰቦች ባላቸው ኣስተዋጾ ሊበረታቱ ሊደገፉ ይገባል። ነገር ግን የሙጥኝ ብለን የምንኖረው መርህን መሆን ኣለበት። ስለዚህ የመደመርን መርህ የምንከተለው ዶክተር ኣብይ ስልጣን ላይ እስካሉ ብቻ ሳይሆን ሄደውም ይህን መርህ ስንደግፍ ልንኖር ይገባል። ለውጥ የምናመጣው ሁላችን አስተዋጾ ስናደርግ እሚደገፈውን ስንደግፍ የማይሆነው ላይ ደግሞ እምቢኝ ብለን ስንታገል ነው።

  • ምርኮ ማብዛት
“Politics is about addition, not subtraction” ፖለቲካ የመደመር እንጂ የመቀነስ ጉዳይ ኣይደለም። ይህንን አባባል መጀመሪያ ማን እንደተናገርው ኣይታወቅም። ነገር ግን እውነት ነው ፖለቲካ ስለመደመር ነው። ይህ ሲባል ጥላቻን፣ ወንጀልን ወዘተ መቀነስ ኣይገባም ወይ? የሚል ቀላል ጥያቄ እንደማይነሳ እያሰብን ነው። 

ፖለቲካ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ጉዳይ፣ በፖለቲካ ጉዳይ መደመርን ማደግን ዓላማው ኣድርጎ የሚሄድ የአስተዳደር ጥበብ ነው። በሃሳብ ልቀት በፖሊሲ ልቀት ብዙዎችን እየማረከ የሚሄድ ጥበብ ነው። በሌላ በኩል እንደመር የሚለው ቃል የፍቅር ጥሪ ነው። የብሄራዊ እርቅና መግባባት ጥሪ አለው። 

የማግለል የመቀነስ ባህርይ የለውም። ስለዚህ በመደመር ትግላችን ወቅት ቡድኖችን የማግለል ስራ መስራት የለብንም። የምናገለውና የምናቅፈው ብለን የመለየት ስራ መስራት የለብንም። በፍቅር የመማረክ ስራ መስራትን ይጠይቃል። ባለቅኔው ፍቅር ያሸንፋል! እንዳለው መደመር የፍቅርን የመቻቻልን ጥግ የምናሳይበት ምልክት ነው ። 

በመሆኑም የዶክተር አብይን የመደመር ጥሪ የምንደግፈው ይቅርባይነትን፣ መማረክን፣ በፍቅር ማሸነፍን ታጥቀን መሆን ይጠበቅብናል። የጥላቻ ፖለቲካ ከምድራችን ነቅሎ ይሄድ ዘንድ የመደመር ፖለቲካ በጣም ፍቱን መድሃኒት ነው።

ስለዚህ ስለመደመር ፖለቲካ ብዙዎች ብዙ ሲሉ እየሰማን ነው። አንዳንዶች መደመር ሲባል የምንቀንሰውስ ኣለ ወይ? እነማን ይቀነሱ እነማን ይደመሩ? ይላሉ። ማንንም አንቀንስም። ለመደመር ነው የምንጥረው። ማንንም ለይተን ማንንም ኣንቀንስም። ነገር ግን አንድነትን የማይሻ፣ የመለየት ፖለቲካን የሚሻ ሰው እሱ በራሱ ኣይደመርም። ከዛ ውጭ ልበ ሰፊ ሆነን ሃገራችንን ወደ ተሻለ ስርዓት ለመውሰድ የሚደመሩ የሚቀነሱ ብለን ኣንመድብም። 

በቻልነው ኣቅም ለመማረክ እየጣርን ከሄድን ነው የመደመር ፖለቲካ በጎ ፍሬ አፍርቶ የምናየው። በመሆኑም በፌስ ቡክ ይሁን በሌላ ሶሻል ሚዲያ ግለሰቦችንም ይሁን ቡድኖችን ይደመሩ ዘንድ ምርኮን መሰብሰብ ትልቅ ኣስተዋጾ ይሆናል። በመደመሩ ንቅናቄ ጊዜ አስመሳይ ኣድርባይ ይኖራል። ነገር ግን በሂደት ህዝባዊ ንቅናቄው አሸንፎ ስለሚወጣ ተጽእኖው ያን ያህል ኣስፈሪ ኣይሆንም።

