Latest

በደሴ ሸዋበር መስጂድ በተከፈተ ድንገተኛ ጥቃት በሰው ህይወትና አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ። (ዘሪሁን ገሠሠ)


በደሴ ሸዋበር መስጂድ በተከፈተ ድንገተኛ ጥቃት በሠው ህይወትና በአካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሠ፡፡ የጥቃቱ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ 34 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በደሴ ከተማ የሸዋበር መስጂድ ከመግሪብ ሰላት በኃላ፤ በተሠባሠበው ህዝበ ሙስሊም ላይ፤ ተደራጅተው በገቡና እስካሁን ስለማንነታቸው የጠራ መረጃ ያልተሠጠባቸው ቡድኖች በመጥረቢያና በገጀራ በመታገዝ በከፈቱት ድንገተኛ ጥቃት በርካታ ሠዎች ተጎዱ፡፡

ከደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል፤ ተጎጂዎችን እርዳታ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ የሚገኘው የአይን እማኝ በስልክ እንዳረጋገጠልኝ፤ ጥቃት ፈፃሚዎቹ ከአሁን በፊት በመስጂዱ በሠላት ወቅት የማይታዩ አዲስ ሠዎች ሲሆኑ፤ ለጥቃቱ የሚገለገሉበትን ገጀራና መጥረቢያ በመስጂዱ ጀርባ አስቀምጠው፤ የመግሪብ ሠላት ከሚሠግደው ምዕመን ጋር በመቀላቀል፤ ሶላቱ ተሠግዶ ካበቃ በኃላ፤ ቁርአን በመቀራት ላይ እያለ ያስቀመጡትን መሳሪያ በማምጣት ተቀምጦ ዱዓ በማድረግ ላይ ያለውን ህዝበ ሙስሊም ጨፍጭፈውታል፡፡

አሁን ባለው መረጃ በጥቃቱ ከ10 በላይ ሠዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የመጀመሪያ እርዳታ እየተሠጣቸው ሲሆን፤ አንድ ግለሠብ በመንገድ ላይ እያለ ህይወቱ ማለፉን ነግረውኛል ሲል በስልክ ያነጋገርኩት ወጣት ተናግሯል፡፡

ጥቃቱ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰ በኃላ ከስፍራው የደረሠው የአድማ ብተና ጦር፤ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ "ቦንብ ሊጣል ይችላል፤ ስለዚህ ኮሚቴ ከነዋሪው አዋቅሩና ህዝቡን በትኑ፡፡ በእኛም ላይ ጥቃት ሊሠነዘር ይችላል" በማለቱ ኮሚቴ ተዋቅሮ፤ በጥቃቱ ተሳትፈዋል ከተባሉት ውስጥ 19 እና 15 በድምሩ 34 ተጠርጣሪዎች በሁለት መኪና ተጭነው ወደፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል፡፡

በርካታ የጥቃቱ አድራሾች ግን እንዳመለጡም ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ ሸዋበር በአሁኑ ሠአት ተኩሱም የቆመ ሲሆን፤ ህዝቡም በአድማ ብተና ወደቤቱ እንዲገባ ተደርጓል፡፡

No comments