Latest

ተጨማሪ መረጃ - በአዲስ አበባ ሰልፍ የቦምብ ጥቃት ሰዎች ሞቱ በብዛት ቆሰሉ


የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚን አማን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አንድ ሰው መሞቱን አስታወቁ። ምኒስትሩ በጥቁር አንበሳ፣ ቤተዛታ፣ ጋንዲ፣ ዘውዲቱ፣ አቤት እና ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታሎች 132 የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። እንደ ምኒስትሩ መረጃ ከሆነ 8ቱ የከፋ ጉዳት የገጠማቸው ናቸው።
በዘውዲቱ ሆስፒታል ያሉ የሕክምና ባለሙያ እና የአይን እማኝ በመስቀል አደባባዩ ፍንዳታ ተጎድተው ወደ ሆስፒታሉ ከመጡት ውስጥ የሞተ አለመመልከታቸውን ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ ቢያንስ 60 ሰዎች ሕክምና እየተደረገላቸው ነው። የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው ለተሻለ ሕክምና ወደ የካቲት እና ራስ ደስታ ሆስፒታሎች ተወስደዋል ተብሏል።
 

ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል በፖሊስ የሚጠበቁ ይገኙበታል። የጠቅላይ ምኒስትሩ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በመስቀል አደባባይ የቦምብ ጥቃት እስካሁን የሞተ ሰው አለመኖሩን በትዊተር ገፃቸው ገልጸዋል።

ኃላፊው የፖሊስ እና የሆስፒታል የመረጃ ምንጮችን ጠቅሰው 86 መቁሰላቸውና 6ቱ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ፅፈዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቀደም ብሎ 115 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጾ ነበር።


የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ በጥቃቱ ማዘኑን ገልጿል። "ኢትዮጵያ ትርጉም ያለው የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች እያደረገች ባለችበት ወቅት ኹከት ቦታ የለውም" ሲል ኤምባሲው በትዊተር ገፁ አስነብቧል።  

No comments