በመስቀል አደባባይ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ በ83 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ ገለፀ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ላመጧቸው ለውጦች ድጋፍ እና እውቅና መስጠትን ዓላማ አድርጎ ዛሬ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደው ሰልፍ ላይ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ 83 በሚደርሱ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ፖሊስ ገለፀ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች ውስጥ 15 ሰዎች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ በሂደት ከተጣራ እና ከፖሊስና ሆስፒታሎች መረጃዎች ከተሰበሰቡ በኋላ በተገኘው መረጃ መሰረት በፍንዳታው እስካሁን የሞተ ሰው የለም ብለዋል። ይሁን እንጂ ስድስት ሰዎች በከባድ የጤና ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።
ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመሩ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያን ከጎናቸው መሆናቸውን ለማረጋገጥ ያለ ልዩነት በተሳተፉበት በዚህ ሰልፍ ላይ በመዲናዋ ታሪክ ከፍተኛ የሆነ ህዝብ መውጣቱንም ነው ምክትል ኮሚሽነሩ ያስታወቁት።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬው ሰልፍ ላይ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን መግለፃቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ የእርሳቸው አመራር የጀመረውን የለውጥ ጉዞ በመደገፍ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ይህ በመሆኑ እንዳሳዘናቸውም ነው ያመለከቱት።
No comments