Latest

ባንዲራና አርማ ምርጫ አለው፣ የኦሮማራ ትብብር ግን አማራጭ የሌለው የህልውና ጉዳይ ነው!! ስዩም ተሾመ


"አንድነት" ማለት "አንድ ዓይነት" መሆን አይደለም! የኦሮሞና አማራ ህዝቦች አንድነት የተመሠረተው "አንድ ዓይነት" ቀለምና አርማ ባንድራ ስለሚያውለበልቡ ወይም አንድ ዓይነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ስለሚያራምዱ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ የሁለቱ ህዝቦች አንድነት የተመሠረተው በወደፊት አብሮነት (Common Future) ላይ ነው፡፡ የኦሮሞና አማራ ልሂቃን የተለያየ አይነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ቢኖራቸውም የጋራ ወይም የተሳሰረ ህልውና አላቸው፡፡ ሁለቱ ህዝቦች በመካከላቸው ያለው ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በጋራ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ እርስ-በእርስ መተባበርና መደጋገፍ አለባቸው፡፡

ኦሮሞና አማራ እርስ-በእርስ ከመተባበር ይልቅ መለያየት፣ ከመደጋገፍ ይልቅ መጠላለፍ ከጀመሩ የፖለቲካ ስልጣኑን አናሳ ድምፅ ላለው የፖለቲካ ቡድን ወይም ለውጪ ሃይል አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ ይህ በኢትዮጲያ ታሪክ በተደጋጋሚ የተረጋገጠ እውነታ ነው፡፡ ለምሳሌ በ1760ዎቹ የጎንደር ንጉስ ዳግማዊ እያሱ ሲሞት ዙፋን የወረሰው በእድሜው ገና ልጅ የነበረው እዮኣስ ነበር፡፡

የጎንደር፥ ቋራ ተወላጅ በሆኑት የእዮኣስ አያት እትጌ ምንትዋብ እና የዬጁ  ኦሮሞ በሆነችው የእዮኣስ እናት እትጌ ውቢት መካከል የንጉሱ ሞግዚት ለመሆን የሃይል ሽኩቻ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ እትጌ ምንትዋብ የቋራ ዘመዶቿን ስትጠራ፣ እትጌ ውቢትም የዬጁ ዘመዶቿን ወደ ጎንደር ጠራች፡፡ የጎንደር ከተማ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በመግባቷ ምክንያት እ.አ.አ በ1764 የትግራዩ ገዢ የነበረው ራስ ሚካኤል ስሁል ከ20,000 የሚበልጥ ጦር አስከትሎ ጎንደር ገባ፡፡ ወደ ንጉስ እዮኣስ የሚደረገውን የስልጣን ሽግግር በገላጋይነት ተጠርቶ የመጣው ራሱ ንጉሱን በሻሽ ታንቆ እንዲገደል አድረገ፡፡ ከዚያ በኋላ ሁለት ንጉሶችን ሾመ፡፡

በዚህ መልኩ ኦሮሞና አማራ በጋራ ጉዳያቸው ላይ መስማማትና መተባበር ሲሳናቸው ራስ ሚካኤል ስሁል ጎንደር ላይ ፈላጭ-ቆራጭ ሆነ፡፡ የጎንደር በሽብር እንድትዋጥ አደረጋት፡፡ በራሳቸው ጠርተው ያስገቡትን ሰውዬ በስንት ጦርነት ከጎንደር አስወጡት፡፡ ራስ ሚካኤል ስሁል ከጎንደር ከወጣበት ግዜ ዘመነ መሳፍንት የሚባለው ዘመን ተጀመረ፡፡ የጎንደር ዘመነ መንግስት ከሞላ-ጎደል ያከተመው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ መለስ ዜናዊ በኢትዮጲያ ፖለቲካ ላይ የሰራው ሥራ ከራስ ሚካኤል ስሁል ጋር አንድና ተመሣሣይ ነው፡፡

በአጠቃላይ ለኦሮሞና አማራ ልሂቃን ከታሪክ መማር ይኖርባቸዋል፡፡ አንድ አይነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ነገር ግን፣ የተሳሰረ ህልውና ስላላቸው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እርስ በእርስ መተባበር አለባቸው፡፡ ባንዲራና አርማ ምርጫ አለው፡፡ የኦሮማራ ትብብር ግን ምርጫና አማራጭ የሌለው የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ወይ አብረን እንኖራለን፣ አሊያም አብረን እንጠፋለን!!

No comments