  • ማባዛት፣ ማካፈልና መቀነስ
መደመርን ግባችን አድርገን ወደዚህ ግብ ለመድረስ መቀነስን፣ ማባዛትን ማካፈልን ልንጠቀምባቸው እንደምንችል ማሰብ ለመደመር ስራችን ትልቅ ሃይል ይሆነናል። አንዳንድ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ የማይረዱ ጎታች የሆኑ አስተሳሶብችን መቀነስ እንደ መደመር ይቆጠራል። ጥላቻን መቀነስ ፍቅርን መደመር ነውና። አለመተማመንን መቀነስ ማህበራዊ ሃብት ያድግ ዘንድ መደመር ነውና። ያለንን እውቀት ማካፈል፣ አስተዋጾዎቻችንን ማብዛት መደመር ነውና። 

በመሆኑም ለዶክተር አብይ የመደመር ጥሪ መቀነስን፣ ማካፈልን፣ ማባዛትን ሁሉ መደመር አድርገን ልንጠቀምባቸው እንደምንችል ማስላት በተለይ ለተደረጁ ሃይላት ያስፈልጋል። ኣደገኛ ጉዳዮችን ሁሉ ወደ በጎ ለውጥ የመቀየር ችሎታ መደመር ነው። ለውጣችንን የሚጎዱ ነገሮችን መቀነስ፣ መተማመንን የሚጎዱ ጉዳዮችን መቀነስ ማለት ፖለቲካ ማለት መደመር ነው የሚለውን ኣይጻረርም። ይልቁን መደመራችንን የሚያዳብር ነውና።

  • የተቋማት መደመር
የዶክተር አብይ የተደመሩ ጥያቄ ለብሄሮችና ለዜጎች ብቻ ሳይሆን በተለይ ለተቋማትም ይመስለኛል። ፍርድ ቤት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ተደምሪያለሁ ማለት አለበት። ፖሊስ፣ ደህንነት፣ ወታደሩ፣ ባለሙያው ፣ ተማሪው አስተማሪው ተደምረናል የሚል ኪዳን ያስፈልጋቸዋል። ይህ የመደመር ንቅናቄ የፖለቲካ ርእዮት ሳይሆን ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓት ለማሻገር የሚደረግ ንቅናቄ በመሆኑ ተቋማት በተለይ ድጋፋቸውን ሊያሰሙ ይገባል። ይህ ነገር ለህዝቡ ትልቅ ተስፋና አቅም ይሆናል። ለለውጥ ሃይላትም ትልቅ የሞራል ድጋፍን የሚሰጥ ይሆናል።

በመጨራሻም ዶክተር አብይንም ሆነ አብረዋቸው ለለውጥ የሚታግሉ እንደነ ኦቦ ለማ መገርሳ ያሉ የለውጥ ታጋዮችን ሁሉ ለጀመሩት ለዚህ የመደመር ፖለቲካ እያመሰገንኩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ተግባራዊ የሆኑ ለውጦች እንዲመጡ ሃገራችን ወደ ብሄራዊ መግባባት እንድታልፍ እኛ ዜጎች ለመደመርና ለመደመር ቆርጠን መነሳት አለብን።
 

የለውጡ ሃይላትም ሃገሪቱን ወደ ተሻለ መድብለ ፓርቲ ስርዓትና ምርጫ በአንድ ቃልም ወደ ሪፐብሊክ እንዲመሩ እንደዜጋ እጠይቃለሁ። ሃገራችን ቀድሞ የነበራት ዝናና ገናናነት ተመልሶ በእኛ ትውልድ የምናየው መደመርን መርህ አድርገን ስንታገል ነው።

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com

No comments